‹‹ስለ ልቤ ዝም አልልም››

ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል። ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።

ከቤት የወጣችው ማለዳ ወፍ ሳይንጫጫ ነው። ዛሬ ሌሊቱን ሙሉ ሲያስጨንቃት ላደረችበት ስጋት መልስ ማግኘት አለባት። ውርጩ፣ ዝናቡ፣ ቆፈኑ ያሳሰባት አይመስልም። ከሰፈሯ ርቃ ልትሄድ መንገድ ጀምራለች። ቦርሳዋን ጠበቅ አድርጋ ከእግሮቿ ነጠቅ እያለች ተራመደች። ከታክሲው ገብታ የእጅ ስልኳን ከወሸቀችበት ጉያዋ ስታወጣ ሰዓቷ ከንጋቱ አስራ ሁለት ከሰላሳ ይላል።

ብርሃኔ ካለችበት ስትወርድ ሌላ ታክሲ ትይዛለች። ጊዜውን እያሰላች በሀሳብ ነጎደች። ከአውቶቡስ ተራ ቦሌ ለመድረስ ቅርብ መንገድ አትጓዝም። ውስጧን አበርትታ የሚሆነውን ጠበቀች። ጥቂት ከታገሰች ካሰበችው እንደምትደርስ ታውቃለች። የመንገዱን መጋመስ ስታውቅ ብዙ አልቸኮለችም።

ከቆይታ በኋላ ከምትሻው ሐኪም ደርሳ የሚላትን ትሰማለች። ይህን ስታስብ መከረኛ ልቧ የተለመደ ድምታዋ ተሰማ። እንደምንም አባብላት ለመረጋጋት ሞከረች። ደረቷን ደግፋ ትንፋሽዋን ስታዳምጥ አሁንም ልቧ እየሮጠች፣ እየፈጠነች ነበር። ከስጋቷ መለስ ብላ በጎውን ለማሰብ ሞከረች። ይሄኔ ሲያስጨንቃት የቆየው ስሜት ገለል ሲል ተሰማት።

ዓመታትን ወደኋላ

ገና በጠዋቱ አባወራቸውን በሞት ያጡት ወይዘሮ በቤታቸው ከባድ ፈተና ወድቋል። የሰውዬው ደንገቴ ህልፈት ወዳጅ ዘመዱን አስደንግጧል። ለእሳቸው ግን ሀዘኑ ከሌሎች ሁሉ የተለየ ነው። ገና በወጉ ያልቆመ ጎጆ፣ ነፍስ ያላወቁ ልጆች፣ ብቸኝነትና አዲስ ሕይወት የእሳቸው ቀጣይ ፈተና ሆኗል።

ወይዘሮዋ በሆዳቸው ያለው ሽል ሲገላበጥ ሆድ ብሶ ይጨንቃቸዋል። ነገ ምኑን ከምን እንደሚያደርጉት ሲያስቡ በትኩስ ዕንባ ይታጠባሉ። ለሆድ እንጂ ለሥራ ያልደረሱት ትንንሽ ልጆች የአባታቸውን ሞት ያወቁ አይመስልም። ዛሬም እንደ ትናንቱ ከሜዳ ከማጀቱ እየሮጡ ይሳሳቃሉ።

የሀዘን ቀናት አልፈው የእንግዶች ቁጥር ሲቀነስ ጎጆው ጭር ማለት ያዘ። ውሎ አድሮ የጠያቂ ወዳጅ ዘመድ እግሮች ቀነሱ። ይሄኔ ወይዘሮዋና ሁለት ልጆቻቸው በብቸኝነት ተዋጡ። እማዋራዋ የሕፃናቱ ፈገግታ እንደ ወላጅ እናት ፊታቸውን አላፈካም። የልጆቻቸው ልጅነት ቢያሳስባቸው መተከዝ፣ አንገት መድፋት ያዙ።

ቀን መሽቶ ነጋ፣ ሳምንታት በወራት ተተኩ። አዲሱ ጨቅላ ጎጆውን ሲቀላቀል ችግር ፈተናው በብቸኛዋ ወይዘሮ ትከሻ መውደቅ ጀመረ። አሁን የቁርጥ ቀን ሊመጣ ማንነት ሊፈተን ነው። ሴትየዋ እጅ አልሰጡም። ቤት ያፈራውን፣ ጓሮ የሰጠውን በረከት ለልጆቻቸው መቃማስ፣ ማጉረስ አላቃታቸውም።

ይህን ሁሉ በቅርበት የሚያዩት ልጆች የእናታቸው ጥንካሬ ስለእነሱ መሆኑ ይገባቸው ጀምሯል። ሁሉም ስለነገ እያሰቡ ቀናትን ማስላት ያዙ። ከፍ ሲሉ የሚያደርጉትን፣ እድሜያቸው ሲደርስ የሚያግዙትን እያሰቡ እቅዳቸውን ተለሙ። እንደዋዛ ጥቂት ዓመታት ሳብ ማለታቸው አልቀረም።

ሁለተኛዋ ልጅ

ብርሃኔ ለቤቱ ብቸኛዋ ሴት ነች። ነፍስ ማወቅ ስትይዝ አንስቶ አባቷ ስለመሞታቸው ሰትሰማ አድጋለች። ከዚህ ውጭ ስለእሳቸው አንዳች ትውስታ የላትም። ዓይኗን ስትገልጥ ጀምሮ የምታውቀው እናቷን ነውና ሌላ ዓለም አታወቅም። ለእሷ ደግሞ የእሳቸው መኖር ትርጉሙ ይለያል። ሁሌም በመኖራቸው ተስፋዋ ይፈካል። ስለሳቸው ታስባለች፣ ትሰስታለች።

ብርሃኔና ባልንጀሮቿ ከእንሰት ተክሎች መሀል ሲዘሉ ይውላሉ። አንዳንዴ በጨዋታቸው መሀል የሚያነሱት ጉዳይ የልጅ ጨዋታ አይመስልም። ነገራቸው ሁሉ የሩቅ ሀገር ወሬ፣ የከተሜዎች ጉዳይ ነው። ከሌሎች ደግሞ የብርሃኔ ትኩረት ለየት ይላል። እሷ ስለሰዎቹ ስትሰማ አርቃ ታስባለች። እነሱን መሆን ትመኛለች።

የገጠሯ ልጅ የከተሜዎቹ ኑሮ፣ ሁሌም አምሮ ተውቦ ይታያታል። ይህ እውነት የእናቷንና የቤተሰቡን ሕይወት እንደሚለውጥ ታምናለች። ቀዬ መንደሯን ለቆ መሄድ ዕቅድ ሀሳቧ ነው። ይህን ለማሳካት ዕንቅልፍ ካጣች ቆይታለች።

ብርሃኔ ዕድሜዋ ከፍ ማለት ሲይዝ ትምህርት ቤት ገባች። ቀለም ቆጥራ ስትመለስ፣ እንደ ሌሎች ደብተር አንስታ አታጠናም። ተቀምጣ ትብሰለሰላች። ተኝታ ታስባለች። አሁንም የእሷ ምኞት ከተማ ዘልቃ ራስን መቻል፣ በሥራ መለወጥ ነው።

ከቀናት በአንዱ

አሁን ብርሃኔ የሰው እገዛ የቤተሰብ ርዳታ አያሻትም። ራሷን ችላ ማንነቷን መምራት ጀምራለች። ያለችበት ዕድሜ ከቤት አርቆ ይመልሳታል። ውላ ብትመጣ አርፍዳ ብትመለስ የሚታሰብላት አይደለችም። እንዲህ መሆኑ ለውሳኔ አመችቷል። አሁን ርቃ መሄድ፣ ሰርታ መመለስ ትችላለች። ሁሌም የእናቷን ውለታና ድካም አትረሳም። ዘወትር ሸክማቸውን ማሳረፍ፣ ሃሳባቸውን መካፈል ትሻለች።

ብርሃኔ ከቀናት በአንዱ ህልሟን ልታሳካ ከቤት ከቀዬዋ ራቀች። እግሮቿ የት እንደሚያደርሷት አልጠፋትም። አዲስ አበባ መሀል መርካቶ ስትቆም የሚቀበላት አላጣችም። እንግድነቷን ሳትቸገር ቀናትን ቆጠረች። ውሎ ሲያድር ግን እሷም ዘመዶቿም መፍትሔ ያሉትን መከሩ። ብርሃኔ ውላ የምትገባበት ሥራ ተፈለገላት። ለእሷ የሚሆን መተዳደሪያ አልጠፋም።

ከጠዋት እስከ ማታ እንግዶች የሚተራመሱበት ሆቴል እረፍት አልባ ነው። አላፊ አግዳሚው ጎራ እያለ ያሻውን ጠይቆ ይመገብበታል። የቤቱ ባለቤት ስለ ስሟ የማትሆነው የለም። ደንበኞች ርቀው፣ ገበያ እንዳይቀዘቅዝ ትጠነቀቃለች። አስተናጋጆች፣ ዕቃ አጣቢዎች፣ እንጀራ ጋጋሪዎች፣ እረፍት ይሉት ብርቃቸው ነው። ለአፍታ ቢዘናጉ የባለቤቷ ጦረኛ ዓይኖች በግልምጫ ያነሷቸዋል።

ብርሃኔም በዚህ ሆቴል ለመስተንግዶ ተቀጥራ መሥራት ጀምራለች። ሥራዋን አክብራ መያዟ በብዙዎች ዘንድ እያስወደዳት ነው። የአሰሪዋን ባህሪ ካወቀች ወዲህ ስለራሷ መጠንቀቅ ልምዷ ሆኗል። ሳትታዘዝ፣ ሳትጠየቅ ሥራውን መቅደሟ በባለቤቷ ዓይኖች ሞገስ ሆኗታል።

ሰርታ መግባቷ፣ የአቅሟን መያዟ ለውስጧ ሰላም ፈጥሯል። እንዳሰበችው ባይሆንም ገንዘብ አጠራቅማ ለእናቷ ትልካለች። አንዳንዴ ሀገር ቤት ስትሄድ ቡናውን ጋዝና ጨውን፣ ሳሙናና ልብሱን ቋጥራ ነው። ስትመለስ እጇ ባዶ ቢሆንም ምርቃት፣ ምስጋናው በረከት ሆኖ ያኖራታል።

ጥቂት ጊዚያት በአዲስ አበባ የዘለቀችው ብርሃኔ ሥራውን ለምዳ ሰዎችን አወቀች። ጉልበቷን ሳትሰስት የምትሮጥበት ሥራ ዛሬም ከክብሯ አላወረዳትም። የልቧን የምታደርስላት አሰሪ አሁንም በሙሉ ዓይኖችዋ እያየች የወር ደሞዟን ትከፍላታለች።

አንዳንዴ ብርሃኔ ደርሶ ድንገቴ ድካም ይፈትናታል። እንዳልሰማ ሆና ለማለፍ ትሞክራለች። በየቀኑ ሲደጋገም አረፍ ብላ ውስጧን ማዳመጥ ያዘች። ስሜቱ ከዚህ በፊት አጋጥሟት፣ ደርሶባት አያውቅም። ውሎ አድሮ እግሯ ማበጥ፣ ሰውነቷ መለወጥ ያዘ። ይህን ተከትሎ ወደታች የሚላት ህመም መጸዳጃ ቤት ያመላልሳት ጀመር።

አሁን ብርሃኔ እንደቀድሞው ለሆቴሉ ሥራ በፍጥነት አትሮጥም። አንቆ የያዛት ህመም በየአፍታው እያንገላታ ያሰቃያታል። ከቀድሞ ፍጥነቷ መቀነሷን ያስተዋለችው የቤቱ ባለቤት የሠራተኛዋን ችግር አምና መቀበል አልፈለገችም።

እውነቱ ቢገባትም ህመሟን አሳባ እንድታርፍ ፈቃዷ አልሆነም። ለሆዷ ህመም ሩዝ እንድትበላ፣ ሎሚ እንድትጠጣ፣ ለእግሯ እብጠት ደግሞ በውሀ እንድትነከር ደጋግማ መከረቻት።

ብርሃኔ የአሰሪዋ ያልተገባ ምክር አልጠቀማትም። ጊዜ አግኝታ ሆስፒታል አልሄደችምና ከህመሟ አልዳነችም። የችግሯን መባስ ያዩ ብዙዎች ስጋታቸውን ነገሯት። ችግሩ ውሎ ሲያድር የሚያስከትልባትን ጠንቅ በነገሯት ጊዜ ስለራሷ ፈጥና ወሰነች። በድንገት ሥራውን ለቃ፣ ቤቱን ትታ ለመታከም ቆረጠች።

በመንገዷ ላይ

አሁን ብርሃኔ የጤና ስብራቷ አሳስቧታል። በእጇ የያዘችው ገንዘብ ለዛሬ ችግሯ በቂ የሚባል ነው። ተመርምራ ለመታከም ሐኪም ቤቱን ጠይቃ አውቃለች። ስፍራው ደርሳ የጤና ችግሯን መስማት፣ መረዳት ትሻለች። ይህን እያሰበች መንገድ የጀመረችው ብርሃኔ በድንገት ከጎኗ ደርሳ በተዋወቀቻት ሴት አቀራረብ ተማረከች።

ሴትዬዋ ውስጧን የተረዳች ይመስላል። ጠጋ ብላ እሷ በምታውቀወና አፍ በፈታችበት ቋንቋ እያወራቻት ነው። ብርሃኔ የተለየ ቅርበት ተሰማት። የሴትዬዋ ፈገግታ፣ አቀራረብና ጨዋነት ውስጧን ገዝቶ ማንነቷን አሸነፈ። ሁለቱም ለመግባባት ጊዜ አልፈጁም። ስለችግሯ ጠየቀቻት። መታመሟን ገልፃ መታከም እንደምትሻ ነገረቻት።

በሀገሯ ልጅ ቅርበት ገጽታዋ የፈካው ብርሃኔ ችግሯን ሰምታ መፍትሔ በሰጠቻት ሴት ዕምነቷን ጣለች። በእጇ ያለውን ገንዘብ አልደበቀቻትም። ሴትየዋ በብርሃኔ እጆች ያለውን ገንዘብ ተቀብላ በሶፍት ጠቀለለች። ጥንቃቄ የሞላውን ድርጊት የምታየው ወጣት ቀጥሎ ስለሚሆነው አላወቀችም። ድርጊቷን እያስተዋለች ቀሪ የእጆቿን ገንዘብ አስረከበቻት።

ከደቂቃዎች በኋላ ብርሃኔ ራሷን ያገኘችው በበርካታ ሰዎች ተከባ ነበር። መታለሏ ቢገባትም ፈጥና ያደረገችው የለም። ከህመሟ በላይ ውስጧ ያደረው ሀዘን አንገቷን አስደፋት። የሕክምናዋ ጉዳይ ያለ መፍትሔ ቀናት ቆጠረ። ብርሃኔ አሁንም እግሮቿ ያብጣሉ። ድካምና ዝለት አብዝቶ ይፈትናታል። የዚህ ችግር መደጋገም ከእሷ አልፎ ሌሎችን ያሳስብ ይዟል።

አንድ ቀን ብርሃኔ እንደምንም ብላ ከሐኪም ፊት ቀረበች። ሙሉ ምርመራ ጨርሳም ውጤቱ ተነገራት። ቆየት ያለና ከባድ የሚባል የልብ ህመም አለባት። ዛሬ ነገ እያለች የመቆየቷ እውነት በጊዜ ለመታከም አላስቻላትም። ብርሃኔ የልቧ ችግር ደጋግሞ ሐኪም ፊት አቀረባት። አሁን ተከታታይ ሕክምናና መድኃኒት ያስፈልጋታል።

ዛሬ ብርሃኔ እንደትናንቱ ተሯሩጣ የምትሰራ አይደለችም። ለሕክምናውና ለመድኃኒት ግዢም በቂ ገንዘብ ሊኖራት ግድ ይላል። ብርሃኔ ውስጧ አብዝቶ ተፈተነ። የሰዎች ምክር ከእሷ ጭንቀት ተዳምሮ ያለመፍትሔ ቀናትን ቆጠረች። ውላ አድራ ግን ከራሷ መክራ ተማክራ ይበጃል ባለችው ሃሳብ ቆረጠች።

አዲሱ ቤት

ብርሃኔ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ሥራ ከጀመረች ሳምንት አልፏታል። በቅንነት ማገልገል በጀመረችበት ቤት ያሉ ቤተሰቦች የእሷን ከእነሱ መቀላቀል የወደዱት ይመስላል። በዚህ ቤት ለዓመታት ታመው የቆዩት እናት ዛሬም አልተሸላቸውም። ውሎ አዳራቸው ካልጋ ነውና የርዳታ እጆችን ይሻሉ። ለዓመታት ራሳቸውን ሳያውቁ በሰው እገዛ ቆይተዋል።

ወይዘሮዋ አብሯቸው የኖረው የአዕምሮ ህመም ከሌሎች አግባብቶ አላኖራቸውም። እንደማንም ራሳቸውን አውቀው መጸዳጃ አይጠቀሙም፣ ‹‹ራበኝ ጠማኝ›› ማለትን አያወቁም። እንዲያም ሆኖ ሰላማዊና ዝምተኛ ናቸው። ብርሃኔ በዚህ ቤት ያጋጠማት እውነት ይህ ብቻ አይደለም። የሴትየዋ ትልቅ ልጅ በተመሳሳይ የአዕምሮ ህመም የተጠቃ ነው።

ብርሃኔ በዚህ ቤት ገብታ ሥራ ከጀመረች ወዲህ ከባድ ኃላፊነት ተቀብላለች። የእሷ የዕለት ተግባር እንደተለመደው ዓይነት የቤት ሥራ ብቻ አይደለም። በተለየ ተግባር ተጠምዳ ትውላለች። በወጉ ራሳቸውን የማያውቁ እናትና ልጅን ማገዝ ቀላል አይደለም። እንዲህ መሆኑ ግን አማሯት፣ አስጨንቋት አያውቅም።

የልብ ነገር

ብርሃኔ የልቧን ጉዳይ አልዘነጋችም። በዚህ ቤት ተቀጥራ መሥራት ከጀመረች ወዲህ በጤና መድህን ተጠቃሚ ሆናለች። በየጊዜው እየተመረመረች መድኃኒቷን ትወስዳለች። ባለችበት ቤት ኃላፊነት ወስዳለችና በእጆቿ ስላሉት ነፍሶች ግድ ይላታል። ሴትዬዋን አብልታ፣ አልብሳ፣ አጸዳድታ ማሰደሰት የዘወትር ተግባሯ ሆኗል። ይህን ማድረጓ ለእሷ ህሊና ብርታትና ርካታ ነው።

ጥቂት ጊዚያትን እንደዘለቀች የቤቱ ወይዘሮ በሞት ተለዩ። ከእሳቸው ሀዘን በኋላ ቤቱ ያለምንም ባለቤት መቆየቱ ግድ ሆነ። አሁን የሴትዬዋ ልጅ በቤቱ ቀርቷል። ከእናቱ ሞት በኋላ ብቻውን መኖሩ፣ ለእሱ ፈተና እንደሚሆን ማንም ያውቃል።

እሱ እንደሳቸው ራሱን ስቶ ከአልጋ ባይውልም ውስጡን ገዝቶ ሕይወቱን መግዛት የሚችል አይደለም። መደበቂያ በሆኑት ጫትና ሲጋራ ተሸሽጎ መዋልን ልምድ አድርጓል። ከአማኑኤል ሆስፒታል የሚወሰድው መድኃኒት ያረጋጋው ይመስላል። ከሁሉም ጋር ግንኙነቱ ሰላማዊ ነው። አንዳንዴ በሚያስገርም ቅርበት ከሰዎች ይግባባል።

ብርሃኔ የዚህ ሰው እናት ከሞቱ በኋላ በግዴለሽነት ትታው አልወጣችም። ቤቱን በኃላፊት ከተረከበው አንድ ዘመዱ ጋር ሕይወትን በጋራ ቀጠለች። በግቢው የሚከራዩ ቤቶች ገቢ ለቤት ወጪና ለእሷ ደሞዝ ክፍያ ይውላል። እንደ ልጅ፣ እንደ እህት ሆና በምትመራው ቤት ማንም ሠራተኛ ነች የሚላት የለም።

ታማኝነት ለአስራ አራት ዓመታት

አሁን ብርሃኔ በዚህ ቤት ኑሮ አስራ አራት ዓመታትን ቆጥራለች። ካለባት የልብ ህመም ጋር ደሞዟ በቂ ነው ባይባልም ያለማንም አዛዥነትና ግዴታ በራሷ የመኖር መብት አላት። ሕክምና ባሻት ጊዜ ከጤና መድህን ባላት ጠቀሜታ በወቅቱ ትታያለች።

በከባድ ሥራ እንዳትያዝ፣ በጭንቀት እንዳትወጠር የእሷ ኑሮ ዋስትና ሆኗል። አዲስ አበባ ላይ ብዙ ዘመድ የላትም። አባቷ ሲሞቱ ሆድ ውስጥ የነበረው ታናሽ ወንድሟ ግን በቅርቧ ነው። ዛሬ የጋራዥ ሠራተኛ ሆኖ ራሱን ያግዛል።

ዛሬ ላይ

ብርሃኔን ያገኘኋት ከአንድ የግል ሆስፒታል ልቧን ለመታየት በመጣችበት አጋጣሚ ነበር። በእጇቿ ያሉትን የሕክምና ወረቀቶች በጥንቃቄ መያዟ ያስታውቃል። ከልብ ህመም ጋር ለአስራ አምስት ዓመታት ቆይታለች። ከሰሞኑ በተለየ መልኩ የሚሰማት ህመም ጤና ቢነሳት ዳግም ምርመራ ለማድረግ ከሆስፒታሉ መምጣቷ ነው። ክፍያው እስከ ዛሬ በጤና መድህን ከምታወጣው ወጪ በእጥፍ ይጨምራል። እንዲያም ሆኖ ስለልቧ ዝም አትልም። ለመኖር ልቧ ዋስትናዋ ነው። በልቧ ትርታ ውስጧን ታደምጣለች። ለምትኖርለት ተስፋ ጥላ ከለላ ሆኗታልና ሁሌም ‹‹ስለ ልቤ ዝም አልልም›› ትላለች።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You