ከካሜራ በስተጀርባ ብዙ ጉዳዮች ሆድና ጀርባ ናቸው ከቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ እንደ ፊት መስታየት የምንመለከታቸው ምስሎች ወደ ገሀዱ ዓለም ሲመጡ ግን ያንኑ መሳይ እውነተኛ ምስል አያስመለክቱንም የመስታየቱን አቅጣጫ እየዘወሩ ሲያስመለክቱን የነበሩ ሰዎችን ምስል ከእውነተኛው የሕይወት መስታየታቸው ላይ ከተመለከትነው ምናልባትም አራንባና ቆቦ ሊሆንም ይችላል የጠላነውን ወደን የምንወደውንም አምርረን እንጠላው ይሆናል የሚያበግኑን ቀዝቀዝ እንዳለ ውሃ የሚያረሰርሱን ሆነው ይገኛሉ
ከካሜራው ፊት ከነበረው ይኼው መስታየት ውስጥ ጨካኝ የመሰሉ ከካሜራው በስተጀርባ የርህራሄን ጥግ ሊያሳዩን ይችላሉ ሲያስቁን የነበሩ በራሳቸው ሕይወት ግን ሊያስለቅሱን እንደሚችሉ አይተናል ከካሜራው ፊት ለጋሽና መጽዋች የነበሩት ከገሀዱ ቀማኝ ዘራፊዎች ሆነው ብንመለከት አይግረመን በኑሯቸውና ባላቸው ነገር ቀንተን ምነው እነርሱን ባደረገኝ ያልናቸው ሰዎችን ምናልባትም መልሰን ከእነርሱስ ሰውረኝ የምንላቸው ይሆናሉ ከካሜራው በስተጀርባ የምንመለከተው አንዳንድ እውነታ አንዳንዴም ሰቅጣጭ ነው እንደ እሬት ይመራል የምንጠብቀው እንዳልጠበቅነው፣ የምናውቀውም እንደማናውቀው ሆኖ የማናይበት ምክንያት የለም
ከካሜራ በስተጀርባ የምናደርገው ይኼው ምልከታችን የተቃና ይሆን ዘንድ ለማሳያነትም ስለ አንድ ፊልም እናነሳለን ፊልሙ በራሱም “ከካሜራ ጀርባ “ይሰኛል የፊልም ብቻም ሳይሆን የሕይወት ተዋንያንም እንዳሉ ይነግረናል እነማን ከካሜራ በስተጀርባ?…እውነተኛ የጥበብ ልጆች፣ ቤተኞች፣ ልማደኞችና ለምደኞች ይገኙበታል በበጎች መሀል የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችም አድፍጠውበታል ራሳቸውን ጎድተው የጥበብን አጥንት ከሚያለመልሙት ጎን ለጎን ቆመው ጥበብን እስከ አጥንቷ ድረስ እየቀረጠፉ የሚግጧት አልጠፉም ከካሜራው በስተጀርባ ያለው ትልቁ ውጋትም ገንዘብ ነው የጥበብ ካዝናዋ በገንዘብ የተራቆተ በመሆኑ ይህን ተከትሎ ደራሽ አልባሽ መስለው ከውጭ የሚገቡ የጥበብ አንበጦች ሞልተዋል እንደ አጠቃላይ ከካሜራው ጀርባ የፊልምና ድራማ ተዋንያንን፣ ደራሲና ዳይሬክተሮችን፣ አዘጋጅ ፕሮዲዩሰሮችን፣ ሙዚቀኛ ድምጻውያንን፣ የሚዲያ ጋዜጠኞችና የማኅበራዊ ሚዲያ ዘዋሪዎችን እናገኛለን እንዲሁም ደግሞ በየዘርፉ ውስጥ በየስርቻው የተሸጎጡትን ደላሎችንም አናጣም
ተባርከው ለጥበብ የቆሙ፣ እንደ እርግማን መዥገር ተጣብቀው የሚመጠምጡትንም እናይ ይሆናል እነርሱ እስካሉ ድረስ ብቃትና ብቁነት ሁሌም ቦታ አለው ማለት ከንቱ እምነት፣ የባዶ ጣሳ ጩኸት ነው ተክሎች እየተረገጡ አረሞች ተኮትኩተው ሊንዠረገጉ ይችላሉ እውነታዎች ተደፍጥጠው ቅጥፈቶች ሊያብቡና ፍሬ የሚሰጡ መስለው ሊታዩም ይችላሉ::::
በሁሉም የጥበብ ዘርፎች ውስጥ የተጠናከረ ኢንዱስትሪ ባለመኖሩ ለተራቡ ጅቦች መና መስሎ ቢታይ አይደንቅም ጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች በሀብት ላይ ሀብት፣ በዝና ላይ ዝና የሚታጠቁበት ዓለም ከካሜራው በስተጀርባ እንደተጎለተ ነው በዚህ ምክንያትም ለፍቶ አዳሪዎች ጾም አዳሪ ናቸው በሥራቸው እንደፊኛ ተወጥረው በቀለማት ሲንሳፈፉ የምናውቃቸው በኑሯቸው ግን የተነፈሰ ፊኛ መስለው ይታያሉ ስማቸው እንደ ጎልያድ ገዝፎ ሕይወታቸው ግን እንደ ዳዊት ጠጠር በተአምር ነው ዋንጫና ሰርተፍኬቱ ክምር ጓዳና ኪስ ግን ቁር ይሆናል ሁልጊዜም ባይሆን አዘጋጁ በሽልማት ዝግጅቶች አመሃኝቶ የራሱን ኪስ በመሙላት፣ ለሠራውና ለተሸላሚው ግን ጠብ የሚል ነገር ሳያደርግ በስሙ ሲነግድበት መኖር አለ::
ጥበብና የጥበብ ሰው ለሸቀጥ ገበያ አውጥተው በካሜራ ካስገመቱና ካስጎበኙ በኋላ “በሉ ደህና ሰንብቱ!” ይባላሉ የካሜራው ጀርባ እንጂ የካሜራው ፊት ይህን አይነግረንም ሁሌም አሳምሮና አስጊጦ ሲደልለን ይኖራል::
“ከካሜራ ጀርባ” ፊልም…የዚህ ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ኤሊያስ ወርቅነህ ሲሆን፤ ጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም ተመርቆ ለእይታ በቅቷል ከዚህ ቀደም በፊልሞችም ይሁን በድራማዎች ውስጥ ከካሜራ ፊት ያለውን የራሳችንና የማኅበረሰባችንን ሕይወት በአርቲስቶቹ ውስጥ ስንመለከት ቆይተናል በዚህ ፊልም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከካሜራ በስተጀርባ ያለውን የራሳቸውን ሕይወት አሳይተውናል ፊልሙም በይዘትና በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ለማለት እንችላለን::
ከካሜራ በስተጀርባ ያሉትን የፊልም ዳይሬክተሮችን ሰቆቃና እንግልት የሚያስመለክተን ሞገስ በተሰኘው ገጸ ባህሪ ውስጥ ነው ይህ ገጸ ባህሪም የአብዛኛዎቹን የፊልም ደራሲና ዳይሬክተሮችን መልክ ተላብሶና ይዞ ሲጓዝ እንመለከታለን ሞገስ በፊልሙ ዘርፍ ዕውቅና አዋቂ ከመሆኑም በሠራቸው ሥራዎቹ በርካታ ዕውቅናና ሽልማቶችን ያገኘም ነው እጅግ ዝነኛና ሁሉም አብሮት ለመሥራት የሚፈልገው ዓይነት ሆኖ ይታያል በአሥር ፊልሞቹ የዓመቱ ምርጥ በመባልም በተለያዩ ጊዜያቶች አሸናፊ ለመሆን የበቃም ደራሲና ዳይሬክተር ነው ይህን ያህል ጊዜ እያሸነፈና እየተሸለመ የኖረው ሞገስ ግን በራሱ ፊልም ለመሥራት ቀርቶ ኑሮውን ለመምራት የሚሆነው ቤሳ ቤስቲን የለውም ፊልሙ ሲጀምር ገና ሞገስ አሸናፊ የሆነበትን የመድረክ አጀብ እያሳየን ይጀምራል ቀጥሎም የሽልማት ዋንጫውን በእጁ እንደታቀፈ አስፋልቱን በእግሩ እየደቃ ለብቻው ጥግ ጥጉን ይዞ እንደቆዘመ በእግር ወደ ቤቱ ሲመለስና ተጋፍቶ የታክሲ ወረፋ ሲጠብቅም ይገኛል::
ለሚሠራው አዲስ ፊልም ፕሮዲዩስ የሚያደርገውን ፍለጋ የማይጠናው የባለሀብት ደጅ የለም አንዳንዶቹም ይስማሙና የወደዱትን ገጸ ባህሪ “እኔ የምጫወተው ከሆነ…እገሊትን እገሌን…” የሚል ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጡለታል ይወጣና ይሄዳል አብዛኛዎቹም ሀገራዊና ታሪካዊ ጭብጥ የያዘውን ፊልም ኮሜዲ አድርገህ የምትሠራው ከሆነ ብቻ ይሉታል አሁንም ጥሏቸው ይሄዳል ከብዙ ፍዳና አሳር መልስም ፕሮድዩስ የሚያደርገውን ያገኛል ነገር ግን ልፋትና ውጣውረዱን የምትመለከተው እህቱ ግን ለጉዳይ ያስቀመጠችውን 4 መቶ ሺህ ብር ሥራበትና ትመልሳለህ በማለት ትሰጠዋለች የፊልም ሥራው ከተጀመረ በኋላም በከባድ ህመም ሲሰቃይ የሚኖረው የእህቱ ልጅ ሁኔታ ጭንቀት ሲዘራበት እንመለከታለን ከዚያ በፊት በሠራው በአንደኛው ፊልሙ ውስጥ ያሠራትን አንዲት ሴትንም በአጋጣሚም መንገድ ያገኛታል እርሱ ባሠራት ፊልም ምክንያት የውጭ ሀገር ዕድል አግኝታ፣ ሀብትም አካብታ ባለጠጋ ለመሆን የበቃች ነበረች ከተመለሰች በኋላም ላደረገላት ውለታ ለፊልም ሥራው የሚረዳውን ዘመናዊ ካሜራ ብትልክለትም አበሳው ከጉምሩክ ደጃፍ ጠበቀው ከመንግሥት አካላት በየጊዜው የተሰጡትን ሰርተፍኬቶች በቦርሳው አጭቆ ቢሄድም ካሜራው የተገዛበትን አንድ ሦስተኛ ያህል ዋጋ ቀረጥ እንዲከፍል ተገደደ ለመክፈል ያቅተውናም ካሜራው ወደመጣበት እንዲመለስ ይደረጋል
“የጥበብ ቤርሙዳ…“ከካሜራ በስተጀርባ” ሌላ አንድ አስቀያሚ የሕይወት ዐሻራ ከነመዳፉ ያስመለክተናል ሴትነትን ተላኮ፣ ውበት ላይ አድፍጦ እንደ እሽኮኮ ሹክክ! እያለ ይቀርባል ይጠጋል እንደ እባብ በደረቱ እየተሳበ ደርሶ ይናደፋል የሳር ውስጥ እባብ ሳያዩት ሳያስተውሉት ምራቁን እየደፈቀ ተጠቅልሎ ጭን ውስጥ ይሸጎጣል ሴትነትን ያራክሳል ውበትን ያጠለሻል ገንዘብ ዓይን አስጨፍኖ ህሊናን ይደፍናል በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእሳት ረመጡ የሚንተከተክበት የነውር መጋረጃ ተሰቅሏል ዝነኛም ይሁኑ ጀማሪ፣ በካሜራ ውስጥ ያለፉ ቆንጆ አርቲስቶችን በተመለከቱ ቁጥር እንደ ሸቀጥ በገንዘብ ገዝተው፣ ከቀናቸው የእርድ በሬ ያደርጓቸዋል በየሙዚቃው ክሊፕ ውስጥ የሚሠሩ ሞዴሎች፣ የፊልም ተዋንያን፣ ድምጻውያን፤ በአጠቃላይ በኪነ ጥበቡ አካባቢ በሚሠሩ ዕውቅ የጥበብ ባለሙያ ሴቶች ላይ ያንዣበበው ጭልፊት አሞራ የዋዛ አይደለም::
በዚህ ፊልም ደራሲው እውነታውን በፊልሙ ውስጥ ሲያሰፍር፣ ራሱ ዳይሬክተሩም መርቶ ገሀዱን ሲገልጥ ከጉያቸው ስር ከሚሆነው በመነሳት ነው በፊልሙ ውስጥ አብረው በአንድ ቤት ውስጥ ከሚኖሩት ከአራት ሴት ገጸ ባህሪ መካከል ሁለቱ የፊልም ተዋንያን ናቸው አንዷ ሴት የሙዚቃ ክሊፖች ላይ የምትሠራ ሞዴል ስትሆን፤ ሌላኛዋ ደግሞ በማስታወቂያው ዘርፍ ላይ የምትሠራ ሆና ትገኛለች::
ከካሜራ ፊት ብዙኃኑ የሚያውቃቸው ቆነጃጂት የጥበብ ባለሙያ ናቸው ከካሜራ በስተጀርባ ግን ለማመን የሚከብድ አስቀያሚና ወልጋዳ ሕይወት የሚኖሩ ሆነው ይገኛሉ የሚፈልጉት ዝናን ብቻ አይደለም ገንዘብ ትልቁ የሕይወት መርህ ቁልፋቸው ነው ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ደግሞ በባለገንዘቡ እቅፍ ውስጥ ይወድቃሉ ቆነጃጅቱን እና ባለሀብቱን የሚያገናኘው መስመር ደግሞ ጥቁር የንስር ዓይን በያዙ ደላሎች ይታጠራል ደላላውም አማራጩን በምግብ ሜኑ መልክ ያቀርብለታል ፈላጊውም የሴቶቹን ሁኔታ ከነፎቶ የያዘውን ባህረመዝገብ እያገላበጠ፣ የፊቷን ውበት እየመዘነ፣ የጭንና ዳሌዋን ወርድና ስፋት እየለካ “ለዛሬው ይህቺ ትሁንልኝ” ይላል::
ለቆነጃጂቱም ቀድሞውኑ መስመሩ ላይ ያሉበት ከሆነ የሎተሪ ዕጣ የወጣላቸው ያህል ነው ከባለሀብት ባለሀብት፣ ከገንዘብ ገንዘብ፣ ከሀገር ሀገር እያማረጡ ዓለማቸውን መቅጨት ብቻ ቆንጆና ያማረ ቅንጡ መኪና ይዞ ሀገር ምድሩን እንቁልልጭ ማለት ብቻ ምናልባትም የባለሀብቱና የደላላው ፈተና የሚበዛው አዳዲስ ብቅ በሚሉና ገና ባልተቀጠፉ ትኩስ አበባዎች ነው ምክንያቱም ለእርዱ ቢታጩም እነርሱ ግን የመጡት ለጥበብና ለሙያው ፍቅር ነውና “ወግድ ዞር በል!” ማለታቸው አይቀርም::
በፊልሙ ውስጥ የቡድኑ አምስተኛ አባል ሆና የምትመጣዋ ሴት የአንደኛዋ የልጅነት ጓደኛ ናት ከልጅነቷም ጀምሮ ተዋናይ የመሆን ልዩ ፍላጎትና ምኞት አላት ከክፍለ ሀገር ሆና ከቤተሰብ ጎረቤቱ ጋር ተሰባስበው ጓደኛዋ የተወነችባቸውን ፊልሞች በተመለከቱና ቃለ መጠይቆቿን በተከታተለች ቁጥር ሁሉ እየደወለች “እባክሽን እኔም ወደ ትወናው የምገባበትን መንገድ አመቻቺልኝ” በማለት ትማጸናታለች የትወና ፍቅሯንና ህልሟን፣ በዝነኛዋ ጓደኛ ከካሜራ ፊት ከቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ የምትመለከተውን የሚያስቀና ሕይወት እንጂ ከካሜራ በስተጀርባ ስላለው የጉድ ዓለም የምታውቀው አንድም ነገር የለም ውስጠ ሚስጥሩን የምታወቀው ዝነኛዋ ጓደኛዋም የእርሷ ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባት ስትል ለብዙ ጊዜያት “እንደምታስቢው ቀላል አይደለምና ይቅርብሽ” ስትልና ጥያቄዋን ስትገፋባት ኖራለች ገፍታ ስትመጣባት ግን ጥያቄዋን ተቀብላ መንገዶችን ለማመቻቸት እንደምትሞክርላት በመግለጽ ቃል ትገባላታለች::
