ሱስ በጣም ውስብስብ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሱስ የመያዝ ምክንያቶችም እንደ ሰው፣ እንደ አካባቢውና እንደ አኗኗራችን ሊለያይ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን ሰዎችን ለሱስ ይዳርጋሉ ወይም ተጋላጭ ያደርጋሉ ተብለው ከሚታመንባቸው ምክንያቶች መካከል ለጭንቀትና መፍትሔ የማጣት ስሜት መሰማት ነው፡፡ ለችግር ወይም ለጭንቀት ቀጥተኛ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ሱስን እንደ ጊዜያዊ መጠለያ መጠቀም፤ እንደ አጋጣሚ ተጀምሮ ራስን ማላቀቂያ መንገዶችን አለማወቅ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ፣ ለራስ ያለ ክብር ወይም ስለራስ ያለ አመለካከት ዝቅ ማለት፣ የአቻ ግፊት፣ በአቻዎች ተቀባይነትንና ተወዳጅነትን መሻት ወዘተ… የሱስ መነሻ ምክንያቶች ሊሆኑ ከሚችሉ ሁኔታዎች መካከል ይገኙበታል።
በኢትዮጵያ ከሕዝብ ቁጥሯ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው ወጣቱ በተለያዩ የሱስ ዓይነቶች ማለትም በጫት፣ በሲጋራ፣ በመጠጥና መሰል የሱስ ዓይነቶች ተዘፍቆ እንደሚገኝ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህም ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደምታጣ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።
ጋዜጠኛና የፀረ ሱስ አክቲቪስት የሆነው ወጣት አሸናፊ ግዛው ወይም በቅፅል ስሙ (አሼ ታለንት) ተወልዶ ያደጋው በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ከተማው ሀዋሳ ተከታትሎ ለከፍተኛ ትምህርቱ በትውልድ ከተማው ሀዋሳ ወደሚገኘው ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በማቅናት በቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
ከ13 ዓመታት በላይ ለሚሆኑ ጊዜያት በፀረ ሱስ አክቲቪስትነቱ የሚታወቀው ወጣት አሸናፊ ወደዚህ ሥራው እንዲገባ መነሻ ምክንያት ስለሆነው ነገር ሲናገር፤ “ልጅነቴን ያሳለፍኩበት አካባቢ የተለያየ ዓይነት የሱስ ልምምዶች የሚዘወተሩበት ከመሆኑ ባሻገር ወላጅ አባቴም የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ነበር፤ ይህ በልጅነት ያሳለፍኩት ሕይወት የፈጠረብኝ ቁጭት ነው ሱስን አምርሬ እንዲጠላና እንዲታገል ምክንያት የሆነኝ፡፡” ይላል።
“በተለይ ሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት የተለያየ ስያሜ ተሰጥቷቸው የሚከበሩ በዓላት ምን ያህል ወጣቶች በአፍላ ዕድሜያቸው ወደ ሱስ እንዲገቡ ምክንያት እንደሆናቸው ተረዳሁ፤” የሚለው ወጣት አሸናፊ፣ ይህንኑ ለመከላከል ከልጅነቱ ጀምሮ የተለያየ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ ተነግሮ፤ ሱስ በቤተሰቡ ውስጥ ያሳደረውን ተፅዕኖ፣ ወጣቶች ላይ እያመጣ ያለውን አደገኛ ችግር ለመከላከል ወደ ፀረ ሱስ ሥራው በማተኮር ሙሉ ሕይወቱን እንዲሰጥ ምክንያት እንደሆነው ይገልጻል።
አሼ ታለንት፣ ‘ፕሮፋይል ሚዲያና ኮሚኒኬሽን’ የተባለ ኤዲቶሪያል ፖሊሲውን የጸረ-ሱስ ቅኝት ያደረገ የግል የሚዲያና ኪነጥበብ ድርጅት መስርቶ ከ13 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ የቢሮ መሠረቱን ሀዋሳ እና አዲስ አበባ አድርጎ በመሥራት ላይ የሚገኝ ወጣት ነው፡፡ ወጣቱ፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ ሱሰኝነትን ለመከላከል ወሳኝ ስለመሆኑ ይናገራል።
