ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከፍ ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን እየተጋፈጠችና እየተሻገረች፤ ዕድሎችና ድሎችንም እየፈጠረችና እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ በተለይ ከለውጡ ማግስት ያሉ ስድስት ዓመታት፤ እንደ መንግሥት ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን እየተጋፈጠ፣ ፈተናዎችን ደግሞ እንደ ዕድል በመጠቀም በፈተና ውስጥ ጣፋጭ ድሎች እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
በዚህም በአንድ በኩል እንደ ሀገር የገጠመውን የግጭትና ጦርነት አዙሪት ዘላቂ እልባት በመስጠት ከችግሮቹ ባሻገር እያሰበ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እየሠራም ይገኛል፡፡ በሌላው በኩል የዜጎችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ብሎም ሌሎች አስተዳደራዊና የሰላም ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችለውን የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡
ይሄ የዜጎችን ጥያቄ የመመለስ ጉዞ ደግሞ ሁሉ ነገር ቀና ሆኖለት የሚጓዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም በአንድ በኩል የውስጥ የሰላም እና ተያያዥ የአሠራር ችግሮች በእጅጉ አንቀው ይዘውት ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ከፍ ብላ መራመዷ የማይዋጥላቸው ኃይሎች በተለያየ መልኩ ጫና ሲፈጥሩባት እና የልማቷ እንቅፋት በመሆን ውጫዊ የእጅ ጥምዘዛ ተግባራትን መፈጸማቸው ኢኮኖሚዋ ላይ የሚያሳርፈው ጫና አለ፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ሀገራዊም ሆኑ ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልታሳካ ካለመችው የብልጽግና መንገድ ፈጽመው ሊያስተጓጉሏት አልቻሉም። ምናልባት ፈተናዎቿን አብዝተው በሚፈለገው ፍጥነት እና ልክ እንዳትጓዝ የቤት ሥራ ይጨምሩባት እንደሆነ እንጂ፤ እስካሁን ባለው ጉዞ ግን መንግሥት ችግሮችን በብልሃትና እውቀት ላይ ተመስርቶ መፍትሔ እየሰጠ፤ የሀገርና ሕዝብን ጥቅም አስጠብቆ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እየተጓዘ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያም የዚህ የሀገርን እና ሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ ከችግሮች ልቆ የመገኘትና የመሻገር ጥበብ አብነት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፈች ከፍ ያለ ድል እያስመዘገበችበት ባለችበት በዚህ ወቅት፤ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ መሸጋገሯ፣ እንደ ሀገር በፈተናዎች ውስጥ ያሉ አቅሞችና ዕድሎችን መለየት ያስቻለ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣይ የሚገጥሙ ፈተናዎችን መሻገሪያ የሚሆን አቅምን መፍጠር የሚያስችላት ነው፡፡
በፖሊሲ ማሻሻያው ማብራሪያ ላይ የተገለጠው እውነትም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በመግለጫው እንደተመላከተው፤ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ የገባችው በተለያዩ ምዕራፎች ተግባራዊ ስታደርጋቸው በነበሩ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች እና በመካከለኛው ዘመን የኢንቨስትመንትና የልማት እቅድ ላይ ተመስርታ ነው፡፡
በመሆኑም፣ የፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራሙ እንዲሳካ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ጥረቶችና ድርድሮች ከልማት አጋሮች ጋር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህ መልኩ ከተከናወነው ስምምነት እና ከተገኘው ድጋፍ ባሻገር በቀጣይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የራሱ የሆኑ ዋና ዋና ርምጃዎችና የሚጠበቁ ሀገራዊ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ እና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮች የሚደገፈው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያበረክት የሚጠበቀው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እና ውጤቶች አሉ፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ከማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው፣ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት የመዘርጋት ተግባር አንዱ ሥራ ነው፡፡
ይሄ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት የመዘርጋት ተግባር ደግሞ፣ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን የማድረግ ሂደት ነው። በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ ደግሞ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል፤ የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል። በክፍያ ሚዛን ላይ ያለውን አለመመጣጠንም ለማስተካከል ይረዳል። ከዚህም ባለፈ ዘላቂና አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ፣ የዋጋ ግሽበት መጠንን ዝቅ ለማድረግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግና ሀገራዊ የውጭ ምንዛሪ አቅምን ከፍ ለማድረግ ወዘተ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
በዚህ ረገድ የሚጠበቀው ውጤት ይገኝ ዘንድም ይሄንን በትናንትናው እለት ብሔራዊ ባንክ “የውጪ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ”ን ወደትግበራ አስገብቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን፣ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲን ሥርዓትን መዘርጋት፤ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ፤ የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስተዳደርን ማሻሻልን የመሳሰሉ ጉዳዮችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡
ምክንያቱም በፖሊሲ ማሻሻያው የሚጠበቁ ውጤቶች ሊገኙም ላይገኙም የሚችሉት በእነዚህ ጉዳዮች ትግበራ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እያንዳንዳቸው ትግበራዎች የሁሉንም ባለድርሻዎች፣ ዜጎች፣ ምሁራንና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማትን ከፍ ያለ ኃላፊነትን የመወጣት ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ትግበራው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን እንዳይጎዳም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መጓዘንም ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ውጤታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም