የማይተዋወቁት ገዳይ እና ሟች

የተወለደው በደቡብ ክልል ጨንቻ ወረዳ ሙላ ቀበሌ ነው። አስተዳደጉ ከአካባቢው ልጆች ብዙም የተለየ አልነበረም። በ1985 ዓ.ም መወለዱን የሚናገረው ቀጮ ቀኔ የተማረው ሞላ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በዛው በተወለደበት ልዩ ስሙ ደቃሞ በተባለበት አካባቢ ከእኩዮቹ ጋር እየተማረ እና እየተጫወተ 8ኛ ክፍል ደረሰ።

ነገር ግን ትምህርቱን ለመቀጠል አልታደለም። እናቱ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ሕይወቱ ተመሰቃቀለ። የሚያበላው፣ የሚያጠጣው እና የሚያስተምረው አጣ፤ ራሱን ለማሸነፍ ሥራ ለመሥራት አሰበ። ነገር ግን በተወለደበት ቀዬ ውጤታማ እንደማይሆን ገምቶ የተሻለ የሥራ ዕድል አለባት ብሎ ወደ ገመታት አዲስ አበባ ከተማ አቀና።

መጀመሪያ የቅርብ ዘመዶቹን አገኝበታለሁ ብሎ ወደ ገመተበት አካባቢ ሽሮሜዳ ሄደ። በእርግጥም በአካባቢው የእርሱ የትውልድ መንደር ሰዎችን አገኘ። አንድ የአካባቢው ሰው ቀጥሮ አሠራው። ሥራውን በአግባቡ እየሠራ ደሞዝ ቢያገኝም ሕይወቱ አልተቀየረም። ሁልጊዜም ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ሆነ። ከአምስት ዓመታት የሰው ቤት ቅጥር በኋላ ከተማዋንም ሆነ ሥራውን በደንብ ሲለምድ፤ በራሱ መሥራት እንደሚችል ሲያረጋግጥ ከቅጥረኝነት ተላቀቀ። በነፃነት ራሱን ችሎ መሥራት ጀመረ።

ሠፈሩን ቀይሮ ከሽሮሜዳ ወደ አንቆርጫ ተዘዋወረ። ቀጮ ይዝናናል። ስፖርት ይሠራል፤ የግል ሥራውንም በደንብ ያከናውናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሸታ ቤት እየገባ ይቀማምሳል። ወጣትነትን አልፎ ምራቁን ሲውጥ ሥራውን አሳድጎ ትዳር መሠረተ። በበረከት ተጥለቀለቀ። ሁለት ልጆች አፈራ። በደስታ ሕይወቱን መምራት ቀጠለ። ነገር ግን ደስታው ብዙ ዘመናትን አልተሻገረም። ከቤተሰቡ ጋር መኖርም ሆነ ከባለቤቱ ጋር ተባብሮ ልጆቹን ለማሳደግ አልታደለም። የሕይወት መስመሩን የሚቀይር መጥፎ አጋጣሚ ተፈጠረ።

የስድብ ጦስ

ቀኑ ጊዮርጊስ ነው። ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ ቀጮ እንደለመደው ሲሠራ ውሎ ቤቱ ገብቶ አረፈ። ቤት ከልጆቹ ጋር መንጫጫት ሲሰለቸው፤ መቀማመስ ፈለገ። ከቤቱ በቅርብ ርቀት ላይ ወዳለው አረቄ ቤት ጎራ አለ። መሽቷልና ቤቱ ሞቅ ብሏል። ቢሆንም መቀመጫ አላጣም። ብዙዎቹ ለሁለት እና ለሦስት እየተጨዋወቱ ሲጠጡ፤ አንድ ጠጪ ግን ነጠል ብሎ ብቻውን አረቄ ሲጠጣ ተመለከተው። ቀጮ የብቸኛ ሰውዬውን ስም አያውቀውም። ‹‹ዓይቼው አውቃለሁ? አላውቅም?›› እያለ ራሱን እየጠየቀ እርሱም ብቻውን ተቀመጠ።

ቀጮ አረቄውን ይዞ መጠጣት ሲጀምር፤ ብቻውን ቁጭ ብሎ ሲጠጣ የነበረው ሰው ብድግ ብሎ ቀጮ ላይ አፈጠጠ። ቀጮ ግራ ገባው፤ እንደማይተዋወቁ እርግጠኛ ነው። ሰውዬው ቀጮ ላይ በጠጪዎቹ ፊት የስድብ ናዳ ያወርድበት ጀመር። ጠጪዎቹ ‹‹ኧረ ተው›› ብለው ከመጠጥ ቤቱ ቢያስወጡትም ብቸኛው ዳሻ ዳኮ አሻፈረኝ አለ። እየተንገዳገደ ከደጅ ወደ መጠጥ ቤቱ እየገባ መሃይም፣ ደንቆሮ እና ሌሎችም አስፀያፊ ስድብ መሳደቡን ቀጠለ። ከእርሱ አልፎ የቀጮ ቤተሰቦችን በተለይም የሟች እናቱን የሚነካ ስድብ ሲሳደብ ቀጮ ከመቀመጫው ተነሳ። ዘሎ አነቀው።

ብቻውን ቁጭ ብሎ ሲጠጣ የነበረው እና በድንገት ተነስቶ መጠጥ ቤቱን ሲያምስ የቆየው ዳሾ ቢጠጣም ለቀጮ የሚበገር አልሆነም። ቀጮን አንበረከከው፤ እግሩ ስር ጣለው። ቀጮ እልህ ይዞት ቀድሞ ቢገጥምም፤ እጁ መቋቋም ስላቃተው ከወደቀበት ተነስቶ ወደ ቤቱ ሮጠ። ሚስቱን እና ልጆቹን አላሰበም። እነርሱ እያዩት ቤት ውስጥ ያገኘውን የሽንኩርት ቢላዋ ይዞ ሮጦ ወጣ። ተንደርድሮ አረቄው ቤት ገባ። የያዘውን ቢላዋ ዳሾ ግራ እጅ ላይ ሰነዘረ። ቢሰክርም፣ በቢላዋ ቢወጋም ያልተንበረከከው ዳሾ ብድግ ብሎ ወደ ቀጮ ተጠጋ። ቀጮ ‹‹አትጠጋኝ›› እያለ በድጋሚ ቢላዋውን ዳሾ ላይ ሰነዘረ። ዳሾ የግራ ደረቱን በቢላዋ ተወጋ። ዳሾ አሁንም አላፈገፈገም በድጋሚ ሲጠጋው ቀጮ አሁንም እየሸሸ አገጩን ወጋው።

ዳሾ ዳኮ አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆኖ ቢላዋውን ለመንጠቅ በድጋሚ እየተጠጋ ለመታገል ሞከረ፤ ቀጮ ግን ከደረቱ አልፎ የግራ ሆዱን እና የቀኝ ዳሌውን እንዲሁም የቀኝ የሆድ አቃፊውን ሲወጋው ወደቀ። በመጨረሻ ቀጮ እጁን ሲመለከት በደም መጨማለቁን አስተዋለ። ዳሾ ዳኮ ብዙ አልቆየም እዛው በወደቀበት ሕይወቱ አለፈ። ቀጮ የእጁን ደም ልብሱ ላይ ጠራርጎ፤ ቢላዋውን ደብቆ ይዞ መሮጥ ጀመረ። በምሽት ከአንቆርጫ በእግሩ እየሮጠ እያለከለከ ሽሮ ሜዳ ደረሰ። ሽሮ ሜዳ ወንድሙ ያለበት ጊቢ እንደገባ ቢላዋውን ሽንት ቤት ጣለ። ደም የነካውን ልብሱን አውልቆ ጠቅልሎ ደበቀ። ምንም እንዳልተፈጠረ ለወንድሙም ሳይተነፍስ እዛው ቤት አደረ።

የፖሊስ ምርመራ

አንቆርጫ መንደር ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወንጀል መፈፀሙን ጥቆማ የደረሰው መርማሪ ፖሊስ፤ በሥፍራው ሲገኝ ተጠርጣሪው ቀጮ ጠፍቷል። የምርመራ ቡድኑ አስከሬኑን በማንሳት ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ላከ። ማስረጃ እና መረጃ ማሰባሰብ ጀመረ። በጥቆማው መሠረት ድርጊቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረውን ቀጮ ቀኔን ማፈላለግ ቀጠለ። ያለብዙ ድካም ቀጮ ወዲያው እጁን ሰጠ። ፖሊስ ቀጮ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ አደረገ።

በታኅሣሥ 24 ቀን 2015 ዓ.ም በተጠርጣሪ ቀጮ የተሰጠ ቃል ሠነድ እንደሚያመለክተው፤ ቀጮ ነዋሪነቱ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አንቆርጫ መንደር ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ተከሳሽ ቀጮ ቀኔ ቀርጎ የግል ሥራ የሚያከናውን መሆኑን ተጠቅሶ፤ የተወለደው ከአባቱ ቀኔ ቀርጉ ከእናቱ ዋሪት መንተላ እንደሆነ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ ተናግሯል።

ሞላ የአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል ተምሯል። ያገባ ሲሆን፤ የሁለት ልጆችም አባት መሆኑ በሰነዱ ተመላክቷል። ተከሳሹ ቀጮ በዝርዝር ሁኔታውን እንደተናገረው፤ ከግድያው በፊት በስም የማያውቀው ነገር ግን በመልክ ብቻ የሚያውቀው ሰው እርሱ አረቄ ቤት ሲገባ ሟች ለብቻው ተቀምጦ አረቄ ሲጠጣ ነበር። እርሱም ለብቻውን አረቄ ሲጠጣ ያለምንም ምክንያት ሟች መሳደብ ጀመረ፤ አፀያፊ ስድቦችን ቤተሰቦቹንም የሚነካ ስድብ ሲሳደብ በአረቄ ቤቱ ሲጠጡ የነበሩ ሰዎች ‹‹ተው አትሳደብ›› ብለው ከአረቄ ቤቱ ቢያስወጡትም መልሶ እየገባ ደጋግሞ መሐይም እና ሌሎችም ለመናገር የሚያስቀይሙ ስድቦችን በሰዎች ፊት ተሳደበ ብሎ የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል።

ሟች ዳሾ ሰድቦኛል በሚል ምክንያት በሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ አንገቱን የግራ ጎኑን፣ ሆዱን እና ደረቱን እንዲሁም መቀመጫው አካባቢ በመውጋት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርገሃል ተብሎ በንባብ የቀረበለትን ካዳመጠ በኋላ የወንጀል ዝርዝር ድርጊትም ፈፅሜያለሁ ብሎ ማመኑም የእምነት ክህደት ቃሉ ላይ ሠፍሯል።

ድርጊቱን የፈፀመበትን ምክንያት ሲያስረዳ፤ ‹‹በስድቡ ተበሳጭቼ እንጋጠም ብዬ ተነሳሁ። ነገር ግን ስንያያዝ እግር ኳስ ስጫወት እጄ ተሰብሮ ስለነበር መቋቋም አቃተኝ። ስለዚህ ተጎዳሁኝ። ጉዳቴን ይዤ መኖሪያ ቤቴ ከአረቄ ቤቱ ቅርብ በመሆኑ ወደ ቤት ገብቼ የሽንኩርት ቢላዋ ይዤ ሔድኩኝ። እንደፈለግኩት ሟች ዳሾን ፊት ለፊት አገኘሁት፤ በድጋሚ ተጋጠምን። በያዝኩት ቢላዋ ግራ እጁን ወጋሁት። መሸሽ ብፈልግም ሟች ግን ደጋግሞ መጠጋቱን ቀጠለ። ደጋግሜ ቢላዋውን በመሰንዘር የተለያዩ ቦታዎች ላይ ወጋሁት።

…….ሟች ሲወድቅ እጄን ሳይ በደም ተጨማልቋል። ስለዚህ ደንግጬ ቢላዋውን እንደያዝኩ መሮጥ ጀመርኩ። የሮጥኩት ቀድሞ እኖርበት ወደ ነበረው ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው። ወንድሜ ቤት ደርሼ ቢላዋውን ሽንት ቤት ከተትኩት። ደም የነካውን ጃኬቴን አውልቄ እጄን ጠራርጌ አስቀመጥኩት። ›› ብሎ የነበረውን ሁኔታ በሙሉ ለመርማሪ ፖሊሱ ተናገረ። የፖሊስ መርማሪ ቡድንም የሰው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃውን አቀናጅቶ ለዐቃቤ ሕግ አቀረበ።

ዐቃቤ ሕግ

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመዝገብ ቁጥር 759/15 የመጣለትን የክስ ማስረጃ በአግባቡ ከቃኘ በኋላ፤ ተራ የሰው ግድያ ወንጀል ብሎ በመዝገብ ቁጥር 3863/15 ለፍርድ ቤት አቀረበ። የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ባስቀመጠው የክስ ዝርዝር ላይ እንዳመለከተው፤ ተከሳሽ ቀጮ ቀኔ ቀርጎ ሰው ለመግደል አስቦ፤ በታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አንቆርጫ መንደር ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሟች ዳሾ ዳኮን በቢላዎ አገጩን፣ የግራ ደረቱን፣ የግራ ሆዱን፣ የቀኝ ዳሌውን እና የቀኝ የሆድ አቃፊውን በመውጋት ሆዱ እና ደረቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል። በመሆኑም በፈፀመው ተራ የሰው ግድያ ወንጀል ከሳሽ የፌዴራል አቃቤ ሕግ ተጠርጣሪ ቀጮ ቀኔ ለፍርድ መቅረብ አለበት ሲል የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር አቅርቧል።

ከሰነድ ማስረጃዎቹ መካከል አንዱ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የምርመራ ውጤት ነው። ይህ ሰነድም እንደሚያሳየው ሟች ዳሾ ደረቱን የግራ ሆዱን የቀኝ ዳሌውን እና የቀኝ የሆድ አቃፊውን በመውጋቱ ሕይወቱ አልፏል። በክስ ዝርዝሩ ላይ ተከሳሽ ድርጊቱን መፈፀሙን የእምነት ክህደት ቃሉን በሰጠበት ወቅት ማመኑን አመላክቷል።

የፌዴራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ 1ኛ ምድብ ችሎት በሕዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሹን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በሰጠው ውሳኔ፤ ተከሳሽ ቀጮ ቀኔ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You