«ከጀግኖች ስፖርተኞች ጎን ቆሞ ማበረታታት ያስፈልጋል» -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ለ33ኛ ጊዜ በፈረንሳይዋ ፓሪስ ከተማ በሚካሄደው የ2024 ኦሊምፒክ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን ከትናንት በስቲያ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አሸኛኘት ተደርጎለታል። በሽኝት መርሃግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ለልዑካኑ የማበረታቻና ማነቃቂያ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ ስፖርተኞቹ የአደራ ሰንደቅዓላማም ተረክበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለልዑካኑ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹በትውልድ ቅብብሎሽ የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ ላደረጉት ጀግኖች አትሌቶች ምስጋና ይገባቸዋል›› ብለዋል፡፡ በዘንድሮ የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ውጤት እንደሚመዘገብ ያላቸውን እምነት ጠቅሰውም፣ የሀገርን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከሚያውለበልቡ ጀግና ስፖርተኞች ጎን በመሆን ማበረታታት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፣ ስፖርተኞቹ ዝግጅታቸውን በሚያደርጉበት ወቅት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተገኝተው አትሌቶቹን አበረታተዋል፡፡ በወቅቱም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ተሳትፎ ታሪክ በአሸናፊነትና ጀግንነት የተጻፈ መሆኑን በማስታወስ፤ በፓሪስ በሚካሄደው ውድድር ይሄንኑ ድል በማስቀጠል የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ በማድረግ የሀገርን ገጽታ እንደሚገነቡ እምነታቸው ገልፀዋል፡፡

የቡድኑ አትሌቶችና አሠልጣኞችም ለዚህ ዓለም አቀፍ ድግስ በማድረግ ላይ የሚገኙትን ዝግጅት እና በፓሪስ ለማስመዝገብ ስላቀዱት ውጤት አብራርተዋል። የመካከለኛና ረጅም ርቀት አሠልጣኙ ህሉፍ ይህደጎ፣ ለሁለት ወራት በተለያየ የአየር ፀባይ ዝግጅታቸውን እያደረጉ እንደሆነና አትሌቶቹም በቡድን እና በአንድነት ለውጤት መዘጋጀታቸውን ገልጿል። በዚህም መሠረት ከአንድ ዓመት በላይ ለኦሊምፒኩ በሚገባ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ከቶኪዮ ኦሊምፒክ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የቡድኑ አሠልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ፣ ከዚህ ቀደም በሲድኒ እና ለንደን ኦሊምፒኮች የተመዘገበውን እና እየቀነሰ የመጣውን ውጤት፤ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለማስመለስ ክፍተቶችን በመለየት እየተሠራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ የተሻለ ድል ለማስመዝገብ እና ቶኪዮ ላይ የተፈጠረውን ጠባሳ ለመፋቅ ጠንካራና ቆራጥ አትሌቶች በመኖራቸው እስከ መጨረሻው ጠንክረው እንደሚሠሩና አትሌቶቹም ዝግጅታቸውን በጥሩ አቋም እና ከጉዳት ነጻ በመሆን ሲያደርጉ እንደነበር አስረድቷል፡፡

ጀግናዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ፣ ሀጎስ ገብረህይወት እና ሐብታም አለሙም ለውድድሩ ዝግጅታቸውን በአግባቡ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረው፣ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡

ከነገ በስቲያ በሚጀምረው የ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ከሚካፈሉት 206 ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በሶስት ስፖርቶች (አትሌቲክስ፣ ውሃ ዋና እና ቦክስ) ትሳተፋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእነዚህ ስፖርቶችም ከ30 በላይ አትሌቶች ተመርጠው ለሁለት ወራት ሆቴል ተሰባስበው በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ እና ሰንዳፋ ዝግጅታቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ በመካከለኛና ረጅም ርቀት እንዲሁም በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር የምትሳተፍ ሲሆን፤ እንደተለመደው ትልልቅ ድሎችን ታስመዘግባለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በውሃ ዋና ሴቶች 50 ሜትር ነጻ ቀዘፋ እና በወንዶች ቦክስ 57 ኪሎ ግራም ትሳተፋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአትሌቲክስ 33፣ በውሃ ዋና 1 እና በቦክስ 1 በአጠቃላይ በ35 ስፖርተኞች ተወክላም ለውጤት ትፋለማለች፡፡ ኢትዮጵያ እአአ ከ1956 የሜልቦርን ኦሊምፒክ መሳተፍ የጀመረች ሲሆን፤ በ1976 ሞንትሪያል፣ በ1984 ሎስ አንጀለስ እንዲሁም 1988 ሴኡል ኦሊምፒኮች ብቻ ሳትሳተፍ ቀርታለች፡፡

ዓለምን ያለ ዘር፣ እምነት፣ ቋንቋ እና ባህል ልዩነት በአንድ ጥላ ስር በስፖርታዊ ውድድሮች የሚያፋልመው ኦሊምፒክ ከነገ በስቲያ በድምቀት በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ሲጀመር፣ ሌሎች ውድድሮች ከዕለቱና አስቀድሞ መካሄድ ቢጀምሩም ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነችበትና ከዓለም ጋር የተዋወቀችበት የአትሌቲክስ ውድድሮች ከአንድ ሳምንት በኋላ ሐምሌ 25/2016ዓም አንስቶ መካሄድ ይጀምራሉ፡፡ መክፈቻው ከሌላ ጊዜ ለየት ባለ መልኩ ከኦሊምፒክ መንደር ውጪ የሚደረግ ሲሆን የተሳታፊ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች የሀገራቸውን ባንዲራ በመያዝ በጀልባ ላይ ጉዞ የሚያስተዋውቁ ይሆናል፡፡

በዘንድሮ ኦሊምፒክ ከ206 ሀገራት የተውጣጡ ከ10 ሺ 500 በላይ ስፖርተኞች ለ39 ስፖርቶች የተዘጋጁትን ሜዳሊያዎች ለማጥለቅ ይፎካከራሉ፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት በስደት ተጉዘው በሌሎች ሀገራት የሚኖሩ 100 ሚሊዮን ስደተኞችን በመወከል፤ ከ11 ሀገራት የተውጣጡ ስፖርተኞችም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባንዲራ ስር በውድድሩ ይሳተፋሉ፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You