የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ!

የኢንቨስትመንት ዘርፍ በአጠቃላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በባሕሪው ሠላምና ፀጥታን በእጅጉ ይፈልጋል፤ ለኮሽታም ሳይቀር ስስ እንደሆነ ይነገርለታል:: ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ በሀገሪቱ የተለያዩ ግጭቶች ተከስተውም፣ የሰሜን ኢትዮጵያን ያህል ግዙፍ ጦርነት ተካሂዶም፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ላይ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ያደጉት ሀገሮች ጫናዎች አሳድረውም፣ ኮቪድ አሉታዊ ተፅዕኖውን አሳርፈውም ከመቀዛቀዝ ያለፈ፣ ስር የሰደደ ችግር አልታየበትም:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግም በሀገሪቱ መነቃቃት እየታየባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል ይሄው የኢንቨስትመንት ዘርፉ ይጠቀሳል::

መቀዛቀዙም ቢሆን ችግሮቹ መወገዳቸውን ተከትሎ ወደ መሟሟቅ ተሸጋግሯል:: በሌሎች ሀገሮች ባልተለመደ ሁኔታ እነዚህ ችግሮች በሀገሪቱ ቢከሰቱም የውጭዎቹን ጨምሮ በርካታ ባለሀብቶች በዘርፉ ሲሰማሩበት ቆይተዋል:: በሀገሪቱ የታዩት ችግሮች በሌሎች ሀገሮች እንደሚታዩት ችግሮች አይነት እንዳይደሉና ሊፈቱ እንደሚችሉም በማመን ነበር በባለሀብቶቹ በኢንቨስትመንቱ መስክ ሲሠማሩ የነበሩት::

የኮቪድ ወረርሽኝ እየቀነሰ ሲመጣና የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሲያቆም ደግሞ ዘርፉ ፈጥኖ ያገገመበት ሁኔታ ታይቷል:: ይህ መነቃቃት በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመትም ታይቷል::

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2016 በጀት ዓመትን አፈጻጸም በቅርቡ ባስታወቀበት ወቅት እንደጠቆመውም በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ጫና አሳድረው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እያገኙ በመምጣታቸው በዘርፉ መነቃቃት እየታየ መጥቷል:: በበጀት ዓመት በብዙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተስፋ ሰጭ ውጤት የተመዘገበበት ሁኔታም ይህንኑ እንደሚያመለክት ተጠቁሟል::

በዘርፉ ለውጦች ከታየባቸው መካከልም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ይጠቀሳል:: በኢንቨስትመንት ዘርፉ ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት በማምረቻው ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው:: ባለሀብቶች ሊሠማሩባቸው የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንደመኖራቸውና የተሳተፉበት ሁኔታም ቢኖርም አምራች ዘርፉ ብልጫውን ይዞ መገኘት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ብልጫውን ይዞ መገኘቱ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ጥሩ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያስገነዝባል::

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ባለሀብቶች በአምራች ዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ከጀመረች ቆይታለች:: ለሀገር በእጅጉ የሚበጀው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሆኑ በእጅጉ ታምኖበት በሰፊው ጥረት ተደርጓል፤ የማምረቻ ቦታ እና የመሠረተ ልማት ችግርን ለመፍታት ሲባልም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በብዛት በመገንባት ለባለሀብቶች በማቅረብ ላይም ተሠርቷል:: ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪው የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን ለዚህ ዘርፍ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ወደ ዘርፉ ለሚገቡ የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የማበረታቻዎች ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ናቸው::

ዘርፉ ሥራ ከጀመረ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ቆይቶም ቢሆን በዘርፉ ለውጦች መመዝገብ ጀመረዋል:: ያለፈው በጀት አፈጻጸም ከሌሎች ኢንቨስትመንቶች አኳያ ሲታይ የታየበት ሰፊ ለውጥ በተዓምር የመጣ አይደለም፤ በግብርናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን በማምጣት ኢንዱስትሪው የግብርናውን ስፍራ እንዲይዝ ለማድረግ፣ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣባቸው ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተከናወኑ ጠንካራ ሥራዎችን ተከትሎ የመጣ ውጤት ነው::

ባለፉት የለውጡ ዓመታት ባለሀብቶች ወደ አምራች ኢንዱስትሪው በስፋት እንዲገቡ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ የኢንቨስትመንት አዋጁ ተሻሽሏል፤ ሀገሪቱን ኢንቨስትመንት በቀላሉ የምትስብ እንድትሆን ለማድረግ ተሠርቷል፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለውጭ ባለሀብቶች ብቻ ይቀርቡ የነበረበትን ሁኔታ በማሻሻል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርኮቹን ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጭምር ክፍት የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ወደ ፓርኩ ለመግባት የሚያስፈልጉ ክፍያዎችን በኢትዮጵያ ገንዘብ መፈጸም እንዲቻል ተደርጓል፤ ይህን ሁሉ ተከትሎም ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እየተሳቡ ያገኛሉ:: እነዚህና የመሳሰሉት ተግባሮች የአምራች ዘርፉ አፈጻጸም ከሌሎች ዘርፎች አፈጻጸም የተሻለ እንዲሆን አርገዋል ብሎ መውሰድም ይቻላል::

በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እየተከናወነ ባለው ተግባር የዘርፉ ተግዳሮቶች የሆኑትን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የቦታ፣ የገበያና የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራትም ለዚህ ውጤት የራሳቸው ድርሻ አላቸው:: በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲሳቡ አላደረገም ማለትም አይቻልም::

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት በጥሩ ጉዞ ላይ መሆኑንም ያሳያል:: በዘርፉ እየታየ ያለው ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢንቨስትመንቱን ሊፈትኑ የሚችሉ ችግሮች ዛሬም ጥቂት ባልሆኑበት ሁኔታ፣ እንደ ሀገርም ቢሆን የዘርፉ ገበያ የሆነው አሜሪካ ከሰሐራ በታች የሚገኙ ሀገሮች ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገሪቱ እንዲያስገቡ የፈቀደችው ዕድል /አጎአ/ ለኢትዮጵያ ዝግ በሆነበት፣ አልፎ አልፎ የፀጥታ ችግሮች አሁንም በሚታዩበት ሁኔታ ዘርፉ በለውጥ ላይ መገኘቱ ኢንቨስትመንቱ በጥሩ መሠረት ላይ የቆመና በቀላሉ የማይደነግጥ መሆኑን መሆኑን ያመለክታል::

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በቀጣይም በአፈጻጸሙ ለውጥ ሊያስመዝግብ እንደሚችል ባለፈው በጀት ዓመት የተከናወኑት ተግበራት ለቀጣዩ ሥራ ጥሩ መሠረት ሊሆኑ እንደሚችሉ መልካም ማሳያዎች አሉ:: ይህን አቅም፣ በዘርፉ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር የተገኘውን ውጤት ከመጠበቅ ባሻገር የላቀ እንዲሆን ለማድረግ አሁንም ጠንክሮ መሥራት ይገባል:: የአምራች ዘርፉን ከሚጠበቅበት ስፍራ ማድረስም ይህንኑ ይፈልጋል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You