ላለፉት 13 ዓመታት ከሱስ፣ አደንዛዥ ዕፅና አደንዛዥ አስተሳሰቦች ነፃ ማህበረሰብ የመፍጠር ራዕይ አንግቦ ሥራውን የሚሠራው ወጣት አሸናፊ በዋናነት አራት መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ይናገራል።
የመጀመሪያው የሰው ልጅ በሰውነቱ ያገኘውን ጥበብና ፀጋ ሱስ ምን ያህል እንደሚጎደው በማሳየት ፈጣሪ የሰጠውን አቅም ሳይረዳ እንዳያልፍ (ሳይንሳዊ ተሰጥኦ አጋዥ መፍትሔ) በሚል መርህ በተለይ ወጣቶች ያላቸውን ጥበብ ተጠቅመው ለራሳቸው ሆነ ለማህበረሰቡ በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሰራ ይናገራል።
“ሰው ጥሪውን ሲያውቅ አጉል ነገር ውስጥ አይገባም” የሚለው ወጣት አሸናፊ፤ ገንዘብ በማውጣት እንጂ በነፃ በማይገኝ ሱስ ውስጥ ገንዘቡን ከፍሎ እራሱን የሚጎዳው ጥሪውን ባለማወቁ የተነሳ ነው ይላል፡፡ በመሆኑ ይህንን ከግምት በማስገባት ግንዛቤ ለመፍጠር ለአብነት የአሼ ታለንት የጸረ-ሱስ የቁንጅና ውድድር እና ፋሽን ሾው በመዘጋጀት ወጣቶች ያላቸውን ነገር ማስተዋወቅ እንዲችሉ ዕድል የመፍጠር ሥራ እንደሚሰራ ያስረዳል።
በሁለተኛ ደረጃ (አዎንታዊ ዓለም አቀፋዊነት) በሚል መርህ ዘመን አመጣሽ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምክንያት በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ መነሻ ወደ ሱስ የሚገቡ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው። አንድ የሚያደንቁት ሰው ሲያደርግ ያዩትን እነርሱም ለመተግበር ይሞክራሉ፡፡ ይህ በተለይ ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ችግሩ እየጎላ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ወጣቱ፣ ዓለም አቀፋዊነትን በበጎ ነገር እንረዳ በሚል ወጣቶች የሌሎች ሰዎችን መጥፎ የሕይወት ልምድ ተካፋይ እንዳይሆኑ ጥረት እንደሚያደርግ እንደሆነ ይገልጻል።
በሶስተኛ ደረጃ (የአስተሳሰብ ልማትና ኢትዮጵያዊ ከፍታ) በሚል መርህ ሥራዎችን እንደሚሰሩ የሚናገረው ወጣት አሸናፊ፣ የዚህ ምክንያትም ሰው ነገሮችን በበጎነት መመልከት የሚችለው ያለው አመለካከት የጠራ ሲሆን ብቻ በመሆኑ ይህንን ለማሳደግ ወጣቶች ሱሰኝነትን በተመለከተ ስለጎጂነቱ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ የሚዲያ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ያብራራል።
ሱስ በባህርዩ የአዕምሮ ጤና ችግር ጭምር እንደሆነ የሚናገረው አሸናፊ፣ አስተሳሰብን የሚያደንዝ፣ አመለካከትን የሚያበላሽ፣ ለነገሮች ያልተገባ ዕይታ እንዲኖረን የሚያደርግ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገር ዕድገት ላይ የሚኖረው አሉታዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች በኪነጥበብ ድርጅቱ አማካኝነት እንደሚሰራ ይናገራል።
