222 ወረዳዎች ተለይተው የወባ በሽታ ቅኝትና ክትትል እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ 222 ወረዳዎች ተለይተው የወባ በሽታ ቅኝትና ክትትል እየተደረገ ነው ሲል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የወባ በሽታ ስርጭት ከመስከረም እስከ ታህሳስ እና ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ጫናው ይጨምራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በ222 ወረዳዎች ተለይተው የወባ በሽታ ቅኝትና ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡

ባለፈው አንድ ወር 700 ሺህ የወባ ህሙማን ህክምና እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፣ ከ6 ሚሊዮን በላይ ህሙማንን ማከም የሚችሉ የጸረ ወባ መድኃኒት መሰራጨቱንና ሰባት ሚሊዮን በላይ ፈጣን መመርመሪያ ኪት ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል 551 ሺህ ተጨማሪ አጎበሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እየተሰራጩ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ባለፉት ቀናት አንድ ነጥብ ስምንት ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት መካሄዱን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ 152 ወረዳዎች ላይ በተደረገ የኮሌራ በሽታን የመቆጣጠር ሥራ 109 ወረዳዎች ነጻ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት 43 ወረዳዎች ላይ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በ 444 ወረዳዎች ላይ የነበረውን የኩፍኝ ወረርሽኝ በተደረገው ክትትል ከ422 ወረዳዎች ላይ ነጻ ማድረግ ተችሏል ያሉት ዶክተር መቅደስ፣ በቀሪ 22 ወረዳዎች ላይ የመቆጣጠር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በተጨማሪም በጥቂት ሳምንታት በተደረገ አሰሳ ምንም አይነት ክትባት አግኝተው የማያውቁ 600 ሺህ ህጻናትን ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም የጸጥታ ችግር ባለባቸው የተለያዩ አካባቢዎች መንግሥት የህክምና መድኃኒቶች ለዜጎች እያቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ የሚቀርቡለትን የህክምና መድኃኒቶች ሊጠቀምባቸው እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የጸጥታ ችግር ባለባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የህክምና መድኃኒትን ጨምሮ ግብዓቶች እየቀረቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች ተሠራጭተዋል፡፡

የጸጥታ ችግር ባለባቸው የአማራ፣ በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ በተለየ ሁኔታ የመድኃኒት ስርጭት እየተካሄደ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ባለፉት ወራት ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች ተሠራጭተዋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል በባህርዳር፣ ጎንደርና ደሴ፣ በቤኒሻንጉል አሶሳ ቅርንጫፎች ላይ መሰራጨታቸውን ጠቅሰው፣ የአየር ትራንስፖርትን በመጠቀም ጭምር የክትባት፣ የኤችአይቪ፣ ቲቢ፣ የወባና ሌሎች አስፈላጊ መድኃኒቶች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25  /2016 ዓ.ም

Recommended For You