በኢትዮጵያ እግር ኳስ በርካታ ተጫዋቾችን በማፍራት ተጠቃሽ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል አርባ ምንጭ ከተማ እና አካባቢው አንዱ ነው:: ከዓመት ዓመት እግር ኳስ እንደተሟሟቀ የሚካሄድባት አርባ ምንጭ ያፈራቻቸው ከ85 በላይ ተጫዋቾች በዚህ ወቅት ብቻ ከብሔራዊ ሊግ እስከ ፕሪምየር ሊግ ባሉት የውድድር እርከኖች ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ:: በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ከአርባ ምንጭ የተገኙ በርካታ ተጫዋቾች ሃገራቸውን የሚወክሉ ሲሆን፤ ይህንኑ በአደረጃጀትና በውጤታማነት አጠናክሮ ለመቀጠል የከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት በትኩረት እየሠራ ይገኛል::
የከተማዋ መለያ የሆነው አርባ ምንጭ ከተማ(አዞዎቹ) ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወረድ ዓመት ራሱን አጠናክሮ በከፍተኛ ሊጉ ብልጫ በማስመዝገብ ወደ ተፎካካሪነቱ መመለስ መቻሉ ይታወቃል:: ይህንንም ተከትሎ ክለቡ በገቢ ተጠናክሮ ራሱን እንዲችል ለማድረግም ሃገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌታ ሽታ ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል:: ሃብት በማሰባሰብ ሂደቱም ሕዝባዊ የሩጫ ውድድር፣ የአደባባይ የቦክስና የቴኳንዶ ውድድሮች እንዲሁም ከተማዋ ያፈራቻቸው አንጋፋ ተጫዋቾችን የሚያሰባስብ ዝግጅት ለማከናወን ታቅዷል::
በመላው ኢትዮጵያ ክለቦች ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ተጫዋቾችም የውድድር ዓመቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የክረምቱን ወቅት የሚያሳልፉት በከተማዋ እንደመሆኑ የተለያዩ ውድድሮች ይዘጋጃሉ:: ልማት ካፕ እና ሰመር ካፕ በሚል ውድድሮች እየተካሄዱ ሲሆን፤ በዚህም ሂደት ስፖርቱን ከማሳደግ ባለፈ ተተኪ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን በማፍራት እንዲሁም አዳዲስ ተጫዋቾች በክለቦች ዓይን እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም አላቸው:: ዘንድሮ 10ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ልማት ካፕ በዚህ ዓመት በድንገተኛ ሁኔታ ያለፈውን ወጣት ተጫዋች አለልኝ አዘነን በመዘከርም ነው እየተከናወነ የሚገኘው:: በሁለት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተጀመረው ይኸው ውድድር አሁን ላይ የመንግሥት እና የአካባቢው ወጣቶች ድጋፍ ታክሎበት በድምቀት በመካሄድ ላይ ይገኛል::
በከተማዋ በፊፋ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱትን ጨምሮ በአጠቃላይ የጋሞ ጎፋ ዞን ውስጥ ትምህርት ቤቶችን አካቶ ከ28 በላይ ፕሮጀክቶች (ከ15 እስከ 20 ዓመት የሆናቸውን ታዳጊ ወጣቶች የያዙ) መኖራቸውን ኃላፊው ይጠቁማሉ:: ይሁንና በከተማዋ ካለው የእግር ኳስ እንቅስቃሴ አንጻር ይህም በቂ ሊባል አይችልም:: በርካታ በጎ ፈቃደኛ አሠልጣኞችም በስፖርቱ ላይ የራሳቸው ዐሻራ በማሳረፍ ላይ ቢገኙም ሥልጠናቸው በልምድ እንጂ በዘመናዊ ሥልጠና የተደገፈ አይደለም:: ይህም የነገ ተስፋ በሆኑ ታዳጊዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል በመገንዘብ የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ሥልጠናን እየሰጠ እንደሚገኝ ኃላፊው አስረድተዋል:: በዚህም በእውቀት የታነጸ፣ በአእምሮና በአካል ብቁ የሆነ ትውልድ ለማፍራት እንደሚያስችል ይታመናል::
በእግር ኳስ ስፖርት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያላት አርባ ምንጭ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ትዝታ ሆኖ በቀረው አንጋፋው ክለብ አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ይበልጥ ይታወሳል:: ፋብሪካው አሁን ላይ በመልካም ሁኔታ የሚገኝ እንደመሆኑ ክለቡ በድጋሚ እንዲመሠረት ጽሕፈት ቤቱ ንግግር በማድረግ በቀጣይ ዓመታት እውን ሊሆን የሚችልበት ፍንጭ ተገኝቷል:: የከተማዋ መለያ የሆነው አርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ደግሞ ራሱን በገቢ እንዲችል እንዲሁም በስሩ የታዳጊ ክለቦችን በማቋቋም እንዲመጋገቡ በማድረግ ላይም በትኩረት እየተሠራ ነው:: ወደ አንደኛ ሊግ እንደሚያድግ ተስፋ የተጣለበት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ክለብም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል:: ሌሎች ክለቦች ደግሞ በባለሃብቶች ድጋፍ የተመሠረቱ ቢሆንም በአቅምና በአደረጃጀት አንጻር ውስንነት ያለባቸው በመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል::
ከተማው የእግር ኳስ ስፖርት ማዕከል ይሁን እንጂ የሚመጥነው ስታዲየም የለውም:: እጅግ በተጎዳውና ያልተሟላ መሠረተ ልማት ያለው ሜዳው ጨዋታዎችን ለማድረግም ይሁን ደጋፊውን ለማስተናገድ አስቸጋሪ በመሆኑ በሕዝቡ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች እንደሚነሱበት ይታወቃል:: በዚህም ላይ ከተማው ከሕዝቡ ጋር በመተባበር የፊፋን መስፈርት ያሟላ ሜዳ ለመገንባት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል:: ግንባታው የተጀመረ ሲሆን፤ ሕዝቡ ተሳታፊ እንዲሆንም የማሳመን ሥራ እየተሠራ ነው:: ለምሳሌ ያህል ዘንድሮ 19 ክለቦች የተሳተፉበት የአንደኛ ሊግ ውድድር በከተማዋ አዘጋጅነት ሲካሄድ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ከተማዋ ገቢ አግኝታለች፣ በመሆኑም ስፖርቱ ለአካባቢው ያለውን አስተዋፅዖ በማመላከትና ጥቅሙን በማሳየትም የሕዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሠራ ነው::
ከእግር ኳስ ባለፈ አካባቢው በአትሌቲክስ የሜዳ ተግባራት፣ ቦክስ እና መረብ ኳስ በመሳሰሉ ስፖርቶች እምቅ አቅም እንዳለው ይታወቃል:: ይሁን እንጂ በበቂ ሁኔታ እንዳልተሠራባቸው ኃላፊው ያምናሉ፤ ይህንንም ተከትሎ ከእግር ኳሱ ጎን ለጎን ውድድሮችን በማስፋፋት የላቁ ስፖርተኞችን የማፍራት ውጥን ይዘው እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ይጠቁማሉ:: በቅርቡ በከተማዋ የተካሄደው ታላቁ የአርባ ምንጭ ሩጫም በዚህ እንቅስቃሴ የራሱ ድርሻ እንደሚኖረውም ታምኖበታል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም