![](https://press.et/wp-content/uploads/2019/06/ታተተተ-2-11-3.png)
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን አስፍቶ ለውጡን በጋራ እንምራ የሚል ጥሪ በሚያደርግበት እና የታሰሩት ተፈተው፣ የተሰደዱት ወደ አገር ገብተው፣ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም ለዲሞክራሲው ምህዳር መስፋት የሚያግዙ ተቋማትን የማደራጀትና የማጠናከር ስራ በሚሰራበት፤ በቀጣይም ስልጣን በህዝብ ምርጫ ብቻ ይደረጋል ተብሎ ሰፊ ዝግጅት በሚደረግበት በዚህ ወቅት ስልጣንን በጉልበት ለመያዝ በማሰብ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ እጅግ አሳዛኝ ነው።
ሰኔ 15 ቀን አመሻሽ ላይ በባህርዳር በተቃጣው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልላዊ መንግስት እና የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን ህይወት የቀጠፈ አረመኔያዊ ድርጊት ተፈጽሟል። ከፍተኛ አመራሮቹ ከስራ ሰዓት ውጪ በሆነው የእረፍት ጊዜያቸው ህዝብና መንግስትን ለማገልገል በቢሮ ውስጥ ስራ ላይ ባሉበት የራሴ ወገን በሚሉት አካል በጥይት ተደብድበው መገደላቸው በእጅጉ የሚቆጭና የሚሰቀጥጥ ክስተት ነው።
በአገራችን በተለያየ ጊዜያት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ነበሩ፤ ሆኖም ሙከራዎቹ ከሙከራነት በዘለለ ያመጡት ለውጥና ውጤት አልነበረም። አሁንም የተካሄደው ሙከራ በተመሳሳይ በህዝብና በመንግስት ጥረት ከሽፏል። ይሁን እንጂ አምስት መተኪያ የሌላቸውን ለኢትዮዽያ አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ሲያገለግሉ የነበሩ አመራሮች በግፍ ተገድለዋል። ይሄ በኢትዮዽያ ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ እጅግ አሳፋሪና አሳዘኝ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ነው። በመሆኑም በአንድ ድምጽ ሊወገዝ ይገባል።
አመራሮቹ ለአማራ ህዝብ ብሎም ለኢትዮዽያ አገራቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያለዕረፍት የሚሰሩትና የሚደክሙት በአገራችን የተጀመረው የለውጥ ሂደትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው በታሰበው ልክ ወደፊት እንዲሄድ፤ የህዝቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ነው። ሀገርን የሚያስተዳድር መንግስት በጉልበት ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ መንገድ በምርጫ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ለማስቻል ነው፤ ይህ ለውጥ በሀገሪቱ እንዲመጣ እና አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስም የክልሉ አመራሮች እና ጀነራሎቹ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱ ናቸው።
እነዚህ አመራሮች በሰሩት ስራ ሀገር ገብታበት ከነበረችበት ቀውስ ወጥታ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ባደረጉት አስተዋጽኦ ሊመሰገኑና ሊሸለሙ የሚገባቸው ነበሩ። ከጎናቸው በመሆን አለንላችሁ ሊባሉ ይገባም ነበር፤ ይሁን እንጂ ለልፋታቸው ለድካማቸው የተከፈላቸው የጥይት ናዳ መሆኑ ሲታሰብ በጣም ያማል፤ ያቆስላል። በተለይ ስልጣን በጉልበት በሀይል ለመያዝ በማሰብ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተቀናጀው በክልሉ ከፍተኛ አመራር አስተባባሪነት መሆኑ ደግሞ አረመኔያዊ ተግባሩን እጅግ የከበደ ያደርገዋል። ይሄ በየትኛው መንገድ በማንም የማይደገፍ እኩይ ተግባር ነው፡፡ ይህ የግለሰቦች ጥቃት ሳይሆን በክልሉ ህዝብ ላይ የተቃጣ የህዝቡንም ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው።
ስልጣን በዲሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ ድምጽ የሚያዝበትን ስርዓት እየተመቻቸ ህጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች እየተሻሻሉ፣ ተቋሟት እየተደራጁ ባሉበት በአሁኑ ወቅት በመፈንቅለ መንግስት በጉልበት ወደ ስልጣን ለመውጣት መሞከር በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ እብደት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። በመሆኑም በሁሉም ህዝብ ዘንድ በአንድ ድምጽ ሊወገዝ ይገባል። ይሄ እብደት ህዝብን ከህዝብ የሚያጫርስ ሀገርን የሚያፈራርስ እንጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ አይደለም። በመሆኑም መላው የሀገራችን ህዝቦች ድርጊቱን ሊቃወሙት እና ሊያወግዙት ይገባል ።
የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ ዜጎች ያለምንም ስጋትና ፍርሀት ወጥተው እንዲገቡ፤ መስራትና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ደግሞ የህግ የበላይነት መከበር አለበት። የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድም ኃላፊነት ያለበት መንግስት ነው። መንግስት ይሄንኑ አጠናክሮ መስራት ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ በጥፋት ድርጊቱ በመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ ተደራጅተው የነበሩትን ቡድኖች በጥንቃቄ በመለየትና ለፍትህ አካል በማቅረብ የእጃቸውን እንዲያገኙ ማድረግ አለበት።
መንግስት ህግን ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥም ጥፋተኞችን አጋልጦ በመስጠት ህዝቡ ከጸጥታ አካላትና ከመንግስት ጎን መቆም ይጠበቅበታል። ህዝብ መንግስትና የጸጥታ መዋቅሩ ከተባበሩ ጥፋተኞችን አድኖ መያዝ ከባድ አይሆንም። ማንኛውም ወንጀል ከህዝብ የተደበቀ አይደለም። ወንጀለኞችም የሚገኙት በህዝቡ ውስጥ ነው። ስለዚህ መላው የሃገራችን ህዝብ ጥፋተኞችን በማጋለጥና በመጠቆም በህግ ፊት ቀርበው የእጃቸውን እንዲያገኙ መተባበር አለበት። የክልሉ መንግስት አመራሮችም ከዚሁ ጎን ለጎን ለቀጣዩ የክልሉ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት መስራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011