ምክክሩ፤ የሚያስተባብሩ አጀንዳዎችን እንድንለይ እድል ሰጥቶናል ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፦ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የተደረገው ምክክር የሚያፎካክሩ አጀንዳዎችን ብቻ ሳይሆን የሚያስተባብሩ አጀንዳዎችን እንድንለይ እድል ሰጥቶናል ሲሉ ኢዜማ እና ትዴፓ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በሀገራዊ ስትራቲጂያዊ ጉዳዮች ላይ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ባካሄዱት ምክክር የተሳተፉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ምክክሩ የሚያፎካክሩ አጀንዳዎችን ብቻ ሳይሆን የሚያስተባብሩ አጀንዳዎችን ለመለየት ዕድል የሚሰጥ ነው።

ሀገር የፖለቲካ ሥሪት ነው ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ፤ ፖለቲካ ደግሞ ብዝሃ ሃሳብና አመለካከቶች የሚንጸባረቁበት መሆኑን ጠቅሰው ስለዚህ የተለያዩ አመለካከቶችና ብዝሃ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት መድረክ መፈጠሩ ሊበረታታ የሚገባ ነው ብለዋል።

በየጊዜው የተለያዩ ሃሳቦች የሚደመጡበት መድረኮች መፍጠር አካታች የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት ይጥላል ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደመጡበት መድረክ ካገኙ ሌሎች አማራጮችን ከማየት ይልቅ በሃሳብ የበላይነት የሚያምኑ ይሆናሉ ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብ የሚደመጡበት መድረክ ከሌለ የአመጽ በር እንዲከፈት እና ሃሳቦች በኃይልና በጉልበት እንዲንጸባረቁ እድል ይፈጥራል ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ እንዳይሆን ፓርቲዎች ሃሳባቸውን እያነሱ፣ መከራከር ባለባቸው ጉዳዮች እየተከራከሩ እና መተባበር ባለባቸው እንዲተባበሩ የሚያስችል የውይይት መድረክን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ትውልዶች ያሳለፈችው ፖለቲካ በሁሉም ነገር ልዩነት መፍጠርና መጣላት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህም መውጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሀገር ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደህንነት፣ የሰላም ጉዳይ፣ የተቋማት ግንባታ እና መሰል ሥራዎች በአንድ ኃይል ወይም ቡድን የሚሠሩ ሥራዎች አለመሆናቸውን መገንዘብ እንደሚገባም ተናግረዋል። በዚህም የምንመኛት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አመራር አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በሀገራዊ ስትራቲጂያዊ ጉዳዮች ያደረጉት ውይይት በአግባቡ ልንጠቀምበት የሚገባ ነው ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ባህል የሚያስተባብሩና የሚያለያዩ ጉዳዮችን አንድ የማድረግ እሳቤ ነበር ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ አሁን ላይ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ምክክር መጀመሩ እንደሚበረታታ ጠቁመዋል።

የሚያለያዩ ጉዳዮችን ደግሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከር መጀመሩም በመልካም የሚታይ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህ ጅማሮ ቢሆንም በቀጣይ ጊዜያት እንደሀገር ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ያስችላል ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ እንደሀገር ሲንከባለሉ ለመጡ የጋራ የፖለቲካ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማበጀት እድል ይፈጥራል። ይህም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።

ምክክሩም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ገዢው ፓርቲ ቁርጠኛ መሆን አለበት ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የተደረገው ምክክር የሚያፎካክሩ አጀንዳዎችን ብቻ ሳይሆን የሚያስተባብሩ አጀንዳዎችን እንድንለይ እድል ሰጥቶናል ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

ሐምሌ 19 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You