የአሜሪካ ብሔራዊ ዕዳ መጠን ከ35 ትሪሊዮን ዶላር አለፈ

የአሜሪካ ብሔራዊ ዕዳ መጠን ከ35 ትሪሊዮን ዶላር አለፈ፡፡

የዓለማችን ልዕለ ሃያል ሀገር አሜሪካ የዕዳ መጠኗ ከ35 ትሪሊዮን ማለፉን የሀገሪቱ ግምጃ ቤት በድረገጹ አስታውቋል።

የሀገሪቱ የእዳ መጠን በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የዋጋ ግሽበት መፈጠሩ፣ ለዩክሬን እና እስራኤል የተሰጠው ርዳታ በየጊዜው መጨመር እና የፊታችን ሕዳር ወር ለይ የሚደረገው ምርጫ መንግሥት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን እንዲጨምር አድርጓል ተብሏል።

የአሜሪካ መንግሥት እዳ መጠን ባሳለፍነው ጥር ላይ 34 ትሪሊዮን ደርሶ የነበረ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ተጨማሪ ብድር መበደሩ ተገልጿል።

አሜሪካ ያለባት ብድር ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርቷ በላይ ነው የተባለ ሲሆን ብድሩ ከዓመታዊ እድገቱ ጋር ሲነጻጸር 120 በመቶ ደርሷል ተብሏል፡፡

የሀገሪቱ ብድር መጠን በዚሁ ከቀጠለ በ2054 የአሜሪካ ጠቅላላ ብድር ከዓመታዊ እድገቱ ጋር ሲነጻጸር 166 በመቶ ያህል እንደሚጨምር ተገልጿል፡፡

የብድር መጠን መጨመሩን ተከትሎ በርካታ አሜሪካውያን ፖለቲከኞች እና ነጋዴዎች ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን ጉዳዩ መፍትሔ እንደሚያሻው በመናገር ላይ ናቸው፡፡

አሁን ላይ የአሜሪካ መንግሥት በየቀኑ አምስት ቢሊዮን ዶላር እየተበደረ ነው የተባለ ሲሆን ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ይህ እብደት ነው ሲል በኤክስ አካውንቱ ላይ ጽፏል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You