“የተማርኩት ሀገርና ማህበረሰብ ለማገልገል ነው፡፡” የሚለው ወጣት አሸናፊ፣ እስከ አሁን በቆየባቸው የፀረ ሱስ ሥራዎች፤ ከ20 በላይ የጸረ-ሱስ ሩጫ፣ የእግር ጉዞና የጎዳና ላይ ትምህርታዊ ትርዒት፣ ከ13 በላይ ዓመታዊ የጥንዶች ፌስቲቫል፣ ከአንድ ሺ 500 በላይ የቀጥታ ሥርጭት የአሼ ታለንት ፕሮፋይል የጸረ-ሱስ ቅኝት የሬዲዮ ዝግጅት፣ ከ30 በላይ የቲቪ ፕሮዳክሽኖች፣ ሶሻል ሚዲያን ለበጎ አላማ የሚያነሳሳ በማህበራዊ ሚዲያ በርካታ የጸረ-አደንዛዥ አስተሳሰብ መልዕክቶችን ጨምሮ ከ15 ሺ በላይ በራሪ የመልዕክት ወረቀቶችን ማሰራጨት ተችሏል፡፡ እንዲሁም በተለያዩ የሕትመት ሚዲያ አምዶች ላይ ጽሑፎች በማዘጋጀት ወጣቱን ከተለያየ ሱስ ለመታደግ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ውስጥ ለተካተተው በብሮድካስት ሚዲያ አልኮል ምርት ማስተዋወቅ፣ ከትምባሆ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ላለው ሕግ መውጣት የራሳችንን ድርሻ ተወጥተናል የሚለው ወጣት አሸናፊ፤ በአሁን ሰዓት በመንግሥትና በሕዝብ እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች ተቋማትና የማህበረሰብ ክፍሎች ከሱስና አሉታዊ የመጤ ባሕሎች/ልምዶች ጋር ተያይዞ ላለው ትኩረት የአሼ ታለንት ሚና ከፍተኛ ነው። ለዚህም ከተለያዩ አካላት የተሰጡት ዕውቅናዎች ማረጋገጫ በመሆናቸውን ይጠቅሳል።
“አደንዛዥ ዕፆችና አስተሳሰቦች በሀገር ላይ እያሳደሩት ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡” የሚለው ወጣት አሸናፊ፣ “ስለዚህ ማህበረሰቡ ስለጉዳዩ የነቃ አመለካከት ሊኖረው ይገባል፤ መንግሥትም እንዲሁ ከሽብርተኝነት ቀጥሎ ለሀገር ደህንነት አደጋ የሆነውን ሱሰኝነት ለመከላከል ቁርጠኝነት ሊኖረው ይገባል፡፡” ይላል።
“ስለ ሱስ አደገኛነት ስናወራ ፈተና የሆነብን ሃይማኖታዊ አጀንዳ የምናነሳ የሚመስለው ሰው አመለካከት ነው፡፡” የሚለው አሸናፊ፣ “ይህ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። በወጣቱ በኩል ደግሞ ሱስ በቁም የሚገድል በሽታ መሆኑን ለማስረዳት ጥረት በምናደርግበት ወቅት እኛን ነገሮች የማይገቡን በተለምዶ ቋንቋ (ፋራ) አድርጎ በመውሰድ ሱሰኝነትን የዘመናዊነት አንዱ መገለጫ አድርጎ የመውሰድ ችግር አለ፤ ይህ እጅግ አደገኛ የሆነና መቀረፍ ያለበት አመለካከት ነው፡፡” ሲልም ያክላል።
“ሱሰኛ ባለበት ሰላም አይኖርም፡፡” የሚለው ወጣት አሸናፊ፣ በርካታ የወንጀል ልምምዶች ሱስን ተገን በማድረግ የሚመጡ ናቸው። አሁን በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ወንጀሎች ሱስና አደንዛዥ ዕፅ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ያስረዳል።
“ሁላችንም ስለችግሩ እኩል መረዳት ሊኖረን። ሀገር የሚለውን ትልቅ ነገር በማስቀደም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ካልተቻለ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፤ ስለዚህ በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ወጣት ለማዳን መሥራት አለባቸው በማለትም ለጉዳዩ አጽንኦት ይሰጣል፡፡
“በሀገራችን አሁን ባለው ሁኔታ የማይጠጣና የማይቅም ሞኝ፤ በተቃራኒው በሱስና አደንዛዥ ዕፅ የተጠመደ ግን የነቃ ወይም በተለምዶ (አራዳ) ተደርጎ ይወሰዳል፡፡” የሚለው ወጣት አሸናፊ፣ ይህ አደገኛ ልምምድ መቀረፍ አለበት፤ በሱስ ደንዝዞ እራሱን ያላገኘው እንጂ ከሱሰኝነት የፀዳ ሰው (ፋራ) ሊሆን አይችልም፡፡” ይላል።
