ኢትዮጵያ ሁሌም ከሶማሊያ ወንድም ሕዝብ ጎን ሆና ትቀጥላለች!

አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ መተባበር፣ መደጋገፍ፣ በጋራ አብሮ ከፍ የማለትና የመበልጸግ፣… የኢትዮጵያ የዘመናት የማይዋዥቅ የውጪ ዲፕሎማሲ መርህ ሆኖ የዘለቀ ነው። ይሄ አቋሟ ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ ከባለሁለት እስከ ባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብርና ግንኙነት ውስጥ ሲንጸባረቅም፤ በውጤት ታጅቦም ዘልቋል፡፡

በተለይ በጋራ ተባብሮና አቅምን ደምሮ ከመሥራት እና የጋራ ሰላምን ብሎም ልማትን እውን ከማድረግ አኳያ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ በቀጣናው ብሎም በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይተካ ሚናዋን ተወጥታለች። እየተወጣችም ትገኛለች። ለአብነት፣ ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ስምሪቶች ስኬታማ ተግባር ፈጽማለች፡፡

በዚህም በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በሶማሊያ እና በሌሎችም ሀገራት አህጉራዊም፣ ዓለምአቀፋዊም ተልዕኮዎችን በብቃት ተወጥታለች። በተለይ በሶማሊያ፣ በአሚሶም ጥላ ስርም ሆነ በራሷ አቅም ያበረከተችው ሚና ተኪ የሌለው ነው። በተለይ የሶማሊያ ሕዝብ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሰላምና መረጋጋት ርቆት፤ መንግሥት አልባም ሆኖ በቆየባቸው ዓመታት፤ ከዚህ ችግሩ ይወጣ ዘንድ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ መስዋዕትነትን ከፍላለች፡፡

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት፣ ለሶማሊያም አንድነትና ሉዓላዊነት ሳትታክት ሠርታለች። መንግሥት አልባዋን ሶማሊያ ባለ መንግሥት፣ ሰላም የራቀውንም ሶማሊያ ሕዝብ የተረጋጋ ሰላም ባለቤት እንዲሆኑ አድርጋለች። ለዚህም አንድም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ (አሚሶም) ማዕቀፍ ውስጥ ሆና፤ በሌላ በኩል በራሷ አቅም ታግዛ ወታደሮቿን በማሰማራት ለሶማሊያውያን ሰላም እና ለሶማሊያ መረጋጋት የደም እና ሕይወት መስዋዕትነት ውድ ዋጋን ከፍላለች፡፡

ዛሬም በአንድ በኩል በጎሳ ግጭት፣ በሌላ በኩል በሽብር ቡድኖች እየታመሰች ለምትገኘው ሶማሊያ፤ ኢትዮጵያ ይሄው አጋርቷን እየገለጸች ዘልቃለች። ከሶማሊያውያን ወንድም ሕዝቦች ጎን ቆማ አለኝታነቷንና አጋርነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች። ይሄ ደግሞ አንድም ለሶማሊያ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ካላት ከፍ ያለ መሻት የመነጨ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በቀጣናው ከፍ ያለ የሰላም፣ የልማትና የትብብር ዓውድ ተፈጥሮ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሀብቶቻቸውን በጋራ አሰባስበው በጋር እንዲበለጽጉ እያደረገች ያለው ተግባር መገለጫ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ አቅምን አሰባስቦና ሀብትን አቀናጅቶ በጋራ ሠርቶ ለመበልጸግ እየሄደችበት ባለው መርህ፣ የቀጣናውን መረጋጋትና መልማት የማይሹ ኃይሎች አጥብቀው ይቃወሙታል። ከመቃወም አልፈውም ዕቅድና አካሄዷን ለማምከን የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ለሃሳባቸው ተገዢ የሆኑ መንግሥታትንም ለዓላማቸው ማስፈጸሚያነት ይጠቀማሉ፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቀጣናውን አቅም አቀናጅቶ የመልማትና የመበልጸግ መርሆዋን ለማቅናት፤ የዘላቂና ያልተቆራረጠ አስተማማኝ የባህር በር ተደራሽነቷንም እውን ለማድረግ በሕግም ሆነ በታሪካዊ ዳራም መብቶቿ ታግዛ ባቀረበችው መሠረት ከሶማሌ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች። ይሄ መልካም እና ለቀጣናው ሰላምና ልማት ጥሩ ዕድል ሆኖ ሳለ፤ በሶማሊያ መንግሥት በኩል የተነሳው ተቃውሞ ግን በእጅጉ ከብሔራዊ ጥቅም ባፈነገጠና ለውጪ ኃይሎች በተለይም ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጥቅምና ፍላጎት የተገዛ ነው፡፡

ለዚህም ነው የሶማሊያ መንግሥት የሕዝቡን ብሎም የቀጣናውን ጥቅምና ፍላጎት ከሚያስጠብቅ እሳቤ ይልቅ፣ ተግባሩን የሶማሊያን ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚጋፋ አስመስሎ የተሰጠውን ሃሳብ ደጋግሞ ሲያነብና ሲስተጋባ የሚታየው። ይሁን እንጂ ይሄ የሶማሊያ ባለሥልጣናትን ከሀገር ይልቅ ለሌሎች ጥቅምና ፍላጎት መጠለፍ የታየበት መግለጫና ንግግር፤ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህም ሆነ፣ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ወንድም ሕዝብ የምታደርገውን አጋርነት የሚያስቆም ያልሆነው። ከሰሞኑ ኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግሥት መሠረተ ቢስ ውንጀላ በተቃራኒ ለሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ሕዝቦች ሰላምና መረጋጋት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ዋጋ እየከፈለች ቆይታለች። ይሄን እውነት በገፋ መልኩ የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኃላፊነት የጎደላቸው መግለጫዎችን ኢትዮጵያ ላይ ማውጣታቸው ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም፣ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ላይ እየሰነዘሩት ያለውን መሠረተ ቢስ ውንጀላ እየተከታተለ ነው።

ይሁን እንጂ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ያላቸውን የደም እና የባህል ትስስር የምታስቀድመው ኢትዮጵያ፤ ለሶማሊያ መንግሥት መሠረተ ቢስ ክስ ቦታ የማትሰጥ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የስጋት ቀጣና በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ያለው ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ እና የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በአካባቢው ሰላም ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ስለምትረዳ ጉዳዩን በትዕግሥት ይዛዋለች። በትኩረትም እየተከታተለችው ነው” ብሏል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ባላት ጽኑ አቋም በቀጣናው ግጭት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን መከላከሏን የምትቀጥል ሲሆን፤ በዚህም ቀጣናዊ ሰላምን ብሎም ልማትን እውን ከማድረግ አኳያ ከምትሠራው ሥራ ባሻገር፣ የሶማሊያ ሕዝብ ከዚህ ሰላምም ሆነ ልማት ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ኢትዮጵያ ወደፊትም ከሶማሊያ ወንድም ሕዝብ ጎን ሆና ትቀጥላለች!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 /2016 ዓ.ም

Recommended For You