ብዙ ሰዎች ነፃነት የላቸውም። ነፃነት የምለው በፖለቲካ ቋንቋ የተለመደውን የመናገር፣ የመሰለፍ እና ሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ማለቴ አይደለም። እርሱማ እንኳን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የተንበሸበሸባቸው ናቸው በሚባሉት ሀገራትም አከራካሪ ነው። የኢትዮጵያን ለየት የሚያደርገው ግላዊ የአመለካከት ነፃነት የሌለን መሆኑ ነው። ሀገራዊ ነፃነት የሚመጣውም ከግለሰብ ነፃነት ነው። መጀመሪያ ግለሰቡ ነፃ ሆኖ ማሰብ ሲችል ነው።
ፍረጃ የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ አደገኛ ነገር ነው። አንድን ሰው እንዲህ ነው ብሎ ለመበየን ሰውየውን ብቻውን በነፃነት የማየት ነፃነት የለንም። ብዙዎቻችን ራሳችንን ችለን በራሳችን መዝነን ድርጊቶችን በነፃነት ማየት አንችልም። ከዚያ ይልቅ ከዚህ በፊት ውስጣችንን በሞላው ትርክት እንጠለፋለን። ድርጊቱን ብቻውን ከማየት ይልቅ ትርክቱ በፈጠረው ኃይል አዛብተን እንፈርጃለን። ነገሬ ግልጽ እንዲሆን ቀላል ማሳያ ልጠቀም።
ለምሳሌ፤ የከተማ ልጅ እና የገጠር ልጅ የሚባል ነገር አለ። የከተማ ልጅ የገባው፣ ሁሉን ነገር በቀላሉ የሚረዳ፣ የሚያርጋቸው ነገሮች ሁሉ ትክክል… ተደርገው ይነገራሉ። በተቃራኒው የገጠር ልጅ ደግሞ በቀላሉ የማይገባው፣ አሰልቺ፣ የሚያደርገው ነገር ልክ ያልሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ይህ እንግዲህ በትርክት የምንሰማው ነገር ነው።
ይህን ማሳያ ይዘን አንድ ራሱን ችሎ ማሰብ የማይችል ሰው፣ ድርጊቶችን በራሱ መበየን የማይችል ሰው ሊያደርግ የሚችለውን እናስብ። አንድ አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ፣ በባህሪውም ‹‹የጨሰ አራዳ›› የሚባል ሰው መንገድ ዳር ሽንቱን ሲሸና ተመለከተ እንበል። ይህ ራሱን ችሎ ማሰብ የማይችል ሰው ይህ የከተማ ልጅ መንገድ ዳር ሲሸና ቢያው፤ የነፃነት፣ ማንንም የማይሰማና ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ፣ ፈላስፋ ነገር አድርጎ በበጎ ያይለታል። ለምን? አዕምሮው ቀድሞ ሰውየውን በበጎ ያየው ስለነበር ማለት ነው። በተቃራኒው ደግሞ ከገጠር የመጣ ነው የተባለ ሰው መንገድ ሲያጸዳ ቢያየው፤ ‹‹እዩት አወቅኩ አወቅኩ ብሎ፣ እዩት ይሄን ፋራ! የሠለጠነ መስሎት እኮ ነው!›› ሊል ይችላል። ለምን? አዕምሮው ላይ በሠራው ነገር ይህን ሰው በበጎ ስላላየው።
ቀደም ሲል እንዳልኩት ይህን የሚያደርጉት ራሳቸውን ችለው ማሰብ የማይችሉት ናቸው። ራሱን ችሎ ማሰብ የማይችል ሰው መንገድ ዳር ከመሽናት እና መንገድ ከማጽዳት የትኛው ነው የሥልጣኔ ምልክት ከማለት ይልቅ ‹‹ማነው ያደረገው?›› የሚለው ላይ ያተኩራል። በጣም ቀላል ምሳሌ ነው የወሰድኩት። ነገሩን ወደ ፖለቲካና ሀገራዊ ጉዳይ ስናሳድገው የዚህ ነፀብራቃዊ ነው ለዚህ ሁሉ ችግር ያደረገን።
ፍረጃ አዕምሮ ላይ የሚሠራ መጥፎ ነገር ነው። አንድን ሰው ከድርጊቱ ይልቅ የሰውየውን ምንነት ማየት ማለት ነው። የምንነት መፈረጃችን ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ዕድሜ… ሊሆን ይችላል። ሃይማኖትና ብሄር በጣም የታወቀና የተለመደ ስለሆነ የዕድሜና የፆታ ምሳሌዎችን እንውሰድ።
ሴቶች እንዲህ ይወዳሉ፣ ወንዶች እንዲህ ያደርጋሉ፣ ሴቶች ይህን አይችሉም… የሚሉ ትርክቶችን ገንብተናል። ብዙ ሰው በዚህ ውስጡ የተሞላ ነው። አንዲት ሴት የሆነ ነገር ብትሳሳት የተሳሳተችው ሴት ስለሆነች ነው ብሎ ያስባል እንጂ እንደ ሰው ነው ብሎ አይረዳውም። ወንድ መቶ ጊዜ የሚሠራውን ስህተት ሴት አንድ ጊዜ ብትሠራው ‹‹አይ የሴት ነገር!›› ይባላል። አንድ የመሳካት ዕድል የሌለውን ነገር ሴት ሄዳበት ሳይካሳ ቢቀር ‹‹ድሮስ የሴት ነገር!›› ሊባል ይችላል። ለምን? ነገርየውን ሎጂካል ሆኖ ያልተሳካበትን ወይም የተበላሸበትን ምክንያት የማየት ነፃነት የለንም። ፍረጃ ውስጣችንን አበላሽቶታል።
በተመሳሳይ የዕድሜ ፍረጃዎችም ነፃነት እንዳይኖረን አድርገውናል። ለምሳሌ፤ አንድ በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሰው ማንኛውም ሰው የሚሳሳተውን ነገር ቢሳሳት ‹‹ውይ! በቃ አረጀህ!›› ይባላል። ማንኛውም ሰው ሊረሳ የሚችለውን ነገር ሲረሳ ‹‹በቃ አረጀህ!›› ይባላል። ነገርየውን ሰዋዊ ከማድረግ ይልቅ ስላረጀ ያደረገው መስሎ ይታየናል። የአለባበስ ምርጫዎችን ሰዋዊ ምርጫ ከማድረግ ይልቅ ከዕድሜ ጋር የተያያዘ ፍረጃ እንሰጠዋለን።
እዚህ ላይ የራሴን ምሳሌ ላንሳ። ሙቀት አልችልም። ጃኬት ስደርብ ይሞቀኛል። በዚህም ምክንያት ብዙ ጊዜ በቲሸርትና በሸሚዝ ነው የምንቀሳቀው። ጠዋት ጠዋት በቲሸርት መሄድ ፍላጎቴ ሆኖ ሳለ ‹‹ገና ጎረምሳ ነኝ ለማለት ነው?›› የሚለው የአንዳንድ ባልደረቦቼ ቀልድ ‹‹ይሄ ነገር እንደዚያ ይመስል ይሆን እንዴ?›› ብየ እንዲያስብ ያደርገኛል። በመሆኑም ጠዋት ጠዋት ለሰው ዓይን ስል እየሞቀኝም ቢሆን ጃኬት እደርባለሁ።
ከሞቀው አንድ የ80 ዓመት አዛውንት ለምን ዝናብ ለዝናብ በቲሸርት አይሄድም? ከበረደው አንድ የ20 ዓመት ጎረምሳ ለምን ካፖርት ለብሶ አይሄድም? አዕምሯችን ነገሮችን ነፃ ሆኖ ስለማያይ ነው።
አዕምሯችን ነፃ ባለመሆኑ ምክንያት ቅድመ ጥላቻ (Prejudice) ውስጥ ይገባል። ቅድመ ጥላቻ ማለት ሰውየው ገና ምንም የበደለን ነገር ሳይኖር ዝም ብሎ አይቶ መጥላት ማለት ነው። ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎችን ከማወቃችን በፊት ስንገምታቸውና ከተግባባን በኋላ ስናውቃቸው ሌላ ሰው የሚሆኑብን። በቅድመ ግምት የሆነ ስብዕና እንሰጣቸዋለን፤ ቀርበን ስናያቸው ግን የሰጠናቸው አይነት ላይሆን ይችላል። የቅድመ ጥላቻ ችግሩ ግን ቀርበን እንድናውቃቸው ዕድል አይሰጠንም። ምክንያቱም ፈርጀናቸዋል።
አንዳንድ ሰዎች የሚወዱት ሰው ምንም ቢያደርግ ትክክል መስሎ ይታያቸዋል። አስቀድመው የጠሉት ሰው ግን ምንም በጎ ነገር ቢያደርግ አይዋጥላቸውም። ምክንያቱም ነገርየው የሚሠራው አዕምሮ ላይ ነው። አዕምሮ ላይ የሚሠራ ነገር ከፍተኛ ኃይል አለው። አዕምሮ ላይ የሚሠራ ነገር መሬት ላይ የሌለ ነገር እንዳለ አድርጎ ሊያሳየን ይችላል፤ ወይም መሬት ላይ ያለውን ነገር እንደሌለ አድርጎ ሊያሳየን ይችላል። አንዲት ጓደኛዬ የነገረችኝን አስቂኝ ገጠመኝ ልጥቀስ።
አባቷ ልጆች ቅቤ ሲቀቡ አይወድም። ባይሸት እንኳን ሸተተኝ ይላል። ልጆቹ ቅቤው እንደማይሸት ሲነግሩትም አያምንም። እናም አንድ ቀን ልጆቹና እናታቸው ተመካክረው እንዲህ አደረጉት። ምንም ቅቤ ሳይቀቡ ፀጉራቸውን ልክ ሲቀቡ እንደሚደረገው በሻሽ ሸፍነው ጠበቁት። ልክ ገና ከመግባቱ ‹‹ኤጭ! እንዲያው ይሄንን ቅቤ እየተቀባችሁ…›› ማለት ጀመረ። ‹‹አባዬ የምር ሸቶሃል?›› አለችው። መጥፎ ነገር ሲሸት የሚባለውን ድምጽ እያወጣ ‹‹አዎ!›› አላት። ይህኔ ሁሉም እየተሳሳቁ የተሸፈኑትን እየገለጡ አለመቀባታቸውን አሳዩት። እሱም አባት ነውና ምን ታመጣላችሁ በሚል ስሜት ትንሽ ፈገግ ብሎ አለፈው።
የሥነ ልቦናን ነገር ለማረጋገጥ ጥሩ ማሳያ ነው። ሰውየው ቅቤ ይሸተኛል የሚል ነገር በአዕምሮው ውስጥ ተሠርቷል። ስለዚህ የሚሸት ቅቤ ባይኖር እንኳን ቅቤ ሲቀቡ የሚያየውን አሸፋፈን ካስተዋለ የሸተተው ይመስለዋል ማለት ነው።
ይሄን ነገር በብዙ መንገድ አረጋግጫለሁ። አንዳንድ ሰዎች የማይጠሉት ሰው ላይ ያለ አደገኛ ሽታ ብዙም አይረብሻቸውም። የሚጠሉት ሰው ላይ ግን ለማንም የማይሸት ነገር ሁሉ ሸተተኝ ሊሉ ይችላሉ። ለምን? ሰውየው ላይ የሠሩት ፍረጃ ስላለ። ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለውን ነገር ለሚጠሉት ሰው ሲሆን እንደማንኛውም ሰው ስለማያዩት።
ከእንዲህ አይነት ነገር እንድን ዘንድ ውስጣዊ ነፃነት ይኑረን! ነገሮችን ከግለሰባዊ ማንነትና ምንነት ይልቅ ድርጊቱን ብቻውን ለማየት ነፃ እንሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም