በክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 700 ሺህ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው

አዲስ አበባ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት 700 ሺህ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆኑን የክልሉ መንግሥት ገለጸ። አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የክልሉ ነዋሪዎችም በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።

የክልሉ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ አለሙ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በዘንድሮ ክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 14 ዘርፎችን በመለየት ወደ ሥራ ተገብቷል።

በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ 700 ሺህ ወጣቶችና በጎ ፍቃደኛ ማህበረሰቦች እየተሳተፉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ የሺዋስ፤ በሚሰጠው አገልግሎት አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ 978 የአቅመ ደካሞች እና የአረጋውያን ቤቶች ግንባታ እና እድሳት እንደሚደረግም ኃላፊው ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ እና የወባ መከላከል ላይ የግንዛቤ ትምህርት መስጠት በመርሃ ግብሩ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከወጪ እንደሚያተርፍ ገልጸዉ፤ ስራው በከፍተኛ ትኩረት ዐቢይ እና ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሞለት በየቀኑ እየተገመገመ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራው ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችም በከፍተኛ ተነሻሽነት እየተሳተፉ መሆኑን አብራርተዋል።

የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ክልሉ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል። የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር የ250 ሺህ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

የቤት እድሳት እና ግንባታ ሥራ ላይ በዘንድሮ ዓመት ከአንድ መቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን አስረድተዋል። በአረንጓዴ ዐሻራ የሚተከሉ ችግኞች ቁጥርም በከፍተኛ  ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል።

የተሳታፊ ወጣቶች ቁጥርም እቅዱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሺህ እንዲጨምር መደረጉን አመላክተዋል።

የበጎ ፍቃድ ሥራ ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት አቶ የሺዋስ፤ ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በበጎ ስራው ተሳትፈው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እና ለሀገር ልማትና ግንባታ አበርክቶ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

መዓዛ ማሞ

ሐምሌ 19 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You