ለዓባይ ግድብ ግንባታ እስካሁን 20 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡- የዓባይ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 19 ቢሊዮን 942 ሚሊዮን 519 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ አንድ ቢሊዮን 712 ሚሊዮን 183 ሺህ 820 ብር በላይ መሰብሰቡም ተጠቁሟል።

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዓባይ ግድብ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የግድቡ መሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 19 ቢሊዮን 942 ሚሊዮን 519 ሺህ 421 ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 18 ቢሊዮን 604 ሚሊዮን 685 ሺህ 725 ብሩ ከሀገር ውስጥ የቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ አንድ ቢሊዮን 455 ሚሊዮን 953 ሺህ 251 ብር ከዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ እንዲሁም አንድ ቢሊዮን 9 ሚሊዮን 325 ሺህ 835 ብሩ ደግሞ ከልዩ ልዩ ገቢዎች መገኘቱን አስታውቀዋል።

በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ብቻ አንድ ቢሊዮን 712 ሚሊዮን 183 ሺህ 820 ብር በላይ መሰብሰቡን የገለጹት አቶ ኃይሉ፤ አንድ ቢሊዮን 488 ሚሊዮን 849 ሺህ 199 ብር በላይ ከሀገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ 17 ሚሊዮን 321 ሺህ 246 ብሩ ደግሞ ከዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ 132 ሚሊዮን 373 ሺህ 92 ብር ደግሞ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልእክት የተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 73 ሚሊዮን 278 ሺህ 133 ብር በላይ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስጦታ አካውንት ገቢ የተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ 362 ሺህ 150 ብር ደግሞ በተለያየ ገቢ የተገኘ መሆኑን አንስተዋል።

የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ እየተገነባ መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዓባይ ግድብ ግንባታ መሠረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መቀመጡ ይታወሳል። የግድቡ የውሃ ሙሌት ላለፉት አራት ዓመታት በስኬት ተከናውኗል።

ፋንታነሽ ክንዴ

ሐምሌ 19 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You