የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እያደገ መጥቷል

– የልማት ድርጅቶቹ ሶስት ትሪሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት አፍርተዋል

አዲስ አበባ፦ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እያደገ መምጣቱን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር አስታወቀ። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት ሶስት ትሪሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን ገልጿል።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም እና ተወዳዳሪነት እንዲሻሻል ማድረግ፣ ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደርና የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓትን መዘርጋት፣ የልማት ድርጅቶቹ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የሚመሩበትን ሥርዓት መዘርጋት ከሚተገብራቸው ተግባራቶቹ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። በዚህም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እያደገ መጥቷል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት 15 በመቶ እንደሚሸፍኑ ገልጸው፤ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከዚህ የበለጠ ድርሻ እንዲያበረክቱት በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የሚገኙ አጠቃላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሶስት ትሪሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት ማፍራታቸውን የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ በአስተዳደሩ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት ከአንድ ነጥብ አምሥት ትሪሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በየዓመቱ ለመንግሥት ገቢና የትርፍ ድርሻ እያስገቡ ይገኛሉ ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ይህንን ስንመለከት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያላቸው አስተዋጽኦ እያደገ መጥቷል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ይህንን አቅማቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር ስምምነት የተፈረመ ሲሆን በዚህም በአመራር፣ በአሠራር እና በሀብት አመርቂ ውጤት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የልማት ድርጅቶች ትርፍ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉና ገቢያቸው እንዲጨምር እንሠራለን። ይህም በምርትና ምርታማነት የሚጨምር ይሆናል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በ2017 በጀት ዓመት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደርና የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓትን መዘርጋት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ችግር ሲፈጠር የቆየው በአስተዳደር ችግር ምክንያት መሆኑን አንስተው፤ ይህንንም ለመቅረፍ የአሠራር ሥርዓቱን የማዘመን እና የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ልማት ድርጅቶቹን የፋይናንስ ሥርዓት በማሻሻል ውጤታማ፣ ተወዳዳሪና አትራፊ እንዲሆኑ ማድረግ የተሰጠን ኃላፊነት ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በዚህም ድርጅቶቹ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You