በባህላዊ ህክምና ለብዙዎች መፍትሄ የሆኑት ሎሬት

ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል የባህል ህክምና፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ቁጠባ፣ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት፣ ዘመን አቆጣጠር፣ ዕደጥበብና የእርቅ ሥርዓት ተጠቃሽ ናቸው። የዕለቱ ትኩረታችንም ለሀገር ግንባታ ጉልህ ሚና ካላቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል አንዱ በሆነው በባህል ህክምና ላይ ልናደርግ ወደናል፡፡

በሀገሪቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባህላዊ ሀኪሞች ስለመኖራቸው ይታመናል። ከእነዚህም መካከል አለሙ ተጨማሪ ምግብ ማቀነባበሪያ መሸጥ የግል ኢንተርፕራይዝ አንዱ ነው። ድርጅቱ ከተለያዩና ሀገር በቀል ከሆኑ የምግብ ቅመማቅመሞች የተቀነባበሩ መድሃኒቶችን ያመርታል። የምግብ ውጤቶችን መሠረት ያደረገው ይህ የባህል ህክምና ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላ ለበርካታ ህመሞች መድሃኒት መሆን ችሏል። በመከላከል ረገድም እንዲሁ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

ብርቱ በሆነ ምርምርና ጥናት እንዲሁም ጥረት የባህል ሀኪም የሆኑት የዕለቱ እንግዳችን በፈጠራ ሥራቸው የሎሬትነት ማዕረግ አግኝተዋል። ለማወቅ፣ ለመመራመርና መፍትሔ ለመሆን ያላቸው ውስጣዊ ተነሳሽነት ዛሬም ትኩስ ነው። የመድሃኒቱን ውጤት ለማግኘት 13 ዓመታትን የፈጀ ጥናትና ምርምር አድርገዋል። ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራ ለመግባትም እንዲሁ ሰባት ዓመታት ታግሰው ደጅ ጠንተዋል። በድምሩ ከሁለት አስርት ዓመታት ትግል በኋላ ዛሬ ውጤት ያገኙበትን የባህል መድሃኒት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ ችለዋል፡፡

ገና በልጅነት በውስጣቸው ይንቀለቀል የነበረውን ፍላጎት በትምህርት አጎልምሰው ዛሬ የባህል ሀኪም መሆን የቻሉት እንግዳችን፤ ከልጅነታቸው ጀምረው ለህክምና ዕውቀት ልባቸው ክፍት ነበር። ከልባቸው መከፈት ባለፈም በቤተሰብ እቅፍ ውስጥ እያሉ ጀምሮ ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሯቸው። ከቤተሰብ በተጨማሪም መምህር ሆነው ሲያገለግሉ ስለ ባህል ህክምና በሚገባቸው ልክ ለማወቅ፣ ለመረዳትና ለመመራመር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። አብዛኛውን ጊዜያቸውን ለንባብና ለምርምር በማዋል ከጎሬ እስከ ሰንዳፍ የባህል ህክምናን ዕውን ለማድረግ ሲታትሩ የኖሩት የዕለቱ እንግዳችን ሎሬት አለሙ መኮንን ይባላሉ። ከጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጀመረው የሎሬት አለሙ ትጋት መዳረሻውን ሰንዳፋ በማድረግ ፍሬ ማፍራት ጀም ሯል።

ትውልድና ዕድገት

ሎሬት አለሙ መኮንን ተወልደው ያደጉት ጥንታዊና ታሪካዊ በሆነችው ጎሬ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ተወልደው ባደጉበት ጎሬ ከተማ ላይ ተከታትለዋል። በጅማ መምህራን ትምህርት ኢንስቲትዩትም እንዲሁ የመምህርነት ሥልጠና ወስደው የመምህርነት ሙያን አግኝተዋል። ትምህርት ሚኒስቴር የሰጠውን ዕድል ተጠቅመው ላቦራቶሪ ቴክኒሻንነትንም አክለውበታል። በመምህርነት ዘመናቸው የኬሚስትሪ መምህር እና የላቦራቶሪ ባለሙያ በመሆን ላለፉት 28 ዓመታት ያገለገሉት ሎሬት አለሙ፤ የማስተማር ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት ጋምቤላ ቢሆንም በተማሩበት ትምህርት ጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም የማስተማር ዕድል ገጥሟቸው አስተምረዋል።

ጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበራቸውን ቆይታ በሙሉ ከመደበኛው የማስተማር ሥራቸው ጎን ለጎን ስለ ባህላዊ ህክምናና መድሃኒቶች ሲያጠኑ ኖረዋል። ስለባህላዊ ህክምና ያለመታከት ሲመራመሩ የቆዩት ሎሬት አለሙ በወቅቱ በርከት ያሉ መነሻ የሚሆኑ ፎርሙላዎችን አሰባስበዋል። ከጎሬ ወደ ሰንዳፋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዝውውር በሄዱበት ጊዜ ያሰባሰቧቸውን ፎርሙላች ይዘው በመጓዝ ከማስተማር ሥራቸው ጎን ለጎን ምርምርና ጥናታቸውን በማስቀጠል ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

መሠረት የጣለው የአባት ምክር

ከተማረና የህክምና ባለሙያ ከሆነ ቤተሰብ የተገኙት ሎሬት አለሙ፤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተምሮ የመለወጥ ውጥን ይዘው ነው ያደጉት። በተለይም ውስጣቸው የነበረውን ፍላጎት ማውጣት እንዲችሉ ወላጅ አባታቸው ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ወላጅ አባታቸውም የተለየ ቀረቤታ የነበራቸው በመሆኑ እንደጓደኛሞች ነበሩ። ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የወላጅ አባታቸውን ሥራ በቅርበት የመከታተል፣ የመጠየቅና የመረዳት አጋጣሚው የተፈጠረላቸው ሎሬት አለሙ፤ ወላጅ አባታቸው መድሃኒት ቤት መክፈት በመቻላቸው ነበር። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜያቸውን በመጠየቅ የሚያሳልፉት፡፡

በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በሀገሪቱ የጤና ተቀሟት ተደራሽ ባለመሆኑ የጤና ተቋማት፣ ክሊኒኮች በተለይም ፋርማሲዎች ተስፋፍተው እንደነበር ያስታወሱት ሎሬት አለሙ፤ በወቅቱ በመላው ሀገሪቷ የጤና ተቋማትን ለማዳረስ በሚል መንግሥት ፋርማሲ መክፈት ለሚፈልጉ ሀኪሞች ፈቃድ መስጠቱን አጫውተውናል። በወቅቱ የጤና ባለሙያ የነበሩት ወላጅ አባታቸው ዕድሉን ተጠቅመው ፋርማሲ መክፈት በመቻላቸው ህክምናን በቅርበት መረዳት አስችሏቸዋል። ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመላው ኢትዮጵያ ፋርማሲዎችና ክሊኒኮች የተስፋፉበት ነበር።

ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ መድሃኒቶችን በቅርብ እየተመለከቱ የማደግ አጋጣሚ የተፈጠረላቸው ሎሬት አለሙ፤ መድሃኒት ነክ ነገር ይስባቸው ጀመር። ስለመድሃኒት ከመረዳት ባለፈ ቀስ በቀስ ፍላጎት እያደረባቸው ሲመጣ ታውቋቸዋል። በመድሃኒት ቤት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራትን በሙሉ ጠንቅቀው የሚያውቁት ሎሬት አለሙ፤ መድሃኒት የመሥራት ፍላጎት እንዲኖራቸው ያደረገ አንድ አጋጣሚ የተፈጠረው በወላጅ አባታች መድሃኒት ቤት ውስጥ ነበር።

አጋጣሚውን መነሻ በማድረግ ታዲያ መድሃኒት የመሥራትና ህክምና ውስጥ መግባት ፍላጎት እንዳላቸው ለወላጅ አባታቸው አጫወቷቸው። ወላጅ አባታቸውም መድሃኒት የመሥራት ፍላጎት ካላቸው በዋናነት እጽዋትና ምግብ ላይ ትኩረት አድርገው ማጥናት እንደሚገባቸው አባታዊ ምክራቸውን ከሙያ ጋር በማስተሳሰር አስረድተዋቸዋል።

ከትምህርት የተገኘው ውጤት

‹‹የተማሩ ሰዎች የባህሪና የሥራ ለውጥ ማምጣት አለባቸው›› የሚሉት ሎሬት አለሙ፤ ትምህርት ሁለት መሠረታዊ ለውጦችን የሚያመጣ ስለመሆኑ በጽኑ ያምናሉ። አንደኛው የሰውዬውን ባህሪ የሚቀይር ሲሆን፤ ሁለተኛው የሥራ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ሰውዬው ተማረ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም በልጅነቱ ያለው ባህሪ እና ከተማረ በኋላ የሚኖረው ባህሪ የተለያዩ ናቸው። ለዚህም ነው በመማሬ ምክንያት በሕይወቴ የባህሪና የሥራ ለውጥ ማምጣት ችያለሁ ይላሉ።

ትምህርት በተለይም የባህሪ ለውጥ ለማምጣት በብዙ የሚያግዝ በመሆኑ ውስጣቸው ያለውን ዕውቀት አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ በር ከፍቶላቸዋል። በተለይም ይላሉ ‹‹በተለይም ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ያስተማሩኝ መምህራኖቼ ውስጤ ያለውን ዕውቀት እንዳወጣ አግዘውኛል። መምህር ተማሪዎች ውስጣቸው ያለውን ዕውቀት ማውጣት እንዲችሉ መንገድ የሚያሳይ ነው። ስለዚህ ውስጤ ያለውን ዕውቀት አውጥቼ መጠቀም እንድችል መምህራኖቼ በብዙ አግዘውኛል›› ያሉት ሎሬት አለሙ በትምህርት ቤት ከመምህራኖቻቸው ካገኙት ዕውቀት በተጨማሪ ከወላጅ አባታቸው ያኙት ምክር ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ያምናሉ፡፡

መነሻ ሃሳብ

ገና ተማሪ እያሉ ለዘመናዊ ህክምና ቅርብ ሆነው ያደጉት ሎሬት አለሙ፤ ሰዎች ከሚገጥማቸው ህመም ለመፈወስ ወላጅ አባታቸው ጋር በመምጣት የተለያዩ መድሃኒቶችን ገዝተው ሲጠቀሙ አስተውለዋል። ከትምህርት የሚተርፍ ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከወላጅ አባታቸው ጋር በመሆኑ መድሃኒት ቤት ውስጥ ብዙ ነገር አስተውለዋል። በዚህ ጊዜ መድሃኒት ማለት በአብዛኛው ፈዋሽ እንደሆነ ተረድተዋል። ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ያለማቋረጥ መድሃኒት ሲወስዱ ተመልክተዋል። ይህን ያስተዋሉት ሎሬት አለሙ፤ በወቅቱ ለምን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

ወደ መድሃኒት ቤት ከሚመጡ ደንበኞች መካከል አንደኛው የስኳር ታማሚ በመሆኑ ዕለት ዕለት ወደ መድሃኒት ቤት በመምጣት መርፌ ይወጋሉ። ይሄን ጊዜ ‹‹እገሌ ለምን አይድኑም›› የሚል ጥያቄ ያቀረቡት ሎሬት አለሙ፤ ወደ ፋርማሲው ከሚመጡ በርካታ ደንበኞች መካከል ቀልባቸውን የሳቡት እኚህ የስኳር ታማሚ ነበሩ። ሰውዬው የወላጅ አባታቸው ጓደኛ በመሆናቸው ጭምር ልባቸው ክፉኛ ተነክቷል። አባትም የስኳር ታማሚ እንደሆኑና በወቅቱ የነበረው የስኳር ህክምና ደግሞ የዕድሜ ልክ ህክምና እንደሆነ አስረድተዋቸዋል። ይህን የተረዱት ሎሬት አለሙ፤ የበለጠ በማዘን ለምን? እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎች ከአዕምሯቸው ጓዳ ሲርመሰመስ ተሰምቷቸዋል።

ስኳር ታማሚዎች መድሃኒቱን በሕይወት ዘመናቸው እስካሉ ድረስ የሚጠቀሙት እንደሆነና መድሃኒቱን ካቋረጡ ግን በሽታው የሚገድላቸው እንደሆነ ከወላጅ አባታቸው የተረዱት ሎሬት አለሙ፤ በልጅነት ትንሹ ልባቸው ክፉኛ በማዘን ግን ደግሞ መፍትሔ ለመፈለግ ወሰኑ። ኀዘናቸውን ያስተዋሉት ወላጅ አባታቸውም ሳይንስ እያደገ እንደሚሄድና ወደፊት የሚሻሻል መሆኑን፤ ዛሬ ያልተገኘው መድሃኒት ነገ እንደሚገኝ ሳይንስ፣ ምርምርና ጥናት አንድ ቦታ እንደማይቆም ሊያስረዷቸው ሞከሩ። ይህን ጊዜ አንዳች ተስፋ በውስጣቸው ሲያቆጠቁጥ ተሰማቸው። እናም ወደፊት የህክምና ሥራ በመስራት ለችግሮች መፍትሔ ለመሆን ለራሳቸው ቃል ገቡ። ቃላቸውን በተግባር ለማዋልም የወላጅ አባታቸውን ምክር በልባቸው ሰንቀው እጽዋትና ምግብ ላይ ትኩረት ለማድረግ ወስነዋል፡፡

መምህርነትና ምርምር

የወላጅ አባታቸውን ምክር በልባቸው ያኖሩት ሎሬት አለሙ፤ በትምህርት ጊዜያቸውም ሆነ በሥራ ሕይወታቸው ሁሉ ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች አሟጠው ተጠቅመዋል። በተለይም የመምህርነት ሙያቸው ለጥናትና ምርምር ትልቅ ድጋፍ የነበረው በመሆኑ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ሌት ተቀን በማንበብ፣ በመመራመር፣ በማጥናትና በመሞከር ውጤት እስኪያገኙ ድረስ ብዙ ለፍተው ወጥተውና ወርደው ውጤት አግኝተዋል።

ልባቸው የተነካበት የህክምና ሙያን ከወላጅ አባታቸው ባገኙት ምክር ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት መምህር እያሉ ነበር። ጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት ሎሬት አለሙ ከመደበኛው የመምህርነት ሥራቸው ጎን ለጎን ቤተመጽሃፍት እና ቤተሙከራ በመግባት ስለ ዕጽዋትና ስለ ምግብ የሚያስረዱ መጽሃፎችን ለይተው ማንበብና መመራመር ጀመሩ። በመጀመሪያው ንባብ ያገኙትና የሳባቸው ቅመማቅመም ነበር። የቅመማቅመም አይነቶችን እና ያላቸውን ጠቀሜታ በዝርዝር ማንበብ ቀጠሉ። ቅመማቅመም በብራዚል፣ በህንድ፣ በአሜሪካና በጀርመን እንዲሁም በሌሎች ሀገራት የተጠኑ በርካታ ጥናቶችን አግኝተው አንብበዋል። በተለይም በህንድና በብራዚል የተጠኑት ጥናቶች በርከት ያሉ ጉዳዮች ያነሱና ሳቢ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

እነዚህን ጥናቶች በሚያነቡበት ጊዜ ታዲያ የባህል ህክምናው የበለጠ የሳባቸው ሎሬት አለሙ፤ ለምግብ ማጣፈጫነት በቤት ውስጥ የምንጠቀማቸው ቅመማቅመሞች በርካታ ጥቅሞች እንዳላቸውና መድሃኒት መሆን እንደሚችሉ ተረድተዋል። ለዚህም ነው ጉዳዩን ጠበቅ አድርገው በመያዝ ሥራቸውን ቀጥለዋል። በወቅቱም ለቁጥር የበዙ ፎርሙላዎችን በማዘጋጀት ስለቅመማቅመሞች ጥቅም በብዙ ተረድተዋል፡፡

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሰንዳፋ ሁለተኛ ደረጃ ተዘዋውረው የመጡት ሎሬት አለሙ፤ ሰንዳፋ ተመድበው ሲያስተምሩና ቅመማቅመሞች ላይ የጀመሩትን ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሰንዳፋ ላይ እንደ ጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባይሆንም የተወሰኑ መጽሐፍቶችን አግኝተው ማንበብና መመራመራቸውን ቀጠሉ። የሰንዳፋ ቤተመጽሐፍት ብዙ አላስደሰታቸውም፤ ያም ቢሆን ታዲያ በውስጣቸው የሚንቀለቀለውን ሃሳብ ዳር ለማድረስ በየጊዜው አዲስ አበባ በመምጣት በየቤተመጽሐፍቱ ተዘዋውረው ማንበብና ስለ ቅመማቅመም ማጥናታቸውን መደበኛ ሥራቸው እስኪመስል ብዙ ጊዜ ሰጥተው ተከታትለዋል።

በተለይም ጥረታቸው ፍሬ እንዲያፈራ በብዙ የታተሩት ሎሬት አለሙ፤ የህንድ መጽሐፍትን በስፋት አገላብጠዋል። ለዚህም ምክንያታቸው ህንዶች በቅመማቅመም የታወቁ በመሆናቸው ነው። የተለያዩ መጽሐፍቶችን ከህንድ ኤምባሲ ማግኘት የቻሉት ሎሬት አለሙ፤ ጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆነው የጀመሩትን ፎርሙላ ሰንዳፋ ላይ ንባብ ጨምረው ማስቀጠልና የበለጠ ማዳበር ችለዋል። ገና በልጅነት በውስጣቸው የተጠነሰሰውን የህክምና ፍላጎትም ከዘመናዊ ህክምናው በበለጠ ወደ ባህላዊ ህክምና እንዲያዘነብሉ ሁኔታዎች ፈቅደውላቸዋል።

የመድሃኒት ግኝት

መምህር ከመሆናቸው ባለፈ የባህል ሀኪም የመሆን ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ በብዙ ሲያነቡ ሲመራመሩና የተለያዩ ፎርሙላዎችን ሲያዘጋጁ የኖሩት ሎሬት አለሙ፤ ትልቁ ትኩረታቸው ገና በልጅነት ውስጣቸውን ለነካው የስኳር ህመም መፍትሔ ማፈላለግ ነበር። ባደረጉት ምርምርና ንባብም ለስኳር ህመም ውጤት ማግኘታቸውን ይናገራሉ። ሰዎች በቤት ውስጥ ለምግብ ማጣፈጫነት የሚጠቀሟቸውን ቅመማቅመሞችን በመቀላቀል ከተለያዩ ህመሞች ለመፈወስ እንዲሁም ለመከላከል ትልቅ አቅም እንዳላቸው ባደረጉት ምርምር ተረድተዋል። በተለይም ለስኳር ህመምና ከሰውነት ውስጥ ዩሪክ አሲድን ለማጥፋት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ውጤት ማግኘት እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከቅመማቅመም ብቻ የተዘጋጁ ተጨማሪ ምግቦች በሚል ስያሜ ያዘጋጁት ምግብ ለተለያዩ ህመሞች መፍትሔ እየሆነ መምጣቱን ተጠቃሚዎች ምስክር ናቸው። እነዚህ መድሃኒትነት ያላቸው ተጨማሪ ምግቦች አሁን ላይ ማህበረሰቡ እየለመዳቸው መሆኑን ያነሱት ሎሬት አለሙ፤ በተለይም ከስኳር ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ህመሞች መፍትሄ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ተጨማሪ ምግብ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው መድሃኒቶችም ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትሉ ስለመሆናቸው ከምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ማረጋገጫ እንዲሁም ከአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ፓተንት አግኝተዋል።

ከተለያዩ ቅመማቅመሞች የተዘጋጁት መድሃኒትነት ያላቸው እነዚህ ምግቦች በተለይም ለስኳር ህመም መፍትሔ እየሆኑ ነው። ይህም ማለት ስኳሩን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻልም የስኳር ተጓዳኝ ህመሞችን ለማስወገድና የስኳሩ መጠን እንዲስተካከል ያደርጋል። በቤት ውስጥ ለምግብነት ከሚያገለግሉ ቅመማቅመሞች መካከል ፌጦ፣ ቅሩንፉድ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ አብሽና ቀረፋ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ቅመሞቹ አንድ ላይ ተዋህደው በምግብ መልክ የተዘጋጁና ህመም የሚያስወግዱ ውህዶች ናቸው። እነዚህ ውህዶችን ወደ ገበያ ለማውጣት ፈቃድ ያገኙት ተጨማሪ ምግብ በሚል ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ተጨማሪ ምግብ በሚል ማህበረሰቡ አውቋቸው እየተጠቀመባቸው ነው። ይህ መድሃኒትነትን በውስጡ የያዘው ተጨማሪ ምግብ ሚልፋን አንድ፣ ሚልፋን ሁለትና ጨይጅን በመባል በሶስት ይከፈላል። ሶስቱም የተለያየ አገልግሎት ሲኖራቸው ሚልፋን አንድ፤ ለስኳር ተጓዳኝ ህመሞች፣ ለኩላሊትና ለጉበት ችግሮች፣ ለአንጀት ውስጥ ትላትሎች፣ ለነርቭ ችግር፣ የካንሰር ሴሎችን መራባት ለመቀነስ፣ የሽንት ፊኛ ችግር፣ ለኪንታሮት፣ ለሳይነስና አስም፣ ለማድያትና ለጨጓራ ባክቴሪያ መድሃኒትነት የሚያገለግል ነው።

ሚልፋን ሁለት፤ ስብን ለማስወገድና ክብደትን ለመቀነስ እንዲሁም ለኮሎስትሮልና ለደም ግፊት ጠቃሚ ሲሆን፤ ጨይጂን የሚል መጠሪያ ያለው ለሪህ /ዩሪክ አሲድ/ ለአርትራይተስ፣ ለጉልበትና እግር እብጠት፣ እግር እጅና ሰውነት ውስጥ ለሚያቃጥል፣ ለወገብ ህመምና ለሌሎችም በመድሃኒትነት የሚያገለግል ተጨማሪ ምግብ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማህበረሰቡ ይዘው የቀረቡት የምርምር ውጤት ከላይ ተዘረዘሩትን ህመሞች ማስወደግ ችሏል። ነገር ግን መድሃኒቶቹ ሲወሰዱ ኪሎ በጣም ያወርድ ነበርና ይህን ለማስተካከል ተጨማሪ ጥናት አድርገዋል። መድሃኒቱን የተጠቀሙ ሰዎች ከህመማቸው መፈወስ ቢችሉም ክብደታቸው በጣም ቀንሷል። በዚህ ምክንያት ተጨማሪ ምርምር ያስፈለጋቸው ሎሬት አለሙ፤ ተጨማሪ ምርምርና ጥናት በማድረግ ከመድሃኒት ውስጥ ክብደትን ሊያወርዱ የሚችሉ ቅመሞችን በመለየት ከውስጥ አውጥተዋል። በመሆኑም መድሃኒቱ ክብደትን ሳይቀንስ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አስችሏል። ወደ ማህበረሰቡ ከማምጣቸው አስቀድመው መድሃኒቱን በራሳቸውና በዙሪያቸው ባሉ ወዳጆቻቸው የሞከሩት ሎሬት አለሙ፤ ያደረጉት ሙከራ ሁሉ ውጤታማ ሲሆን አስተውለዋል። በዚህም የበለጠ በመበረታታት ብዙ ጥናትና ምርምር በማድረግ ቅመማቅመሞችን አዋህደው ለመድሃኒትነት አውለዋል፡፡

ለስኳር ህመም ትልቅ ትኩረት ሰጥተው የሚያጠኑት ሎሬት አለሙ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከሩት ባህላዊ መድሃኒት ለስኳር ህመም ነበር። ስኳር ታማሚ ለነበረ አንድ ሰው የሰጡት መድሃኒት ስኳሩን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ባይችልም ከስኳር ጋር ተያያዥ የሆኑ ህመሞችን ሊያጠፋለት ችሏል። ከፍ ዝቅ እያለ የነበረው የስኳሩ መጠንም እንዲሁ መረጋጋትና መስተካከል ችሏል። ይሄኔ ሞራል ያገኙት ሎሬት አለሙ፤ በርትተው በመሥራት የቀጠሉት ከዛን ጊዜ ጀምሮ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ተለያዩ ቅመሞችን በማቀላቀል ለተለያዩ ህመሞች መድሃኒት መሥራቱን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ለመድሃኒትነት ብለው የሚቀላቅሉት ቅመማቅመሞችም በዓለም ደረጃ የሚታወቁና የተመዘገቡ በመሆናቸው ጉዳት የላቸውም። ‹‹ቅመሞቹ ሲቀላቀሉ የማዳን አቅማቸው ከፍ ይላል›› የሚሉት ሎሬት አለሙ ባህላዊ ህክምናውን ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማስተሳሰር ይሠራሉ። ይህም ማለት ደንበኞቻቸው ከሚጠቀሙት ባህላዊ መድሃኒት በተጨማሪ ዘመናዊ ህክምናው ተከታትለው በየሶስት ወሩ ውጤት እንዲያመጡ ያደርጋሉ። በተለይም የስኳር ታማሚዎች ከባህላዊ መድሃኒቱ ጎን ለጎን በዘመናዊ ህክምና ስኳሩ ያለበትን ደረጃ በየጊዜው እንዲያቀርቡ ይደረጋል። በዚህም አበረታች ውጤት አግኝተዋል። ደንበኞችም ጤናቸው እየተሻሻለ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

የባህል ህክምናን ለማዘመን

የማህበረሰብን ጤና ለመጠበቅ ባህላዊ ህክምና ጉልህ ድርሻ አለው የሚሉት ሎሬት አለሙ፤ ባህላዊ ዕውቀቶች ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር ተሳስረው መሄድ እንዳለባቸውና ሊሰራባቸው የግድ እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ። ሀገር በቀል ዕውቀት የሀገራዊ ችግር መፍቻ ቁልፍ መሆኑን በማመን የፈጠራ ሥራዎች መበረታታት እንዳለባቸው ሲያስረዱ፤ መንግሥት አሁን ላይ ለፈጠራ ሥራ የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽ ነው።

የፈጠራ ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸውን 70 ካሬ ሜትር ስፋ ያለውን ቦታ ከመንግሥት እንዳገኙ የገለጹት ሎሬት አለሙ፤ በአሁኑ ወቅት መድሃኒትነት ያለውን ተጨማሪ ምግብ በማምረት ማህበረሰቡጋ እየደረሱ ነው። ይሁንና አሁን ላይ የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ሥራውን የማስፋት ዕቅድ አላቸው። በመሆኑም ባህላዊ ህከምናውን ማስፋት የግድ እየሆነ መጥቷል። በተለይም የመድሃኒቶቹን አመራረት ዘመናዊ ለማድረግ የቦታ ጥያቄ አቅርበዋል። ወደፊት የቦታ ጥያቄያቸው ከተመለሰ መድሃኒትነት ያላቸውን ቅመማቅመሞች መፍጫና ትልቅ አቅም ያለው መቀላቀያ ዘመናዊ ማሽን በመትከል በስፋት የማምረትና ህክምናውን የማዘመን ዕቅድ አላቸው፡፡

ባህላዊ ህክምናውን በማዘመን በቀጣይ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉት ሎሬት አለሙ፤ የምርምር ሥራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የመምህር ደመወዝ እንደነበር አስታውሰው፤ ከመነሻ ካፒታል የበለጠ ለሀገር በቀል ዕውቀትና ለባህላዊ ህክምና ከፍተኛ ተነሳሽነትና ውስጣዊ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ህክምናውን ለማዘመን ካላቸው ዕውቀት፣ ልምድና ተነሳሽነት በተጨማሪ መነሻ ካፒታል ጭምር ያላቸው በመሆኑ ባህላዊ ህክምናውን በማዘመን ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደርጉት ትግል የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ውጤት

