መንግሥት የንግድ ዘርፉን ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ እና ፍትሐዊ እንዲሆን ለማስቻል የተለያዩ የፖሊሲ ርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። በተለይም የሀገሪቱን የንግድ ዘርፍ በራሱ ጊዜ እና አቅም ወደሚፈለግበት ደረጃ እንዲደርስ ለማስቻል ሰፊ ጥረቶችን አድርጓል። ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታትም ለዚሁ ሲባል ለዘርፉ በፖሊስ ደረጃ ከፍተኛ ጥበቃ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይህም ሆኖ ግን ዘርፉ እንደ ሀገር ወደሚፈለገው ደረጃ ከመድረስ ይልቅ፣ በተለያዩ ሕገወጥ አስተሳሰቦች እና አሠራሮች ተጠላልፎ፣ የመላው ሕዝባችንን ሕይወት በከፋ ሁኔታ እየፈተነ፤ ላልተገባ እሮሮ እና ችግር ሲዳርገው ቆይቷል። አሁንም በተመሳሳይ መልኩ እየተፈታተነው ይገኛል ።
በሀገሪቱ ኮሽታ በተሰማ ቁጥር ሸቀጦችን ከመደበቅ ጀምሮ፣ ያልተገባ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የሕዝባችንን አጠቃላይ የዕለት ተዕለት ሕይወት ችግር ውስጥ ከቷል፣ የሀገር ኢኮኖሚ ፈተና መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል። ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችም ሀገራዊ ከሆነው የመቆጣጠር አቅም ውስንነት ጋር ተዳምሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ቆይቷል ።
ችግሩ መንግሥት ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት አውጥቶ በሚደጉማቸው ሸቀጦች ላይ ሳይቀር በስፋት ሲስተዋል ቆይቷል። ይህ ኃላፊነት በማይሰማቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ዘንድ እየተስተዋለ የመጣው፤ ከአጠቃላይ ከሕዝባችን ባሕል እና ወግ ያፈነገጠ ራስ ወዳድነት፣ ሕዝብ ጥራታቸው የተጠበቁ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደ አቅሙ አማርጦ እንይገዛ ፈተና ሆኖበታል።
ከሁሉም በላይ መንግሥት የንግዱ ዘርፍ በሀገር ውስጥ ተዋንያን እጅ ሳይወጣ ዘርፉን ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ እና ፍትሐዊ እንዲሆን በፖሊሲ ደረጃ ሲያደርግ የነበረው ጥበቃ ትርጉም የለሽ እንዲሆን አድርጎታል። ፖሊሲው በዘርፉ ተዋንያን የተሳሳተ እሳቤ መንገድ ስቶ አጠቃላይ የሆነውን የዘርፉን ዕድገት በብዙ እንዲቀጭጭ እና ሕዝብም አላስፈላጊ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል ።
ከዚህ የተነሳም ዓለም በብዙ አማራጮች ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ እና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓት ፈጥራ፣ ብዙዎች የዚህ ተጨባጭ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ተጠቃሚ እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ፣ ኢትዮጵያውያን ግን የዘርፉ ተዋንያን በፈጠሩት የተዛባ አስተሳሰብ እና ራስ ወዳድነት የተነሳ፣ በሚፈጠረው ያልተገባ ጫና ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህንን ችግር ለመፍታት በመንግሥት በኩል የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፣ ችግሩ በአስተሳሰብ ሆነ በአሠራር ደረጃ ካለበት አስቸጋሪ ደረጃ አኳያ፣ ጥረቶቹ በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። እንዲያውም መሽቶ በነጋ ቁጥር አዲስ የችግር አቅም እያጎለበቱ የሕዝባችንን ሮሮ ከማባበስ አልፈው ዋነኛ የሕይወቱ ፈተና ሆነው ቀጥለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት በቅርቡ መንግሥት የሀገሪቱን ንግድ ነፃ (ሊበራላይዝድ) ማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ለውጥ አድርጓል። በዚህም ለንግዱ ዘርፍ ሲያደርግ የነበረውን የፖሊሲ ጥበቃ በማንሳት ዘርፉ በተወሰነ ደረጃ ለዓለም አቀፍ ገበያ ክፍት እንዲሆን ወስኗል። የፖሊሲ ለውጡ ከሁሉም በላይ ሕዝባችን ሸቀጦችን በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በብዙ አማራጮች ማግኘት የሚያስችለውን ዕድል የሚፈጥርለት እንደሚሆን ይታመናል።
ሕገ ወጥ ነጋዴዎችም ከቀደመው ያልተገባ መንገዳቸው ተመልሰው በኃላፊነት መንፈስ፣ ተወዳዳሪነትን መሠረት ባደረገ የንግድ ሥርዓት ተገርተው፣ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን በታማኝነት ማገልገል የሚችሉበትን መልካም አጋጣሚ ለመፍጠር ይረዳል፣ በቀጣይም በተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ የንግዱ ማኅበረሰብ የራሱን ትርጉም ያለው ዐሻራ እንዲያሳርፍ የተሻለ አቅም እንደሚፈጥርለትም ይታመናል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲም፤ ይህንን እንደሀገር የጀመርነውን የንግዱን ዘርፍ ሊበራላይዝድ የማድረግ እንቅስቃሴ ዋንኛ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በንግዱ ዘርፍ ብዛት ያላቸው ዓለም አቀፍ ተዋንያን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተሻለ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡
በተለይም የውጪ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ የሚደነግገው የመንግሥት ውሳኔ፣ በዘርፉ ገዝፎ የነበረውን ሕገወጥነት በማስቀረት፣ ሕዝባችን ሸቀጦችን በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በብዙ አማራጮች ማግኘት የሚያስችለውን የተሻለ አማራጭ የሚፈጥር፤ የንግድ ዘርፉን ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ እና ፍትሐዊ እንዲሆን የሚያስችል ነው!
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም