በራስ መተማመን ከፍም ዝቅም ይላል። ከፍ ባለ ጊዜ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምትና ግንዛቤ ይጨምራል። ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋም ከፍ ያለ ይሆናል። በሌሎች ሰዎች ዘንድ የሚሰጣቸው ቦታና ከበሬታም ያዛኑ ያህል ያድጋል። ያለማንም ተፅእኖና ጥገኝነት ሥራቸውን በብቃት ያከናውናሉ፤ ስኬታማም ናቸው።
ይሁንና በራስ መተማመን ዝቅ ሲል ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ተቃራኒ ይሆናሉ። በራስ መተማመናቸው የወረደ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ምንም ነገር ማሳካት እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ዓለም ክፉ ትመስላቸዋለች። ሁሌም በራሳቸው ላይ ክፉ ነገር የሚደርስ ይመስላቸዋል። እጅና እግራቸው የታሰረ፤ ምንም ነገር ማድረግ የማይችሉ ይመስላቸዋል።
በራስ መተማመናቸው የወረደ ሰዎች ሁሌም ቢሆን ስለራሳቸው ጥሩ ጥሩውን ሳይሆን መጥፎውን ብቻ ነው የሚናገሩት። በተደጋጋሚ ‹‹እኔ እኮ ደደብ ነኝ፣ አልረባም፣ አልችልም፣ ከሰው ያነስኩ ነኝ›› ይላሉ። በራሳቸው ላይ የሚቀልዱት ቀልድ እራሱ አሉታዊና ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርግ ነው። በተለይ ደግሞ መጥፎ ነገር ካጋጠማቸው ሁሌም ራሳቸውን ይወቅሳሉ። ራሳቸውን ጥፋተኛ አድርገው ይቆጥራሉ። ሌሎች ሰዎች ከእነርሱ የተሻለ ነገር ማድረግ የሚችሉና የተሻለ ውሳኔ መወሰን የሚችሉም ይመስላቸዋል።
እነርሱ የሌላቸው ነገር ሁሉ ሌሎች ሰዎች ያላቸው ይመስላቸዋል። ለእነርሱ ደስታ፣ሳቅ ወይም መዝናናት የሚገባቸው አይመስላቸውም። ሁሌም እንደተቆለፉና ዝግት እንዳሉ ነው። ጭምትም ናቸው። ጥሩ ነገር ሲያደርጉና በሕይወታቸው አንድ ነገር ሲያሳኩ እንኳን ራሳቸውን አያሞግሱም። ‹‹ጀግና ነኝ፤ ጎበዝ ነኝ፤ አደረኩት፤ አሳካሁት›› አይሉም። የሆነ ነገር ሆኖ ነው እንጂ እኔ እንዲህ አድርጌ አይደለም የተሳካልኝ ነው የሚሉት። የሚገባቸውን ክብርና ውዳሴ ለራሳቸው አይሰጡም። ይህም የመጀመሪያው በራስ ያለመተማመን ስሜት ነው።
በሁለተኛው ደረጃ ደግሞ በራስ መተማመናቸው የወረደ ሰዎች ራሳቸውን አያከብሩም። በማንነታቸውና ራሳቸውን በመሆናቸው ብቻ ፍቅር የሚገባቸው አይመስላቸውም። ሁሌም ቢሆን ደፋ ቀና የሚሉት ሰዎችን ለማስደሰት እንጂ ራሳቸውን ለማስደሰት አይደለም። የራሳቸውን ፍላጎት ትተው የሌሎችን ሰዎች ፍላጎት ለማሟላት ይታትራሉ። ሌሎች እንዲያንቋሽሿቸው፣ እንዲሰድቧቸው መረጋገጪያና መረመማመጂያ እንዲያደርጓቸው ይፈቅዳሉ።
ማድረግ የማይፈልጉትን ነገር ለሰዎች ሲሉ በይሉንታ ያደርጋሉ። የራሳቸው ወሰን የላቸውም። አይሆንም፣ አልፈልግም አያውቁም። የክብር፣ የመወደድ፣ የመፈቀር መብት ያላቸው አይመስላቸውም። በዚህም የተነሳ ግብስብሱን ሁሉ ይቀበላሉ። የሚስፈልጋቸውን ነገር አይመርጡም። ይህን ሁሉ ደግሞ የሚሰራው በጭንቅላታው ውስጥ ያለው አቋም ነው።
ሰዎች በየትኛውም የኑሮ ሁኔታ ላይ ቢሆኑ፤ ገቢያቸው አነሰም በዛ፣ ቆሸሹም ፀዱ፣ከፍ አሉም ዝቅ አሉ፣ ሥራ ኖራቸውም አልኖራቸው ፍቅርና ክብር ይገባቸዋል። ከማንም አያንሱም። እንዲያም ሆኖ ግን በራስ አለመተማመን ችግር እዛም እዚም ጎልቶ ይታያል። ታዲያ በራስ አለመተማመን ችግር እንዴት ሊመጣ ይችላል? የብዙዎች ጥያቄ ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ 90 ከመቶ የሚሆነውን በራስ አለመተማመን ችግር የሚመጣው ከአስተዳደግ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ባህልና አስተዳደጋችን ራሳችንን እንድንወድ፣ እንድናከብር፣ ጠንካራ እንድንሆን ሳይሆን እንድንፈራ፣ እንድንሸማቀቅ፣ እንድንሽቆጠቆጥና ሰው ምን ይለኛል ብለን አንገታችንን ደፍተን እንድንኖር ነው የሚያደርገን።
ለአብነት ሰዎች በልጆች ጊዚያቸው በቤት ውስጥ በጣም የሚገረፉ ከሆነ፣ የሚሰደቡ ከሆነ፣ ጥሩ ነገር ሲያደርጉ የማይበረታቱና የማይታዩ ከሆነ፣ ትንሽ ሲያጠፉ ጓደኛውም ጎረቤቱም ተሰብስቦ በመደብደብ፣ በመስደብ፣ በመቅጣትና በማንቋሸሽ የሚረባረብ ከሆነ፣ አሳዳጊዎች ፍቅር የማይሰጡ ከሆነ፣ እንደው አናግረዋችሁም ከሆነ ያናገሩበት መንገድ የሚያጥላላና የሚያንቋሽሽ ከነበረ፣ ከሰው ጋር የሚያወዳድሯችሁ ከነበረ፣ እንደምታስጠሉና እንደማትረቡ ነግረዋችሁ ከነበረ፣ ደካማ፣ ደነዝ ወይም የማትረቡና በራሳችሁ መቆም እንደማትችሉ እየተነገራችሁ አድጋችሁ ከነበረ እያደጉና ነብስ እያወቁ ሲመጡ በራስ መተማመናቸው እየወረደ ይመጣል።
በተመሳሳይ በትምህርት ቤት ውስጥም ታዳጊዎች መምህራኖቻቸው አልያም የክፍል ጓደኞቻቸውና ማህበረሰቡም ጭምር የሚሳለቁባቸው፣ የሚሳደቧቸው፣ የሚያንቋሽሿቸው ከነበረ፣ የሚያዋርዷቸው ከነበረ፣ መደፈር ወይም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው ከነበረ፣ ትምህርት በቶሎ የማይቀበሉ ብሎም የማይረዱ ከሆነ፣ በማህበረሰቡ በወጣ መስፈርት መሰረት ቆንጆ መስለው የማይታዩ ከነበረ፣ እንደሚያስጠሉና ማንም እንደማይፈልጋቸው ሲነገራቸው ከነበረ በቀጣይ ሕይወታቸው በራስ መተማመናቸው እጅጉን ወርዶ ይታያል።
