ውሳኔው የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል ትልቅ እድል ይዞ የመጣ ነው

መንግሥት ላለፉት ስድስት ዓመታት በተጠና መንገድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ከነዚህም ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሰው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ነው ።

ሀገሪቱ ያላትን አቅም ታሳቢ ያደረገ፤ እነዚህን አቅሞች ወደ ልማት በመለወጥ የሕዝባችንን የዘመናት የመልማት/የመበልጸግ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂክ ዕይታዎችን ያካተተው ይህ ፕሮግራም፤ ከሁሉም በላይ የውስጥ አቅምን አሟጦ መጠቀምን ታሳቢ ያደረገ ነው ።

ፕሮግራሙ እስካሁን ባለው አፈጻጸም፣ ለሀገሪቱ ልማት ወሳኝ ናቸው ያላቸውን የቱሪዝም፣ የግብርና፤ የኢንዱስትሪ፣ የማዕድን እና የቴክኖሎጂ ዘርፎችን በመለየት እና ለዘርፎቹ ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው በማድረግ ተስፋ ሰጭ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል። በዚህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማነቃቃት ባለፈ ተከታታይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አስችሏል።

ይህንን እንደ ሀገር እየተመዘገበ ያለውን ልማት ለማስቀጠል እና ዘለቄታ እንዲኖረው ለማስቻል አሁን ላይ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ትግበራው ቀደም ሲል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊበራይዝ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም የውጪ ኢንቨስትመንት ከመሳብ፣ በሕገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ በማዳን ሀገሪቱን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ እየተፈታተናት ያለውን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ በመፍታት ለተጀመረው ልማት አቅም የሚሆን ሀብት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ይሆናል።

እስካሁን የነበረው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት የተረጋጋ የውጪ ምንዛሪ ተመንና ዝቅተኛ የዋጋ ንረት መኖሩን ለማረጋገጥ የታለመ ቢሆንም፣ በሂደት ግን ለጥቁር ገበያ መስፋፋት፣ ለከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ በከበሩ ማዕድናት ለሚደረግ ሰፊ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ ከባንክ ሥርዓት ውጭ እንዲሆንና ከሀገር እንዲሸሽ አንዱና ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

በውጭ ምንዛሪ የሚካሄድ ኢ-መደበኛ ገበያዎች እንዲስፋፉ በማድረግ፣ አብዛኛው የንግድ ማኅበረሰብና የሐዋላ ተገልጋዮች የሚፈልጉትን የውጪ ምንዛሪ ከጥቁር ገበያ እንዲገዙ እና እንዲሸጡ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ከአምራች ዘርፎች ይልቅ ጥቂት ሕገወጦችና ደላሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሥር የሰደደ የውጪ ምንዛሪ እጥረት እንዲከስት አድርጓል፡፡

በዚህ የተነሣ በርካታ የንግድ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ተጎጂ ሆነዋል፤ የወጪ ንግድንና የፋብሪካ ምርቶችን ለማስፋፋት፣ የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ የተቀመጡ ፖሊሲዎችንና ጥረቶች በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ እንዳይሆኑም ተግዳሮት ሆኗል፡፡

አሁን ላይ ወደ ሥራ የገባው አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት፤ ሀገሪቱን በገበያ ላይ የተመሠረተ ተወዳዳሪ ወደሆነ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት የሚያሸጋግራት፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውንና ሥር የሰደደውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚያሻሻልም ይታመናል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጪ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ የንግድ ሥርዓቱ ከአጎራባችና ከሌሎች ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡

በተለይም ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት እና ከፍተኛ የሰው ኃይል አቀናጅቶ ዘላቂ ልማት ለመፍጠር የሚያስፈልገውን ሀብት ከተለያዩ አማራጮች /በብድር፣ በርዳታ እና በቀጥታ ኢንቨስትመንት/ ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይታመናል።

ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሂደት ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን በማስቻል፣ እንደሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞ ትልቅ አቅም መሆን እንደሚችል፣ በተመሳሳይ የታሪክ ምዕራፍ ካለፉ ሀገራት ተሞክሮ ለመረዳት በብዙ የሚያዳግት አይሆንም!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You