
ጎንደር፡- በ2016 በጀት ዓመት ለ105 አልሚ ባለሀበቶች 92 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ማስተላለፉ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሀይ ገለጹ::
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሀይ እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ጎንደርን የኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል:: በ2016 በጀት ዓመት ለ105 አልሚ ባለሀበቶች 92 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ተሠጥቷል::
ባለፈው በጀት ዓመት 116 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 349 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት 92 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ለ105 ባለሀብቶች ማስተላለፍ መቻሉን ገልጸዋል::
በጎንደር ከተማ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው፤ በተያዘው ዓመት ብቻ 27 ፕሮጀክቶችን ወደ ምርት ለማስገባት ታቅዶ 23ቱ ምርት ማምረት ጀምረዋል:: ሰባት ፕሮጀክቶች ደግሞ ማሽን ተከላ ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል::
ኢንዱስትሪዎች እንደ ሀገር የሚገጥመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን እንዲፈቱና ምርትን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ያሉት ከንቲባው፤ በዚህ ዓመት ስምንት ኢንዱስትሪዎች 18 ሺህ 328 ቶን ምርትን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ 49 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል ብለዋል::
ባለፉት ዓመታት በክልሉና በከተማው አቅም አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮችን መከለል እንደተቻለ ገልጸው፤ አራቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው ለባለሀብቶች ተላልፈዋል:: ኢንዱስትሪ መንደር ቁጥር አምስት ደግሞ ለባለሀብቱ ካሳ እየተላለፈ ይገኛል ነው ያሉት::
በአምስቱም የኢንዱስትሪ መንደሮች 46 በቅድመ ግንባታ፣ 137 በግንባታ ላይ ፣ ግንባታ ያጠናቀቁ 70፣ በምርት ላይ ያሉ 192 በአጠቃላይ 445 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል::
እንደ አቶ ባዩህ ገለጻ፣ ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ የከተማውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሳላጥ ባለፈ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት፣ ተኪ ምርትን ለማምረትና የሥራ እድል ለመፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ::
ባለፈው በጀት ዓመት ወደ ሥራ እየገቡ ባሉ ኢንዱስትሪዎች ብቻ ለአምስት ሺህ 71 ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል::
አካባቢው የቅባት እህሎች፣ ቅመማቅመምና ሌሎች ሰብሎች የሚመረትበት በመሆኑ ለአግሮ ፕሮሰሲንግና ለሌሎች ዘርፎች ምቹ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን የተሰሩት ሥራዎች ከተማው ከሚፈልገውና ካለው የልማት እድል አንጻር በቂ ባይሆንም በጸጥታ ችግር ውስጥ ሆኖ የተሠሩት ሥራዎች ተስፋን የሚሰንቁ ናቸው ብለዋል::
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 /2016 ዓ.ም