ማህበረሰብና ሕዝብ የሚሳተፍበት እንቅስ ቃሴ ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል የሚናገረው ወጣት አሸናፊ፣ በኢትዮጵያ ሱስና አደንዛዥ ዕፅ መከላከል ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ ነው። ስለዚህ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደመጣናቸው አዎንታዊ ለውጦች ሁሉ በፀረ ሱሰኝነት እንቅስቃሴም በጉዳዩ ክብደት ልክ ትኩረት በመስጠት መረባረብ እንደሚገባ ይናገራል።
“ኢትዮጵያ የወጣት ሀገር ናት፡፡” የሚለው አሸናፊ፣ የወጣት ሀገር አሁን ምን እንደምትመስል እያየን ነው። በየመንደሩ ትውልዱን የማያንጽ እንደመጠጥ እና የጭፈራ ቤቶች፣ ማደንዘዣ ማዕከላት ተበራክተዋል፤ ይህ የሚታይ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት እና ማህበረሰቡ በጉዳዩ አንገብጋቢነት ልክ ትኩረት ሰጥተው ችግሩን ለመቀነስ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ይላል።
ሱሰኝነትና የአደንዛዥ ዕፆች አጠቃቀም የሀገር ህልውና አደጋ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ልክ መግባባት ካልተፈጠረ የተወሰኑ ሰዎች አጀንዳና የዘመቻ ሥራ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ በዚህ ደግሞ ተገቢውን ውጤት ማምጣት አይቻልም ይላል።
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ የራሷ በቂ ችግሮች እንዳሉበት የሚናገረው አሸናፊ፣ እያንዳንዱ ሰው የመፍትሔ አካል መሆን አለበት፤ የፀረ ሱስ እንቅስቃሴን በተመለከተ በተለይ ወጣቱ ቢያንስ ሱሰኛ ባለመሆኑ ለሀገር ተጨማሪ ሸክምና ችግር ባለመሆን የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ያስረዳል።
ሳይቅሙ መንቃት፤ ሳይጣጡ መዝናናት፤ ይቻላል የሚለው አሸናፊ፣ ሱስና መዝናኛን ቀላቅሎ ማየት እንዲሁም ሱስና ሃይማኖትን ቀላቅሎ ማየት ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሱስ ትውልድ ገዳይ የሀገር ችግር መሆኑን መገንዘብና እራስን ከዚህ ባርነት ነፃ በማድረግ ጠቃሚ ዜጋ መሆን ይቻላል ይላል።
ዘወትር ማክሰኞ እና ሐሙስ ከምሽቱ ከሁለት ሰዓት እስከ ሶስት ሰዓት በኤፍ.ኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ ሬዲዮ ‘አሼ ታለንት ፕሮፋይል’ የተሰኘ ትኩረቱን ፀረ ሱስና አደንዛዥ ዕፅ ላይ ያደረገ የመረጃና የመዝናኛ የሬዲዮ ዝግጅት አለው። የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ የሆነው ወጣት አሸናፊ፣ በዚህ ሥራው በወጣቶች ላይ በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራል።
ወጣት አሸናፊ በመጨረሻም ባስተላለፈው መልዕክት፤ አንድ የኢትዮጵያ ወጣት በዓለም ላይ ያለን ወጣት ማየት አለበት፤ ለምሳሌ አንድ አሜሪካዊ ወጣት ዓላማው ናሳ መግባት ከሆነ፤ ኢትዮጵያዊ አቻው ዓላማው የጫት ማሳ መሆን የለበትም፤ ወጣትነት ደስ የሚል ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ይህንን ወርቃማ የዕድሜ ዘመኑን ተጠቅሞ ነገውን ብሩህ ለማድረግ ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ያስገነዝባል። ሱሰኝነትን የዘመናዊነት መገለጫ አድርጎ መውሰድ አላዋቂነትን የሚያሳይ ነውና ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው ብሏል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም