የአዕምሮ እድገት ውስንነትን በሚመለከት የተለያዩ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ቢኖሩም በሀገር አቀፍ ደረጃ በቂ ጥናት ባለመደረጉ የችግሩን ስፋት በሚገባ ማረጋገጥ አልተቻለም። ሆኖም ከሚታየው እውነታ በመነሳት የችግሩን ስፋት መገመት አያዳግትም። በተለይ በማህበረሰቡ በኩል ባሉ ክፍተቶች የተነሳ ለአዕምሮ እድገት ውስንነት መስፋፋት መንስኤ የሚሆኑ የጤና፣ ማህበራዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ባህላዊና ሌሎችም ችግሮች ከበለፀጉት ሀገራት ይልቅ በኢትዮጵያ እጅግ የበዙ መሆናቸው ግልፅ ነው።
የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ዜጎች የትምህርት ወይም ሥልጠና ተቋማት ተደራሽነት፣ ተሳትፎ እንዲሁም በተቋማትና በህብረተሰቡ የሚደረግላቸው ድጋፍና እንክብካቤ አነስተኛ እንደሆነም ይታመናል። በአንዳንድ አካባቢዎች በማህበራዊ መገለል ምክንያት በቤት ውስጥ ተወስነው እንዲኖሩ ስለተገደዱ ለተለያዩ የጤናና ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ ሲሆኑ፣ ሲገለሉና ልዩ ልዩ በደሎች ሲደርሱባቸው ይታያል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት፣ ህብረተሰቡ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያደርግ ስለሚችለው ድጋፍ በቂ ግንዛቤ አለመኖር እንደሆነም ይገለፃል።
ከዚህ ክፍተት በመነሳት በተለይ መምህራን፣ አሠልጣኞች፣ አመቻቾች፣ የትምህርት ባለሙያዎች ስለ አዕምሮ እድገት ውስንነትና ምንነት በቂ እውቀት፣ ክህሎትና አዎንታዊ የአመለካከት ለውጥ ኖሯቸው ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ለማስቻል ላለፉት ሰላሳ ዓመታት እየሠሩ ካሉ ተቋማት ውስጥ አንዱ ፍቅር ኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር ነው።
ፍቅር ኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር የተመሠረተው ከዛሬ 29 ዓመት በፊት በ1987 ዓ.ም ሲሆን ሥራውን የጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። በጊዜው ማህበሩ ሥራውን ሲጀምር በስምንት ክፍሎች ነበር። በሂደት ቅርንጫፎቹን ወደ አስራ ሰባት በማሳደግ ከ15 ሺህ በላይ አባላትን ማፍራት ችሏል። ማህበሩ ሲቋቋም ዋነኛ ዓላማውም ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር በተያያዘ ለወላጆች፣ ለመንግሥት አካላትና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ብሎም ለማህረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነበር።
በአሁኑ ጊዜም ማህበሩ የአካቶ ትምህርት እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ጥረት ያደርጋል። የአዕምሮ አድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆችን የማፈላለግና ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ያበረታታል። ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ በግንዛቤ እጥረት፣ አገልግሎቱን ባለማወቅ፣ በፍርሃትና በማፈር ወላጆች ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ልጆቻቸውን ከቤት ስለማያስወጧቸው በዚህ መነሻነት ማህበሩ ወላጆችን በማግባባት የሞያ ሥልጠና ማዕከል ከፍቶ ልጆቹ የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ ያደርጋል።
ከዚህ ባለፈ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ይሰጣል። በኢኮኖሚ ለማብቃት ለወጣቶችንና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ወላጆች የሥራ እድል ይፈጥራል። የወላጆችን አቅም የማሳደግ፣ የመረጃ ተደራሽነት በተለይም በሥነ ተዋልዶ ጤናና ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ ይሠራል። ማህበሩ ከአካቶ ትምህርት ጋር በተያያዘ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚሠራ ሲሆን ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የነበረውን አንድ ብቻ የአካቶ ትምህርት ወደ አስራ አምስት ከፍ እንዲል የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል።
በዚህም እስካሁን ድረስ ከ500 በላይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች በተለያዩ ሙያዎች እንዲሠለጥኑ አድርጓል። ከ200 በላይ ለሚሆኑ ወላጆች የሥራ እድል ፈጥሯል። ይህንኑ ለማሳካትም ከኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ይሠራል። ከሌሎች የአካል ጉዳት ማህበራት ጋርም በቅንጅት ይሠራል። ከሁሉ በላይ በርካታ በየቤቱ ተደብቀው ያሉ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ከቤት እንዲወጡ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በሌላ በኩል ማህበሩ ለመምህራን ከአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን ከመምህራን ባለፈ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለፍትህ አካላት፣ ለሚዲያዎች እና ለሌሎችም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ይሠራል። በተመሳሳይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ወጣቶች የመብት ተሟጋች እንዲሆኑ ተከታታይ ሥልጠናዎችን ይሰጣል። በተጨማሪም በማህበሩ የቦርድ አባልነት እንዲመረጡም አድርጓል። የቡና ጠጡ ፕሮግራም ቤት ለቤት በማዘጋጀት ማህረሰቡን የማነቃቃት ሥራም ሠርቷል።
በቀጣይም ማህበሩ የራሱ የሆነ የገቢ ማስገኛ ህንፃ እንዲኖረው አቅዶ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በተለያዩ መድረኮች ወጣቶችን ወደፊት በማውጣት የመብታቸው ተከራካሪ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል። የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች የሥራ እድል እንዲያገኙ አበክሮ ይሰራል። ‹‹Disability Act›› በኢትዮጵያ እንዲፀድቅና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሌሎች አካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር በመሆን የመሥራት ውጥን አለው። ወላጆችን በሥልጠና አቅማቸውን በማሳደግ ከመንግሥት ጋር በመሆን ለልጆቻቸው መብት እንዲሠሩ ማድረግ፣ በመንግሥት ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ከአካቶ ትምህርት አብሮ እንዲሠራበት ማድረግና ሌሎችም እቅዶች ይዟል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም