የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተጀመረውን ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያስችላል!

በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከመጣበት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ7 በመቶ በላይ እያደገ መሄዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ:: በተለይም ሀገሪቱ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ይህን መሰል ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏ እንደ ሀገር ጠንካራ ሥራ መሠራቱን የሚያመላክት ነው::

ቀላል የማይባለው የሀገሪቱ ክፍል በጦርነትና በጸጥታ ችግር ውስጥ ሆኖ በቆየበት ወቅት ሁሉ ከስድስት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ ከለውጡ ወዲህ የተቀየሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው::

ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን በተከታታይ ከወጭ ንግድ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች:: ሀገሪቱ ፍጹም ሰላም በነበረችባቸው ዓመታት እንኳን ከወጭ ንግድ ሲገኝ የነበረው ዓመታዊ ገቢ ቢበዛ ከ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ዘልሎ አያውቅም::

ከ2010 ዓ.ም በኋላ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች እንድታጤንና ለውጭ ገበያም በስፋት እንድታቀርብ ዕድል ከመክፈቱም ውጪ በከፍተኛ ወለድ ስትበደር የነበረበትን አካሄድ በማቆም በአንፃሩ የልማት አጋሮቹ ከሆኑት ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከመንግሥታት ትብብር በአነስተኛ ወለድ ለረጅም ጊዜ በሚሰጡት ብድሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል::

ሆኖም አሁን ያለው የልማት ፍላጎት በዚህ ብቻ የሚሳካ አይደለም:: ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚጠይቅ ነው:: ከዚህም በላይ በሀገር ውስጥ የገንዘብ ፍሰትን ማሳለጥና የውጭ ምንዛሬን በገበያው እንዲመራ ማድረግም አስፈላጊ የሆነበነት ወቅት ላይ ደርሰናል::

ስለዚህም ወቅቱን በሚዋጅ መልኩ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓት ውስጥ መግባት የግድ ሆኗል:: ይህን መሠረት በማድረግም ከሀምሌ 22 ጀምሮ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የገባች ሲሆን ይህም ሀገሪቱ ለጀመረችው የኢኮኖሚ ብልጽግና ትልቅ አቅም ይሆናል የሚል እምነት ተጥሎበታል::

የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በሚያስገኙ ዘርፎች የተሠማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ይጠቅማል:: ወደ ውጭ የሚላኩ እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት የመሳሰሉ ሸቀጦችን የሚያመርቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች፣ የቁም እንስሳትና ሥጋ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አርብቶ አደሮችና ነጋዴዎች፣ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሠማሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ በርካታ ዜጎችና አምራቾች፣ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፎች የተሠማሩ በሺህ የሚቆጠሩ ነጋዴዎች፣ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው/ ጓደኞቻቸው የውጭ ምንዛሪ የሚላክላቸው በሚሊዮን የሚገመቱ የሐዋላ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ከውጭ ገንዘብ ፈስስ የሚደረግላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ተቋማት፣ ከእነዚህም ጋር በሽርክና የሚሠሩና ምርት የሚያቀርቡ ሌሎች አካላት የዚህ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በማድረግ ጤናማ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖር ያስችላል:: ይህ መሆኑ ደግሞ ሀገሪቱ ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ በማድረግ ተስተጓጉለው የነበሩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችና የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ያስችላል::

ከዚሁ ጎን ለጎንም የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ያበረታታል፤ የማምረት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል::

መመዘኛውን የሚያሟሉ የውጭ ኢንቨስተሮችም በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Secu­rities Exchange) እንዲሳተፉ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን እንዲጨምር ያደርጋል:: በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው መያዝን ጨምሮ ልዩ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መብት የሚያናጽፋቸውም በመሆኑ ገንዘባቸውን በሀገር ውስጥ እንዲያፈሱ ያነሳሳቸዋል:: በምትኩም በሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል::

ከሁሉም በለላይ ደግሞ የዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማትና ሀገራት አቋርጠውት የነበረውን ርዳታ እና ብድር እንዲለቁና ኢትዮጵያም ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የምታገኘውን ብድርና ርዳታም ቀጣይነት እንዲኖረው ያስችላል:: ይህ ማለት ደግሞ በፋይናንስ እጥረት የቆሙ የልማት ውጥኖች እንዲተገበሩና ኢትዮጵያ የጀመረችው ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ያስችላል::

በአጠቃለይ የሀገር በቀል ማሻሻያ ሥርዓቱ ቀጣዩን የኢትዮጵያን የዕድገት ደረጃ ከፍ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር ከቀረው የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን እና እያደገ የመጣውን ትስስር ለማጠናከር የሚረዳ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም

Recommended For You