ክለቦችን ከፋይናንስ ቀውስ ይታደጋል የተባለው አዲስ መመሪያ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አክሲዮን ማኅበር የተጫዋቾች ዝውውርን እና የደመወዝ ክፍያ አስተዳደርን በሕግና ሥርዓት ለመምራት ደንብና መመሪያ አውጥቶ ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ከጀመረ ሰንብተል፡፡ በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች ለተጫዋቾች ዝውውርና ደመወዝ የሚያወጡት ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑና እንደ ክለብ የመቀጠል ሕልውናቸው ላይ አደጋ በመደቀኑ አሳሪ ሕግ ለማውጣት መገደዱንም ሲያስረዳ ቆይቷል፡፡

የክለቦች አስተዳደር፣ የመዋቅርና የፋይናንስ ሁኔታቸው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስጠንቶ በተቀመጠው የባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ መሠረት ክለቦች እንዲሻሻሉ ሲሠራም ከርሟል፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ ትልቅ የክለቦች መፍረስ ስጋት በመሆኑ የተጫዋቾች ዝውውርና የደመወዝ ክፍያን በሕግና መመሪያ ለመምራት ወደ ተግባር መግባቱም ይታወቃል፡፡

የክለቦች ዝውውር እና የደመወዝ ክፍያ አስተዳደር መመሪያን አውጥቶ ለመተግበር ብዙ ርቀቶችን እንደተጓዘና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በአተገባበሩ ዙሪያ ሰሞኑን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት አስታውቋል፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ ሊግ ካምፓኒው የተቋቋመው ክለቦችን ካሉበት ሁኔታ ለማሻሻል እና ለማሳደግ በመሆኑ ለዚህ የሚሆኑ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የክለብ አስተዳደር፣ ስያሜ (ብራንዲግ)፣ ስፖንሰርሺፕ ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለአሠልጣኞች እና ለዳኞች ከአውሮፓ በመጡ ታዋቂ ባለሙያዎች ሥልጠናዎችን በመስጠት ክለቦች ካሉበት ሁኔታ እንዲወጡና እንዲጠናከሩ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ክለቦች የሚገኙበትን ሁኔታ ለመመልከት የቦርድ አባላት 16ቱንም ክለቦች እንደጎበኙ አስታውሰው፣ የአንዳንድ ክለቦች አደረጃጀት የፕሪሚየር ሊግ ይቅርና የአንድ ሰፈር ክለብ መሆን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራውን ክለቦችን በአስተዳደር፣ መዋቅርና በፋይናንስ የሚገኙበትን ደረጃ ሰፊ ጥናት አድርጎ ምን መደረግ እንደሚኖርበት ምክረ ሃሳብ መቅረቡን የጠቆሙት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ጥናቱም ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቦ እንዲተገበር ይሁንታን ማግኘት ችሎ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ እንደ መቶ አለቃ ፍቃደ ማብራሪያ፣ ለሚመለከተውና ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቦ በጥናት እንደ ችግር የተለየው የፋይናንስ አስተዳደር ነው፡፡ ክለቦቹ ካሉበት ሁኔታ አንጻር የሚያወጡት ወጪ ከአቅማቸው በላይ እና አወጣጡም ሥርዓት የሌለው ነው፡፡ ክለቦች በሰኔና ሐምሌ በዝውውር ገበያው ላይ ተወዳዳሪ ሆነው ግን ጥቅምትና ኅዳር ላይ ደመወዝ የማይከፍሉበት ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ በዚህም መሠረት ጥናቱ ለጠቅላላ ጉባኤ ከቀረበ በኋላ ቦርዱ ኮሚቴ አቋቁሞ ተጨማሪ ጥናት ተደርጋል፡፡

በጥናቱ ላይ በተደረገው ውይይት መሠረትም አንድ ክለብ በፋይናንስ ሕጉ መሠረት በዓመት ከፍተኛ 57 ሚሊዮን 750 ሺ ብር እንዲሁም ዝቅተኛው 18 ሚለዮን ብር እንዲያወጣ የተወሰነ ሲሆን አተገባበሩ በሁሉም ክለቦች የሚለያይ ይሆናል፡፡ ይህም ኮንትራት ያላቸው ተጫዋቾች በኮንትራታቸው መሠረት የሚፈጸምና ከክለቦች ጋር ውይይት ተደርጎ ከፀደቀ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተመርቶ ከታየ በኋላ የዲሲፕሊን ሕግ መሆን ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ በመመሪያው የተጠቀሱት ሕጎች ቢጣሱ ክለቦች ይቀጣሉ፡፡ በዚህ ሕግና መመሪያ የማውጣት ሂደት ሁሉም አጨብጭቦ የተቀበሉ ቢሆንም የሚሰሙ ጭምጭምታዎች መኖራቸው ግን አልቀረም፡፡ እነዚህ እውነት ሆኖ ከተገኙ “እርምጃ እንወስዳለን ካለበለዚያ ሊጉ ይፈርሳልም” ሲሉ መቶ አለቃ ፍቃደ አሳስበዋል፡፡ በተጫዋቾች ዝውውርና የደመወዝ አከፋፈል ላይ የወጣውን ደንብና መመሪያ የጣሰው አካል ላይ የቅጣት እርምጃ እንደሚወሰድም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በበኩላቸው፣ መመሪያው ወጥቶ 16ቱ ክለቦች ለመፈጸም ፈርመው ከውልና ማስረጃ በመጡ ባለሙያዎች መረጋገጡን ይናገራሉ። የሕግ ጥሰትን የሚፈጽሙ አካላትን ለመለየትና እርምጃ ለመውሰድ ከፋይናንስ፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከፀረ ሙስና እና ከፋይናንስ ኢንተለጀንስ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ይጠቁማሉ። በክፍያ ሥርዓቱ ቼክ መስጠትና ቅድመ ክፍያ የማይቻል ሲሆን ደመወዝ በአግባቡ መከፈል ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ፀድቆ ወደ ትግበራ የገባው የእግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያ መመሪያን በጥብቅ እየተከታተሉ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የተጫዋቾች ዝውውር ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ የፌዴሬሽኑ የክለብ ፍቃድ አሰጣጥ ክፍል፣ ክለቦች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን እንዲያሟሉ ሲደረግ ቆይቷል። ካፍ በዘረጋው አሠራር መሠረት በኦንላይን ሥርዓት እየተመዘገቡ በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አዲስ አሠራር እየተፈጠረ መሆኑንም ያስረዳሉ። የወጡት ደንብና መመሪያዎች መተግበር እንደሚገባቸው የእግር ፌዴሬሽኑ እምነት ነው። የፀደቀውን መመሪያ አብዛኞቹ ክለቦች የተቀበሉና ብዙዎቹ የክለብ ቦርድ አባላት የመንግሥት ኃላፊዎች ስለሆኑ በተዘዋዋሪ መንግሥትም እንደተቀበለ ይናገራሉ። መመሪያውን የመጣስ ጉዳይ ካለ ተያይዞ የሚመጣ ጥያቄ እንደሚኖር እንዲሁም ተጨዋች ሲፈርም የኢንሹራንስ፣ የጤና ሰርተፊኬት፣ መልቀቂያ፣ የልደት ሰርተፍኬት እና የሕይወት መድን ማቅረብ ግዴታ መሆኑንም ያስረዳሉ።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You