
ሀዋሳ፡- በሐዋሳ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማሳደግ እንደሚያስችል የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በቅርቡ በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ በተሻለ ሁኔታ ለመቀየር ያስችላል።
የኮሪደር ልማቱ የመንገድ ማስዋብ ሥራዎችን ያካተተ፣ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገዶችን የለየ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን ከግምት ባስገባ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።
የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት በመስጠት ከተማዋን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል ያሉት ከንቲባው፤ ቱሪዝሙን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የከተማዋ የኮሪደር ልማት በሁለት መልኩ መጀመሩን የተናገሩት አቶ መኩሪያ፤ ሥራዎቹ በማስፋፊያ አካባቢ የሚከናወኑ እና በመሀል ከተማ የሚገነቡ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማስፋፊያ ሥራው 34 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 10 ትልልቅ መንገዶችን የሚሸፍን መሆኑን አስታውቀው፤ በመጀመሪያ ዙር ለ813 ተነሺዎችን ካሣ በመክፈል ቦታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሀል ከተማ የሚሠሩት የሰባት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑት ሶስት መሠረታዊ መንገዶች ቅድሚያ ተሠጥቷቸው እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ የመንገዶቹን ደረጃ የማሻሻል ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
መንገዶቹ ከኃይሌ ሪዞርት የቀድሞ ማዘጋጃ ፣ ከመምቦ ካፌ ሃዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል እና ከዲኤምሲ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እስከ ጥቁር ውሃ መግቢያ የተዘረጉ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባው፤ የመንገዶቹን ደረጃ
የማሻሻል፣ የእግረኛ፣ የብስክሌትና የአካል ጉዳተኞች መንገዶች፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶችን እንዲሁም የውሃ መዝናኛ ፋፏቴዎችን እንደሚያካት ተናግረዋል።
ከዲኤምሲ እስከ ሃዋሳ ሴራሚክስ ፋብሪካ ያለው የመንገድ ልማት ደግሞ በአካባቢው በሚገኙ ተቋማት እንደሚለማ አመላክተው ፤ተቋማቱ መንገዱን ለማልማት በግምት እስከ አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚያወጡ ገልጸዋል።
የሥራው የመጀመሪያ ምዕራፍ ከሶስት እስከ አራት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ያሉት ከንቲባው፤ ሁለተኛ ምዕራፍ የሚጀመርባቸው ቦታዎች ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የኮሪደር ልማቱ የሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ወጪዎችን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፤ የሕዝብ ተሳትፎና ተቋማት የሚያለሙትን ጨምሮ እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚወጣበት አስታውቀዋል።
እንደ ከንቲባው ገለጻ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማት ሥራውን በሃሳብ፣ በገንዘብ እና በተለያዩ መንገዶች እየደገፉ ነው።
የተጀመረው የልማት ሥራ የከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው፤ ሁለት ኮሚቴዎች ተዋቅረው በከፍተኛ ክትትል ሥራው በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም