ያደጉ ሀገራት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል

አዲስ አበባ፡ ያደጉ ሀገራት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ እንደሚገባ እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ላይ ተገለጸ፡፡

እ.አ.አ በሰኔ ወር 2025 በስፔን ለሚካሄደው አራተኛው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮንፈረንስ አጀንዳ ማሰባሰቢያ ኮንፈረንስ ትላንት በአዲስ አበባ መካሔድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ እንደሚገባ በመግለጽ፤ በአሁን ወቅት ዓለም በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ባልተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ትገኛለች ብለዋል።

እንደ አቶ አሕመድ ገለፃ፤ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በኮቪድ-19፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዓለም ሀገራት ፍትሐዊ ባልሆነ የፋይናንስ ሥርዓትና በሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች የፋይናንስ ሥርዓታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል።

በዚህም ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ ለዚህም አዳዲስ የፋይናንስ የፈጠራ ሀሳቦችን በማመንጨት፣ የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ አሕመድ፤ ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ ወጥ አሠራር መዘርጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባሕልና የታሪክ ሀብታም ሀገር መሆኗን የጠቀሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ በመሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ በድህነት ቅነሳ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ዋና ዋና የልማት ግቦች ላይ አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበች መሆኑን ተናግረዋል።

በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉበት የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የግብርናውን ዘርፍ በማጠናከር፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ምቹ የአየር ንብረት እንዲኖር በማድረግ የራሱን አስተዋፅዖ እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት።

እ.አ.አ በ2015 ኢትዮጵያ የሦስተኛውን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ልማት ኮንፈረንስ መሰናዶ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷን አስታውሰው፤ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በማዋጣትና ዛሬን በመጣር የተሻለ ነገን መፍጠር እንዳለባቸው አንስተዋል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፤ ዓለም በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ላይ እንዳለችና በዓለም ላይ በጂኦ ፖለቲካ ልዩነት ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ ያልሆነ የፋይናንስ ፍሰት መፈጠሩን ተናግረዋል።

የተበላሸውን የዓለም የፋይናንስ ሥርዓት ለማስተካከል ካደጉና ባለፀጋ ከሆኑ ሀገራት ብዙ ይጠበቃል ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ በቀጣይ የሚደረገው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ይህን የተዛባ የፋይናንስ ሥርዓት መስመር እንደሚያሲይዝ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

እየተከናወነ በሚገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በርካታ የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚጠበቁ የገለጹት ዋና ፀሐፊው፤ በስፔን የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማጠናከር የተሳለጠ የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት።

እንዲሁም በሦስተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ኮንፍረንስ ለፀደቀው የውሳኔ ሀሳብ እና ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚገባም አሳስበዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You