በስኳር ህመምና በዩሪክ አሲድ ውጤታማ መሆን እንደቻሉ የሚናገሩት ሎሬት አለሙ፤ መድሃኒቱን በትክክል የሚጠቀሙ ሰዎች ውጤት አግኝተዋል። በየሶስት ወሩ ክትትል አድርገው የሚያመጡት ውጤትም ጤናቸው እየተሻሻለ መሆኑን ያሳያል። አብዛኛው ሰው በተለይም ዩሪክ አሲድ ከውስጡ መጥፋት ችሏል። ስኳሩም በተመሳሳይ ሙሉ ለሙሉ መዳን ባይቻልም ለስኳር የሚወስዱትን የመድሃኒት መጠን መቀነስ ችለዋል። በአጠቃላይ እንደ ሰዎቹ ሁኔታ ለመዳን የሚወስድባቸው ጊዜ መርዘምና ማጠር ካልሆነ በስተቀር በአብዘኞቹ መድሃኒቶች ውጤታማ ናቸው፡፡

በብርቱ ልፋት የተገኘ ማዕረግ

የፈጠራ ባለቤት ሎሬት አለሙ መኮንን ሎሬት የሚለውን መጠሪያ ያገኙት ከአቢሲኒያ የሽልማት ድርጅት ነው። አቢሲኒያ የሽልማት ድርጅቱ በየዓመቱ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ትጉሃንን የሚሸልም ድርጅት ነው። ድርጅቱ በ2011 ዓ.ም ለትጉሃን የፈጠራ ሰዎችና አምራች ኢንዱስትሪዎች ዕውቅናና ሽልማት በሰጠበት ወቅት እርሳቸው በሠሯቸው የፈጠራ ሥራ የሎሬትነት ማዕረግ አግኝተዋል።

የሎሬትነት ማዕረግ ያገኙት ሎሬት አለሙ፤ በወቅቱ ብዙ ምርምርና ጥናት በማድረግ ያዘጋጁት መድሃኒትነት ያለው ተጨማሪ ምግብ ሰዎች ተጠቅመውት ውጤት ማምጣት መቻሉ ተረጋግጧል። መድሃኒቶቹም ለተለያዩ ህመሞች መፍትሔ መሆን የሚችሉ ተጨማሪ ምግቦች በመሆናቸው ጤናማ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንጻር ያለው አበርክቶ፤ እንዲሁም በከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ወቅስጥ የሚገቡ መድሃኒቶችን በመተካት ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተመስክሮለታል፡፡

መልዕክት

ሀገር በቀል ዕውቀቶች ሀገራዊ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ጉልህ ሚና እንዳላቸው ይታመናል። የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያም የብዙ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ባለጸጋ ናት። ይሁንና እነዚህ ለቁጥር የበዙ ሀገር በቀል ዕውቀቶች የተረሱ ቢመስሉም ኢትዮጵያውያን የሚያጋጥማቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ሲፈቱበት ኖረዋል። አሁንም ለችግሮች ሁሉ ዘላቂ መፍትሔ መሆናቸው ይታመናል።

‹‹በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን፤ ይህም የፈጠራ ሥራ የሚሠሩትን እጅግ የሚያበረታታ ነው›› ያሉት ሎሬት አለሙ፤ አሁን ላይ ለሀገር በቀል ዕውቀት የተሰጠው ትኩረት ከዚህ ቀደም ያሳለፉኩትን ህመም አክሞልኛል። በማለት በተለይም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ተነሳሽነት በተቀመጠው የፖሊሲ አቅጣጫ ‹‹ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለሀገር ኢኮኖሚ›› በሚል ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት ተሰጥቶ ባህላዊ ህክምናው በጤና ሚኒስቴር እውቅና መሰጠቱ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው›› በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሀገር በቀል እውቀቶች ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚያግዙ በመሆናቸው ማህበረሰቡ መድሃኒቶቹን በቀላሉ አግኝቶ ጤናውን እንዲጠብቅ ይረዳዋል። በተለይም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድሃኒትና መድሃኒት ነክ የሆኑ ምርቶችን ሀገር በቀል በሆኑ ምርቶች በመተካት እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራና በኤክስፖርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የኛም መልዕክት ነው፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም

Recommended For You