በጃፓኗ ሆኬዶ በተሰኘችው የወደብ ከተማ ቤቶች እየተሰበሩ ዝርፊያ ይፈጸምባቸዋል።ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ የወንጀሎቹን ፈጻሚዎች በቀላሉ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡
ፖሊስ ወንጀሉን ቶሎ እንዳይደርስበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ወንጀሉን አዛውንቶች ላይፈጽሙት ይችላሉ በሚል ነበር፡፡
በመጨረሻም ሁነቶችን ለመከታተል የተተከሉ ካሜራዎችን ከተመለከተ በኋላ ዝርፊያውን አንድ አዛውንት ሲፈጽም ይመለከታል፡፡
የአንዱን አዛውንት እንቅስቃሴ ላይ ባደረገው ክትትል የ88፣ 70 እና 69 ዓመት እድሜ ያላቸው ጃፓናውያን አዛውንቶች ተደራጅተው ሲሰርቁ መቆየታቸውን ያረጋግጣል፡፡
እነዚህ አዛውንት ጃፓናውያን አንዱ የሚሰበሩ ቤቶችን በማጥናት ሲሰብር እና ሲሰርቅ፣ አንዱ ደግሞ የተሰረቁ ንብረቶችን በማጓጓዝ ሌላኛው ደግሞ ንብረቶቹን የሚገዛ ደንበኛ አፈላላጊ ሆነው እየሠሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ፖሊስ የአዛውንቶቹን ሙሉ የስርቆት ሰንሰለት ካጠና በኋላ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን ወንጀሉን እንደፈጸሙ አምነዋል ተብሏል፡፡
አዛውንቶቹ ስርቆቱን ለምን እንደፈጸሙ ሲጠየቁም ኑሮ ከብዷቸው ሕይወታቸውን ለማቆየት ብለው ወደ ስርቆት እንደገቡ ለፖሊስ ተናግረዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
የአዛውንት ሕዝብ ብዛት በበዛባት ጃፓን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጡረታ በወጡ አባቶች የሚፈጸሙ ስርቆት ወንጀሎች እየጨመሩ መምጣታቸው ተገልጿል፡፡
በጃፓን በየዓመቱ ከሚወለዱ ሕጻናት ይልቅ ጡረታ የሚወጡ አዛውንቶች ቁጥር ብልጫ አለው የተባለ ሲሆን ሀገሪቱ ዜጎቿ ጋብቻ እንዲመሠርቱ እና ልጆችን እንዲወልዱ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ዘርግታለች፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም