በክልሉ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ:- በአማራ ክልል ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በክልሉ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥርን ለማሳደግ ሰፊ ተሠርቷል፡፡ በዚህም በክልሉ ከ12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በጤና መድህን ታቅፎ አገልግሎት እያገኘ ነው፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ተገልጋዮች የምዝገባና እድሳት አገልግሎት የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ 218 ሺህ 406 ያህሉ በአዲስ የተመዘገቡ የጤና መድህን አባላት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ሁለት ሚሊዮን 612 ሺህ 461 አባዎራዎች የነባር የአባልነት ዕድሳት አገልግሎት ያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

አገልግሎቱንም በሁሉም በክልሉ ዞኖች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በስፋት የተሠራ መሆኑን ሲስተር ክሽን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመትም በወልቃይት ጠገዴ ዞን እና በጠለምት ባሉ ሁሉም ወረዳዎች የጤና መድህን አገልግሎት ለማስጀመር ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ለ578 ሺህ 661 መክፈል ለማይችሉ አባዎራዎች በክልሉና የወረዳው መንግሥት ወጪ በመደጎም አባል እንዲሆኑ የተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡ ለዚህም ከ513 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ ተደርጓል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ከከፋይ የጤና መድህን አባላት ብቻ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ብር ተሰብስቧል ያሉት ኃላፊዋ፤ ከተናጥል ድጎማ እና የፌዴራል ጠቅላላ ድጎማ በአጠቃላይ ከሶስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን፤ በጤና ተቋማት የአገልግሎት ሙሉ አለመሆን፤ የህክምና የግብዓት ዕጥረት እና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ድጋፍ ለማድረግ አለመቻል ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ተግዳሮቶቹን ለመፍታት ከአመራሩ ጋር በመነጋገር የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር ማወያየት፤ ለሕዝቡ ግንዛቤ መፍጠር፤ በየአቅራቢያው ባለው ባንክ ክፍያ በመክፈል መታወቂያ እንዲታደስላቸው የማድረግ ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመት በክልሉ ከአራት ነጥብ አምሥት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አዲስ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላትን ለማፍራት የታቀደ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በጤናው ላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በመረዳት ማህበረሰብ አባል መሆን ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You