አንዳንዴም ከአብዛኛዎቹ የሃይማኖት መሪዎች የሚወጣው ነገር የሚያስፈራራ፣ የሚያሳፍር፣ የሚያስደንግጥና የሚያሻማቀቅ፣ እያንዳንዱ የሚደረገው ነገር ሁሉ ሀጢያትና አፀያፊ እንደሆነ፣ እንደሚያጋጭንና እንደሚያጣላ ነው። ይህም በራስ መተማመን ዝቅተኛ እንዲሆን የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል። ንግግሮቹ ሰዎች ራሳቸውንና ማንነታቸውን እንዲጠሉም ያደርጋሉ።
ዞሮ ዞሮ ግን ዋናው ነጥብ የወረደውን በራስ መተማመን እንዴት መመለስ እንደሚቻል ማወቁ ጠቃሚ ነው። የመጀመሪያው በራስ መተማመንን የመገንቢያ መንገድ ራስን መመርመር ወይም ማወቅ ነው። ለመሆኑ የራሳችሁን ባህሪይ ታውቁታላችሁ? ከላይ ከተጠቀሱት በራስ መተማመን መውረድ ባህሪይ ጋር የሚመሳሰለው የእርስዎ ባህሪ ምንድን ነው? መልስዎ ‹‹አዎ!›› ከሆነ የእናንተ በራስ መተማመን ወረድ ያለ ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ግን የወረደ በራስ መተማመን አላችሁና የዓለም ፍፃሜ ቀርቧል ማለት አይደለም። የእናንተ ጥፋትና ፈልጋችሁ ያመጣችሁት ነገር አይደለም። ካጋጠሟችሁና ከደረሱባችሁ ነገሮች ጋር ተያይዞና ተጠራቅሞ የመጣ ማንነት ነው።
በዚህም ልትኮሩ እንጂ ልታፍሩ አይገባም። ምክንያቱም በራስ የመተማመን አቅማችሁን ለመገንባት የመጀመሪያው መንደርደሪያ ራስን መመርመር ነውና። ማንነትዎን፣ ሕይወትዎንና ግንኙነትዎን የሚያበላሹትን ፀባዮችና ባህሪያት ለይቶ ማየትና ማወቅ ይኖርብዎታል። ‹‹ይሄ ችግር አለብኝ›› ብሎ ለራስ መንገር ያስፈልጋል።
ሁለተኛው በራስ መተማመንን የመገንቢያ መንገድ ከራስዎ ጋር የሚያደርጉት ንግግር ነው። ይህ ሕይወትዎን የሚያስተካክለው ወይም የሚያበላሸው አንዱ መንገድ ነው። እስቲ ራስዎን እንዴት ነው የሚያናግሩት ? እስቲ መስታወት ፊት ቆመው ከራስዎ ጋር እንዴት ነው የሚያወሩት? አስጠላለሁ ነው ወይስ አምራለሁ፣ እደብራለሁ ወይስ ደስተኛ ነኝ ነው የሚሉት? ወይም ደግሞ ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ ይጠሉኛል፤ ማንም የሚወደኝ ሰው የለም፤ ነገ ብሞት እንኳን ዞር ብሎ የሚያየኝ ሰው የለም ነው ብለው የሚያስቡት?
እንዲህ የሚያስቡ ከሆነ ለምንድን ነው እነዚህ የማስበው፣ ማነው እንደዚህ ያለኝ፣ ማነው እንደዚህ የነገረኝ ብለው ራስዎን ይጠይቁ። እነዚህ ነገሮች ምናልባት ሰዎች የነገርዎት ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ራስዎ በጭንቅላትዎ የፈጠሯቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ እርስዎ ማድረግ የሚገባዎ ነገር እንዲህ የሚያስበውን ጭንቅላትዎን አንድ በአንድ ‹‹ውሸት ነው›› እያሉ አንድ በአንድ ፉርሽ ማድረግ ነው። እነዚህ አስተሳሰቦች ካፈረሱ በኋላ ደግሞ አዲስና እውነት በሆኑ ነገሮች አእምሮዎን መሙላት ያስፈልጋል። ፍቅር እንደሚገባችሁ፣ውብና መወደድ የምትችሉ ሰው እንደሆኑ ለራስዎ እየደጋገሙ መናገር አለብዎት።
በጭንቅላትዎ ውስጥ ያለው የራስዎ ድምፅ ከየትኛውም ድምፅ በላይ ይጮኻል። ከማንም ሰው በላይ ደግሞ ከራሳችን ጋር ነው ቀኑን ሙሉ የምናወራው። እርስዎም እንደዚሁ። ያ በአእምሮዎ ውስጥ ያለው ድምፅ ራስዎን እንዲጠሉና ራስዎን የበታች እንዲሆኑ የሚያደርጉ ከሆነ አይተርፉም። ሌሎች ሰዎች ከውጭ መጥተው ሲናገርዎት በወረደ የራስ መተማመንዎ ላይ ሌላ መወርድ ያመጣብዎታል። ነገር ግን በውስጥዎ ጥሩ ነገር ካለ፣ ሁሌም ለራስዎ የሚነግሩት ነገር ጥሩ ከሆነ፣ ‹‹እኔ ፍቅር ነኝ፣ እኔ ጥሩ ነኝ፣ ለእኔ ጥሩ ነገር ሁሉ ይገባኛል ካሉ ሰዎች የሚሉኝ ነገር ሁሉ እኔ አይደለሁም›› ብለው ለራስዎ የሚነግሩ ከሆነ ከውጭ ያለው ጫጫታው ወደ አእምሮዎ አይገባም። ነጥሮ ነው የሚመለሰው። ምክንያቱም ከራሳችሁ ጋር አስቀድማችሁ ተስማምታችኋልና።
ሶስተኛው በራስ መተማመንን የመገንባት መንገድ ሲነገርዎ ‹‹ኡፍፍፍ…›› ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን ሕይወትዎንና ማንነትዎን የመለወጥ ኃይል ያለው መንገድ ነው። እሱም አሁን ያለዎትንና ተፈጥሮ የሰጠዎትን ነገር ሁሉ አምኖና ወዶ መቀበል ነው። ሁልጊዜ ራስዎን በመስደብና በማዋረድ ፋንታ ሁሌም ያለዎትንና የሚወዱትን ነገር ሁሉ ያድንቁ። በሕይወትዎ ሊቀይሯቸው የማይችሉትን ነገሮች ደስተኛ ሊሆኑባቸው ይገባል። ሁሉም ሰው አንድ ነገሩን ሊወድ ይችላል። ምናልባት ፀጉሩን፣ ዓይኑን፣ ከንፈሩን፣ አፍንጫውን፣ ጥርሱን፣ ቀለሙን አልያም የሰውነት አቋሙን። ደግነታችሁን፣ አነጋገራችሁን፣ ድምፃችሁን፣ ፍቅር ሰጪነታችሁን፣ አሳቢነታችሁን፣ ታማኝነታችሁን ልትወዱ ትችላላችሁ። ዞሮ ዞሮ ግን ሁሉም ሰው ቢያንስ ስለራሱ አንድ የሚወደው ነገር አለ።
እነዛ በሚወዷቸው ነገሮች ላይ ሲያተኩሩ የማይወዷቸው ነገሮች ከኋላ መደብዘዝ ይጀምራሉ። ነገር ግን አይ ይሄ ነገር ሕይወቴን እያበላሸ ነው፣ ራሴን እንደጠላ እያደረገኝ ነው ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ፤ ለምሳሌ ከመጠን በላይ ወፍራም ከሆኑና እነዚህን መሰል ችግር ቢጋጥምዎ ለራስዎ ደስታና ጤና ሲሉ መቀየር ይችላሉ። ነገር ግን ደግሞ አጭር ስልሆናችሁ ፈጣሪ ሆይ ለምን አጭር አደረከኝ ብለው ማማረር የለብዎትም። እጥረትዎን ውበት አድርጉት። በራስ መተማመን ሲጨመርበት ሁሉም ነገር ያምራል። መቀየር የማይችላቸውን ነገሮች አምነው ሲቀበሏቸው በራስ መተማመንዎ ከፍ ይላል ሰዎችም እርስዎን የሚያዩበት መንገድ ይቀየራል።
አራተኛውና የመጨረሻው በራስ መተማመንን የመገንቢያ ዘዴ ለሕይወት ኃላፊነት መውሰድ ነው። ለሕይወት ኃላፊነት መውሰድ የብዙ ሰው ችግር ነው። በርካታ ሰዎች በሕይወታቸው ለሚፈጠርባቸው ክስተት በአብዛኛው ኃላፊነት አይወስዱም። ሁሌም ሕይወት ለእርስዎ ጠማማ እንደሆነች የሚያስቡና አይሳካልኝም የሚሉ ከሆነ ለተፈጠረው ነገር ወይም ለውድቀትዎ ‹‹የኔ አስተዋጽኦ ምንድን ነው? ብለው ራስዎን ይመርምሩ።
ሁሌም ‹‹እኔ እኮ የሰው መጫወቻ ሆንኩ፣ ጥሩ ሰው ስለሆንኩ ሰዎች መጠቀሚያ አደረጉኝ›› ብለው የሚያለቃቅሱ ከሆነ የሰዎች መጠቀሚያ የሆኑት እርስዎ ሁሉንም የሚጠቅሙና የሚረዱ ስለሆኑ ሳይሆን ለሰዎች በሰዎች ለመወደድ ካላችሁ ከፍተኛ ፍላጎትና ፍቅር አንፃር ነው። በሰዎች መወደድን የሕይወትዎ ትልቁ ስኬት ስላደረጉት ነው። ለሰዎች ምንጣፍ ሆነው ለራስዎ ዘብ የማይቆሙ ከሆነ፣ ሲጠርዎት አቤት ሲልክዎት ወዴት የሚሉ ከሆነ በርግጥም የሰዎች መጠቀሚያ ይሆናሉ።
ነገር ግን ለአንድ ደቂቃ ቆም ብለው ‹‹ይህም ያም ለምንድን ነው መጠቀሚያ የሚያደርገኝ? ነው ወይስ ችግሩ እኔ ጋር ነው?›› ብለው ቢያዩ ለራስዎ ዘብ እንደማትቆሙ፤ ራስዎን እንደማያስከብሩና ራስዎ ለራስዎ ዘብ መቆም እንዳለብዎ ይገባዎታል። ጥፋትዎ የቱ ጋር እንደሆነ ያዩታል። ያ ነው ለራስ ኃላፊነት መውሰድ ማለት። ለሚፈጠርብዎ መጥፎ ነገር በአብዛኛው የእርስዎም አስተዋጽኦ አለበት። በተጠቂነትና በተበዳይነት ስሜት ውስጥ መቆዘም ሳይሆን ‹‹አሃ ለካ እኔም ጥፋት አለብኝ፣ እኔም የችግሩ ተባባሪ ነበርኩ›› ብለው ወደራስዎ ማየት ያስፈልጋል።
ለችግሩ ወይም ለደረሰው ጥፋት የእርስዎም እጅ እንዳለበት ሲያምኑ ከራስዎ ጋር በደንብ ይተዋወቃሉ። በቀጣዩ ጊዜም ጥፋቱን አይደግሙትም። ይህም በራስ መተማመንዎን ያጎለብተዋል። እንደዚህ ዓይነት የሚያሳምም ግልፅነትና ተጠያቂነት ከእርስዎ ጋር ያስታርቅዎታል፤ ያዋድድዎታል። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ደግሞ በራስ መተማመንዎን ጣራ ያስነካዋል።
ከዚህ በተረፈ ሁሌም ቢሆን ከራስዎ ጋር ጊዜ ያሳልፉ። ከራስዎ ጋር ያለውን ግንኙነት ይጨምሩ። ከራስዎ ጋር ይበልጥ ይተዋወቁ። የሚጠቅሟችሁን ሃሳቦች ሁሉ በወረቀት ላይ ያስፍሩ። ደጋግመው ያንብቧቸው፤ ይጠቀሙባቸው። ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ሁሉ ለራሳችሁ ያደርጉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም