የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ ተስፋ!

የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮች ትናንት ጀምረዋል። ኢትዮጵያ በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ትልቅ ተስፋ ካደረገችባቸው ርቀቶች አንዱና ዋነኛው የወንዶች 10ሺ ሜትር ፉክክር ዛሬ ምሽት 4:00 ይካሄዳል።

የቶኪዮ 2020 የርቀቱ አሸናፊ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻና በሪሁ አረጋዊ በዚህ ፉክክር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ወጣት አትሌቶች ሲሆኑ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምትም ተሰጥቷቸዋል። ሦስቱ አትሌቶች ባለፉት ዓመታት በርቀቱ ኢትዮጵያን በዓለም ሻምፒዮናና ኦሊምፒክ መድረኮች ወክለው ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን ትልቅ አቅም እንዳላቸው አሳይተዋል። እነዚህ አትሌቶች በውድድር ዓመቱ ምርጥ ብቃት ላይ ከመገኘታቸው በተጨማሪ በልምድም በስለው ነው ለዛሬው ፍልሚያ የሚቀርቡት።

ከሁለት ኦሊምፒኮች በኋላ የርቀቱን ድል ወደ ኢትዮጵያ የመለሰው ሰለሞን ባረጋ ፓሪስ ላይ ተመሳሳይ ድል ለመድገም ጠንክሮ ሲዘጋጅ የቆየ አትሌት ሲሆን ዳግም የወርቅ ሜዳሊያውን የማጥለቅ ጉጉት እንዳለው በዝግጅቱ ወቅት ተናግሯል። ሰለሞን ከቶኪዮ በኋላ በተካሄዱት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በርቀቱ ወርቅ ማጥለቅ ባይችልም አሁን ካለበት አቋም አኳያ የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ የነበረውን ድክመት አርሞ ወደ ፍልሚያው ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ከወር በፊት በማላጋ በተካሄደው የአትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ላይ ሰለሞን ዮሚፍ ቀጄልቻንና በሪሁ አረጋዊን ተከትሎ ሦስተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። ይሁን እንጂ በርቀቱ ኦሊምፒክ ላይ ወርቅ የማጥለቅ እንዲሁም የፉክክሩን መንፈስ የመረዳት ልምዱ ከሁሉም ተፎካካሪዎቹ የበላይ ያደርገዋል።

በኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ወንዶች ውድድር አንድ የተለመደ ባሕል አለ። ከፓቮ ኑርሚ እስከ ኤሚል ዛቶፔክ፣ ከላሲ ቪረን እስከ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ከቀነኒሳ በቀለ እስከ ሞ ፋራህ አንድ ጊዜ በርቀቱ ኦሊምፒክ ላይ ያሸነፈ አትሌት በቀጣይም ባለድል ሆነው ታይተዋል። ሰለሞን የእነዚህን የቀድሞ ከዋክብት ታሪክ ይደግማል ወይስ አዲስ ሻምፒዮን ይታያል? ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ነው።

የ24 አመቱ ኮከብ አትሌት ሰለሞን ዳግም በርቀቱ ለመንገሥ ጉጉት የሚያሳድርበት ሌላም ምክንያት አለው። በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ የወንድ አትሌቶች ታሪክ ከአንድ በላይ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ታሪካዊው አበበ ቢቂላ፣ ኃይሌ ገብረሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ ብቻ ተጠቃሽ ናቸው። ሰለሞን ከእድሜው አኳያ ሌላ የኦሊምፒክ ዕድል ቢኖረውም ዘንድሮ ሁለተኛውን የኦሊምፒክ ወርቅ አጥልቆ ከወዲሁ የእነዚህን ሕያው ከዋክብት ታሪክ መጋራት ይፈልጋል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ የርቀቱ ኮከብ ዮሚፍ ዘንድሮ የተለየ ድንቅ ብቃት ላይ ይገኛል። በማላጋው ማጣሪያ ቀዳሚ ከመሆኑ ባሻገር የውድድር ዓመቱን ፈጣን ሰዓት እንዲሁም የርቀቱን የምንጊዜም ስድስተኛ ፈጣን ሰዓት በ26:31.01 አስመዝግቧል። የ27 ዓመቱ ኮከብ ከስምንት ዓመት በፊት በሁለት ተከታታይ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናዎች የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ቢችልም በኦሊምፒክና በዋናው የዓለም ሻምፒዮና ወርቅ ማሳካት አልቻለም። በነዚህ ዓመታት ግን የኦሊምፒክ ወርቅ ሲያልም ኖሯል። ይህን ሕልሙን እውን ለማድረግ ፓሪስ ትክክለኛው ጊዜ ይመስላል። በዚህ ኦሊምፒክ በ5ሺ ሜትርም የመወዳደር ዕድል የነበረው ቢሆንም በመጨረሻ ሰዓት በ10ሺ ሜትር ብቻ ለመሮጥ ተገዷል። ሙሉ ትኩረቱና ዝግጅቱም በዚሁ ርቀት ብቻ ይሆናል።

በማላጋው ማጣሪያ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የ23 ዓመቱ ወጣት ኢትዮጵያዊ ኮከብ በሪሁ አረጋዊ በኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና በርቀቱ ልምድ እያካበተና እየበሰለ የመጣ አትሌት ነው። የ2023 የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊም ሲሆን በቶኪዮ ኦሊምፒክም አራተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። ዮሚፍ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ባስመዘገበበት ውድድርም በጥቂት ሰከንዶች ብቻ ነው የተበለጠው። ይህ ትልቅ አቅም ያለው ወጣት ኮከብ ሁሌም ውድድሮች ከመጀመራቸው አስቀድሞ ለአሸናፊነት ከሚታጩ አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ አይጠፋም።

ሦስቱ ኢትዮጵያውያን እንደቡድን ተረዳድተው መሮጥ ከቻሉ አንድ የተለየ ታሪክ ሊሠሩ የሚችሉበት አቅም አላቸው። ምናልባትም 1936 ላይ የፊንላንድ አትሌቶች በርቀቱ ሁሉንም ሜዳሊያ ጠራርገው የወሰዱበትን ብቸኛ ታሪክ ሊደግሙ ይችላሉ ብለው የዓለም አትሌቲክስ ፀሐፍትም ግምታቸውን አስፍረዋል። ይህን ለማድረግም ይሁን የወርቁን ሜዳሊያ ለማጥለቅ ግን አንድ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል። ያም ያለፉት ሦስት የዓለም ሻምፒዮናዎች አሸናፊውና የርቀቱ የክብረወሰን ባለቤት ዑጋንዳዊው ጆሽዋ ቺፕቴጌ ነው።

ቺፕቴጌ በዚህ የፈረንጆች ዓመት በ10ሺ ሜትር ምንም አይነት ውድድር ላይ አልታየም። ከሁለት ወር በፊት ግን በ5ሺ ሜትር ዘጠነኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። ወቅታዊ አቋሙ ባይታወቅም ምናልባትም ለዛሬው ፍልሚያ ድምፁን አጥፍቶ ሲዘጋጅ እንደከረመ ግን መገመት አይከብድም። ቺፕቴጌ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በርቀቱ በሰለሞን ተቀድሞ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀበትን ቁጭት በ5ሺ ሜትር እዚያው ቶኪዮ ላይ መወጣት ቢችልም የ10ሺ ሜትሩን ክብር ማሳካት ካለበት ከፓሪስ የበለጠ ጥሩ አጋጣሚ የለውም። ለዚህም ነው ለኢትዮጵያውያኑ ከዋክብት ትልቅ ፈተና ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው።

የኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ስጋት የሚሆነው ቺፕቴጌ ብቻ አይደለም። የምንጊዜም ኃያል ተፎካካሪ የሆኑት ኬንያውያንም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም። ዳንኤል ማቴኮና የዓለም የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊው ኒኮላስ ኪፕኮሪር ፈጣን ሰዓት ያላቸው ኬንያውያን ናቸው። በዚህ የፈረንጆች ዓመት በራስ አል ካይማህ ግማሽ ማራቶን ያሸነፈው ማቴኮ ከወር በፊት ዩጂን በኬንያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ የራሱን ፈጣን ሰዓት በ26:50.81 አስመዝግቦ አሸንፏል። ኪፕኮሪር ደግሞ በሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ5ሺ ሜትር አራተኛ ሆኖ ነበር የፈፀመው።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You