ልጅትም ጓዟን ጠቅልላ ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ትመጣለች በደባልነት ከሚኖሩት የቆነጃጅት ማኅበርም ተቀላቅላ ነገረ ሥራዎቻቸውን ሁሉ ትመለከትና በልቧም ትታዘባቸው ነበር ከባሕል ወግና ሥርዓት ያፈነገጡ ድርጊቶቻቸውን እየተመለከተች ደስ የማይሉ ስሜቶች ያጭሩባት ነበር ገና በመጀመሪያዎቹ ቀናትም ለብሳ የመጣችውን ቀያይረው የእነርሱን አለበሷት ባይመቻትም ሙደገዳዳ ላለመባል የእነርሱንም ተጫማች የሀር መሳይ ባለ ቆንዳላ ጸጉሯን ዘመናዊ መልክ አበጃጁለት ከሁሉም ነገሮቻቸው እያሸተቱ ይዘዋት ወደ ጭፈራ ቤት አቀኑ::
ድሮም ውብ ልጃገረድ ነበረችና ከዚያ ጭፈራ ቤት ውስጥ የተመለከታት ቅንዝረኛ ሁሉ ዓይኖቹን ሰዶ በስሜት እረመጥ ይቃጠል ጀመረ ገና በመጀመሪያው ዕለትም አዲሶቹን ጓደኞቿን ጠጋ ብሎ ለሽያጭ እንዲያቀርቡለት ይጎተጉታቸውም ገባ እያመቻቹና እያመቻመቹ ግድ የለህም አታስብ በማለት በዚያው የመጀመሪያ ዕለት ከልጅነት ጓደኛዋ ጋር ወደ ቤት የሸኛቸው ሀብታም “እንቺ ለጸጉርሽ መሠሪያ” በማለት የታሠረውን ረብጣ ብር ያወጣል አይሆንም ብትልም ጓደኛዋ “ያዢ ለጸጉርሽ ነው ምን ታካብጂያለሽ” በማለት ብሩ እንዳያመልጥ ከሰውየው ተቀብላ በእጇ ታሲዛታለች ገና በቀናት ውስጥም ያቺ ጨዋ ልጅ አመል ጀማመራት ልክ እንደ እነርሱው እየሆነች መጥታ እነርሱንም አስናቀች ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ ሄደች ክንፍ አውጥታም በረረች ክንፏ ተሰብሮም ወድቃ ተሰበረች::
በኪነጥበብ ሥራዎች ውስጥ በፍጹም…ፍጹምነት አይኖርም “ከካሜራ ጀርባ “ፊልም ውስጥ ደራሲው አንድ አዲስ ነገርን ለማስመለከት የሄደበትን መንገድ አለማድነቅ አይቻልም ጥሩ ነገሮቹ እንዳሉ ሆነው፤ ነገር ግን እንደ ባለሙያ ሳይሆን እንደ አንድ ተመልካች የታየኝን ክፍተት ለማንሳት እወዳለሁ ርዕሱ ሰፊና ግዙፍ እንደመሆኑ ከካሜራ ጀርባ ያለውን ሁሉንም እውነታዎች አጭቆ በአንድ ፊልም ውስጥ ለማስቀመጥ የማይቻል እንደመሆኑ እይታውን ለሁሉም እውነታዎች አማካኝ በሆነ መንገድ ከማስቀመጥ አንጻር ይጎድለዋል::
ሁሉንም ባለሙያዎች ከማማከል ይልቅ በሁለት የታሪክ ጽንፎች ላይ የሚጓዝ ዓይነት ነው በዋናነት የሚታዩት ጀርባዎች በደራሲና ዳይሬክተሮች ስቃይ እና ውበታቸውን በመጠቀም ያለቦታቸው ገብተው በሚፈታፈቱ ቆነጃጂት ሴቶች ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ ሚዛናዊ የሆነውን የበስተጀርባ እውነታ ለማግኘት ፈታኝ ያደርገዋል የገጸ ባህሪያቱ የማንነት ስሮች የተንሳፈፈ ነገር ይታይባቸዋል ከመነሻው ጀምሮ በአንድ መሠረት ላይ ከሚጓዝ የታሪክ ፍሰት ይልቅ ቅንጭብጭብ ያሉ ትዕይንቶች በዛ ብለው የሚታዩበት በመሆኑ ብዙ ነገሮች ግልጽ እንዳይሆኑ ያደርገዋል እኚህ ሁሉ እያሉም ግን ፊልሙ እጅግ ውብና ድንቅ ነው::
ከፊልሙ መጨረሻ…ፊልሙ ተሠርቶ ተጠናቀቀ በተመረቀ ዕለትም ከውጭ ሀገር የመጡ የፊልም ባለሙያዎች ተመልክተው ወደዱለት ለአንድ የውጭ የፊልም ፌስቲቫልም ፊልሙ ተመረጠ ያ የእህቱ ትንሽ ልጅም በድንገት ይታመምና ወደ ውጭ ሀገር ወስዶ ለማሳከም ሲል ፊልሙን ለሚገዙ በርካሽ ያቀርብላቸዋል በዚህ መሀልም ፊልሙ ተሰርቆ ዩቲዩብ ላይ ተጭኗል የሚል መርዶ ይሰማል የነበራትን ገንዘብ ሁሉ ለፊልም ሥራው የሰጠችውን የእህቱን ልጅ ለማዳን ሲል በየጎዳናው ሁሉ ሳይቀር መለመን ይጀምራል “ይኼ ደራሲና ዳይሬክተሩ ሞገስ አይደል…ምን ሆኖ ነው?፣ ያው ገንዘቡን በሱስ ጨርሶት ይሆናል…” እያሉ የሚያፌዙበትም ነበሩ በመጨረሻም ቀደም ሲል ካሜራ ልካለት ከነበረችው ደግ ሴት 1 ሚሊዮን ብር ይደርሰዋል ወዲያውኑ ሲሮጥ እያለከለከ እህቱ ቤት ደጅ ላይ ከመድረሱ የለቅሶና የዋይታ ጩኸት ይሰማል አምርሮ እያለቀሰም ከመሬቱ ላይ ይወድቃል ይህ ሁሉ ጉድና መአትም ከካሜራው ጀርባ ያለ ነው::
ጥበብ መከራና መዘዟ ብዙ ነው የሚወዳት እየተረገጠ የሚጠላት ሊሾምባት ይችላል ገፊዎች እየተንደላቀቁ ጥበበኞችን ሲያረግፉ መኖርም አለ በኛ ሀገር የጥበብ ኢንዱስትሪ ውስጥ በብዛት የምንመለከተው ከደረሰው ፍሬ እየቀጠፉ የሚበሉት ሥራውን የሠሩት ልፋተኞቹ ሳይሆኑ ከዳር ቆመው የሚያሠሩት ናቸው “በጨው ደንደስ በርበሬ ትወደስ” እንዲሉ የሠራው ፈጦ ያልሠራው ይጨበጨብለታል አንዱ በሌላው ጫንቃ ላይ ቆሞ ምስጋናና ሀብት፣ ዝናና በረከት ያጋብሳል የሠራው ከሥራው በልቶ ሊጠግብ ሲገባው የበይ ተመልካች ሆኖ እያሸተተው ብቻ ዕድሉን ወይ ሙያውን ሲራገም ይኖራል::
“ከካሜራ ጀርባ” በፊልሙ ውስጥ የአንድ የፊልም ዳይሬክተር ሆኖ የሚጫወተው ሞገስ የተሰኘው ገጸ ባህሪ እንዲህ ዓይነቶቹ ነገሮች ተስፋ አስቆርጠውት ቢያጣ ወደ አረብ ሀገር ለመሰደድ የወሰነባቸው ጊዜያት ብዙ ነበሩ ጥበብ ግን ለስቃይ ጣር ሁን ብላ አሁንም እየጎተተች ገፍታ ወደመሀል ታስገባዋለች ብዙ የጥበብ ሰዎች “ጥበብ የማይለቅ ዛር አለባት” ሲሉ ግነት ወይም ውሸት አይደለም ይኼው ዛር ባይኖርማ የካሜራን ጀርባ ተመልክቶ በቤቷ የሚቀመጥ ማንስ ይኖር ነበር? አብዛኛውን ጥበበኛ ጠልፋና ጠላልፋ የምታስቀምጠው በዚሁ ዛሯ ነው፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም