ለአንድ ሀገር ህልውናም ሆነ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ሀገራዊ ኢኮኖሚ ወሳኝ ነው። በተለይም በዕድገት የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ሀገራት እና ሕዝቦች የጀመሩት ለውጥ ትርጉም ያለው ፍሬ አፍርቶ ወደ ሁለንተናዊ እድገት ለመሸጋገር በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚኖራቸው አቅም አልፋ እና ኦሜጋ እንደሆነ ይታመናል ።
ይህንን ተጨባጭ ዓለም አቀፍ እውነታ ተሳቢ በማድረግም እነዚህ ሀገራት እና ሕዝቦች ፤ አጠቃላይ ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ የለውጥ ራዕያቸውን እውን ለማድረግ ቀደም ሲል የተፈጠሩትንም ሆነ ለውጡ የፈጠራቸውን አማራጮችን ፤ ለሀገራዊ ኦኮኖሚ እድገት አቅም አድርገው ይጠቀማሉ ። በዚህም ለተሻለ ዕድገት የበቁ ሀገራት ጥቂት አይደሉም ።
ዛሬ ላይ የዓለምን ኢኮኖሚ በበላይነት ለመቆጣጠር እየገሰገሰች ያለችው ቻይናም ሆነች ፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከፍርስራሽ ውስጥ የወጡ የአውሮፓ እና የእስያ ሀገራት የዕድገት ትርክት ጅማሮም ፤ በየወቅቱ የነበሩ መልካም አጋጣሚዎችን ብሔራዊ ጥቅምን በማይጎዳ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ከመቻላቸው ጋር የተቆራኘ ነው።
በርግጥ ለውጥ በራሱ አዲስ /የተሻለ ነገር ከመፈለግ የሚመነጭ ማኅበረሰባዊ መሻት ነው፡፡ ይህንን መሻት እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የቀደሙ አስተሳሰቦች አሻጋሪ ሊሆኑ አይችሉም ። በእነሱ መንገድ የሚደረግ የለውጥ ጉዞ አክሳሪ እና “አዲስ የወይን ጠጅን በአሮጌ አቁማዳ” እንደሚባለው አይነት ከመሆን የዘለለ አይሆንም።
ለውጥ የሚፈጥረውን አዲስ ሀገራዊ ራዕይን እውን ለማድረግ አዲስ መንገድ ያስፈልጋል። ይህ መንገድ ከሁሉም በላይ ሁሉንም አማራጮች ማየትንና ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ መመላለስን የሚጠይቅ ነው ። ከተለመዱ የስጋት ትርክቶች ወጥቶ በከፍተኛ ኃላፊነት እና በሰከነ መንፈስ እንዲሁም በልበ ሙሉነትና በጠንካራ ዲሲፕሊን መጓዝን የሚጠይቅ ነው።
በተለይም ባለንበት ዘመን የማደግ መሻት ያላቸው ሀገራት እና ሕዝቦች እያጋጠማቸው ካለው ውስብስብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመውጣት ፤ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውነታችን በአግባቡ ተረድቶ ፤ ስኬታማ የለውጥ ጎዞ ለመጓዝ የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
ችግሮችን እየተረኩ ከመቆዘም ፣ችግሮች የሚያስከፍሉትን ዋጋ ለምዶ ከመዘናጋት ወጥቶ ፣ እያንዳንዱ ችግር ምንጭ እንዳለው ሁሉ ፤ መፍትሄ እንዳለው አውቆ እና ተረድቶ ፤ ለዘለቄ መፍትሄ ስር ነቀል ርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የለውጥ አመራር ስብዕና መላበስ የሚፈልግ ነው።
በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም የሀገራትም ሆነ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ በብዙ መዋዠቆች ውስጥ በሚገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ፤ ከፍተኛ የሕዝብ መሻት የፈጠራቸውን የለውጥ መነሳሳቶች ስኬታማ ለማድረግ፤ የለውጥ አመራሩ ኃላፊነት የማይተካ እንደሆነ ይታመናል ። ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት ማዳበርም የሚጠበቅ ነው።
ከዚህ አንጻር በሀገራችን የለውጥ ኃይሉ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ማግስት ጀምሮ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የለውጥ መሻቶችን ሁሉ የሚሸከም ለማድረግ እየሄደበት ያለው መንገድ በብዙ መልኩ ተስፋ ሰጪ ነው ። ሀገሪቱ አጋጥሟት የነበረውን አስቸጋሪ የፈተና ወቅት በማሻገር ሂደት ውስጥ የነበረው አበርክቶም ሀገርን ፍጹም ከሆነ ጥፋት የመታደግ ያህል እንደነበር ይታመናል።
በ2011 በጀት ዓመት ወደ ትግበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ሰፊ የፖሊሲ ሃሳቦችን በውስጡ ያካተተ ፤ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያካተተ እና ያሳካ ነው፤ በፕሮግራሙ ተግባራዊ የሆኑ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎች ሀገራዊ ኢኮኖሚው ወደ ተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሸጋገር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም በተደረገው ጥረት ትርጉም ያለው ውጤት ተገኝቷል።
ከ2010 እስከ 2015 ባሉት በጀት ዓመታት በአማካይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ሰባት ነጥብ አንድ በመቶ ደርሷል። በዚህም ሀገራችን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ምሕዳር ጉልህ ሚና ያላት ሀገር ለመሆን በቅታለች። ከሰሐራ በታች ካሉ አፍሪካ ሀገራት የሦስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤትም ሆናለች።
በቅርቡ የፀደቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ከሰሞኑ መተግበር የጀመረው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ትግበራ ቀሪ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያስችል እንደሚሆን፤ የፕሮግራሙን ትግበራ ተከትሎ ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ነጠላ አኅዝ የዋጋ ግሽበት እንደሚኖር ይታመናል።
የውጭ ምንዛሪ መዛባትን በማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር፣ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር የታክስ ገቢን በማሳደግ፣ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት በማሻሻል፣ የመንግሥት ዕዳ ዘላቂነትን በማረጋገጥ፣ የባንክ ዘርፍን ተወዳዳሪነትና ጤናማነት በማጎልበት ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል ።
ይህ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ ዘላቂ በሆነ የዕድገት መሠረት ላይ እንዲዋቀር የሚያስችለው የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ ሀገር ከስጋት ትርክቶች ወጥታ ከሁሉም በላይ ብሄራዊ ጥቅምን መሠረት ባደረገ መንገድ ፣ ዘመን በሚዋጅ እሳቤ እና በሚጨበጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ መሻገር የሚያስችል ነው።
ሀገራዊ ኢኮኖሚው የሕዝባችንን የለውጥ መሻት ሊሸከም በሚችል መልኩ አቅም እንዲያጎለብት በማስቻል ፤ ለተጀመረው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ታሪካዊ ጉዞ ስኬት ትልቅ አቅም የሚሆን ፤ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ፤ የሚደገፍ እና የሚበረታታ ተግባር ነው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም