«በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ» አገልግሎት አንሰጥም የሚሉ ተቋማት የወንጀል ኃላፊነት አለባቸው

አዲስ አበባ፦ “በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ” አገልግሎት አንሰጥም የሚሉ ተቋማት የወንጀል ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል ሲል የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሕግና ፖሊሲ ክፍል ኃላፊ ጋብሬላ አብርሃም ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ 1284/2015 በግልጽ ባስቀመጠው ድንጋጌ ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተቋማት የብሔራዊ መታወቂያን በመጠቀም ሊሰጡ እንደሚገባቸው ተደንግጓል።

ይህ ድንጋጌ በሀገሪቱ ከፍተኛ ሕግ አውጪ አካል በሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተደነገገ አዋጅ ነው ያሉት ጋብሬላ፤ ይህንን የማይተገብሩ ግለሰቦችና ተቋማት የወንጀል ተጠያቂና ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ሊያውቁ ይገባል። ሕግን አክብሮ መሥራቱ ሊዘነጋ አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ግለሰቦች አገልግሎት የማግኘት መብት አላቸው። ይህንን መብታቸውን ትልቅ ሀገራዊ ጠቀሜታ ባለው በብሔራዊ መታወቂያ በኩል ሊያገኙ ይገባል። ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት በተለይም የመንጃ ፈቃድ ትምህርት የሚሰጡ ተቋማት በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት አንጠቀምም የሚሉ አሉ።

ይህ ሁኔታ ግለሰቦች በብሔራዊ መታወቂያ ዙሪያ አሉታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ ይህንን የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ያሉት ጋብሬላ፤ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እና ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን አዋጅ የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ሳይወጣ በፊት የተደነገገ በመሆኑ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች በብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት አንሰጥም ማለታቸውን ገልጸው፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ከባለሥልጣኑ ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፤ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ አመራሮች እና የክፍል ሃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አከናውኗል። የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር በፍትህ ዘርፍ ማንነትን በማጭበርበር የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከመከላከል አንፃር ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ፋይዳ” ዘመናዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን በመገንባት ማንነትን የማረጋገጥ ሂደት ቀልጣፋ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ያደርጋል ያሉት ኃላፊዋ፤ በሀገሪቱ ዘመናዊ እና ማንነትን በዲጂታል መንገድ በማረጋገጥ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል የመታወቂያ ሥርዓት ተገንብቶ በተጠናከረ መልኩ ትግበራ ላይ እየዋለ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You