4ኛው ኬሮድ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በወልቂጤ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች እየተበራከቱ መጥተዋል። አብዛኞቹ ውድድሮች ትልቅ ዓላማ ሰንቀው ቢጀመሩም ተከታታይነት ሲኖራቸው ግን አይታይም። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ካስቆጠረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በስተቀር ብዙዎቹ የጎዳና ላይ ውድድሮች የአንድ ሰሞን ክስተቶች ብቻ ናቸው።

ስያሜውን በጉራጊኛ ቋንቋ “ኬሮድ” ወይም ሠላም በሚል ያገኘውና በየዓመቱ በወልቂጤና በተለያዩ የጉራጌ ዞን ከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ከተጀመረ አንስቶ ሳይቆራረጥ በየዓመቱ መካሄዱን ቀጥሏል።

ኬሮድ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የ15 ኪሎ ሜትር ውድድሩን ከትናንት በስቲያ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል። የውድድሩን ጥራት ከማሳደግ አንስቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣው የኬሮድ ውድድር ዘንድሮ የተሳታፊዎቹን ቁጥርና የሽልማት ገንዘቡን ከፍ አድርጎ ተካሂዷል። በዚህም መነሻውን ወልቂጤ ከተማ ባደረገው የ15 ኪሎ ሜትር ውድድር ከ21 ክለቦች የተውጣጡ ከስድስት መቶ በላይ ኢሊት አትሌቶች ተሳትፈዋል። አምስት ኪሎ ሜትር በሸፈነው የሕዝብ ሩጫም ከአስራ ስድስት ሺ በላይ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል። የአንድ ኪሎ ሜትር የዊልቼር ውድድርም የሩጫው አካል ነበር።

ብርቱ ፉክክር ባስተናገደውና በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር የ3ኛውና የአምናው አሸናፊ አትሌት ጨምዴሳ ደበላ በግል ዳግም የዘንድሮው ውድድር ባለድል ሆኗል። እሱን ተከትሎ የአካባቢው ክለብ ዘቢዳር ያፈራው አትሌት ዘነበ አየለ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ፈፅሟል። ሌላኛው የግል ተወዳዳሪ ጂግሳ ታደሰ ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ አትሌት ነው።

በሴቶች መካከል በተካሄደውና ተመሳሳይ ርቀት በሸፈነው ውድድር መብሪት ግደይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፣ መቅደስ ሽመልስ በግል ሁለተኛ ሆና ፈፅማለች። ጉተን ሻንቆ ከኦሮሚያ ፖሊስ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች አትሌት ሆናለች።

በውድድሩ ቀዳሚ ሆነው ያጠናቀቁ አትሌቶች እያንዳንዳቸው የአንድ መቶ ሺ ብር ሽልማት ሲያገኙ፣ ሁለተኛ ሆነው የፈፀሙ የ50 ሺ ብር፣ ሦስተኛ ደረጃን የያዙ ደግሞ የ25 ሺ ብር ሽልማት ተረክበዋል። እስከ ስድስተኛ ደረጃ ባለው ያጠናቀቁ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው እስከ አምስት ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። አምና ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀ አትሌት የሚያገኘው የ75 ሺ ብር ሽልማት ዘንድሮ ወደ 100 ሺ ብር እንዳደገም ተጠቁሟል።

የጉራጌ ዞን የውድድሩን መሥራች የቀድሞው አትሌትና የአሁኑ አሠልጣኝ ተሰማ አብሽሮን ጨምሮ ወንድሙ አየለ አብሽሮ፣ የኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ፣ ጥላሁን ኃይሌ፣ አንዱአምላክ በልሁና ሌሎችን ትልልቅ አትሌቶች አፍርቷል። የኬሮድ ውድድርም በአካባቢው ሌሎች ወጣት አትሌቶች ወደ ታላላቅ ውድድሮች የሚሸጋገሩበትና ራሳቸውን የሚያሳዩበት ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታትም በዚሁ ውድድር ራሳቸውን አሳይተው በትልልቅ ዓለም አቀፍ የግል ውድድሮችና ሀገራቸውን መወከል የቻሉ በርካታ አትሌቶች ተገኝተውበታል።

በቀጣይ በአጎራባች ዞኖች እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ የውድድሩን አድማስ በማስፋት በየአካባቢው ለሚገኙ ወጣት አትሌቶች ተመሳሳይ የውድድር ዕድል ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የውድድሩ መሥራች አየለ አብሽሮ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግሯል።

“ለኢትዮጵያ ሠላም እንሩጥ”! በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ውድድር ዞኑ በልማቱና በስፖርቱ ዘርፍ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ የተመሠረተ ነው። በዚህም የሩጫ ውድድሩ ወቅታዊ ችግሮችን በመቅረፉ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው ጠቁመው፣ “ውድድሩ ባሕላችንን አጉልተን ያሳየንበት፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነችው ከተማችን ገፅታዋ እንዳይበላሽ ሁሉም በከተማው የሚኖረው ሕዝብ ይህንን ጠብቆ ማቆየት ይኖርበታል።” በማለት ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው፣ የዞኑ ማኅበረሰብ በስፖርት ልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተገኙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ለስፖርት ልማት ሥራ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በምትታወቅበት በአትሌቲክስ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት እና እያስገኘ ያለው ጠቀሜታ የበለጠ ጎልቶ እንዲወጣ በማድረግ ስፖርት ለሠላም፣ ለፍቅር እና ለአንድነት በጋራ ቆመን በአትሌቲክስ ዘርፍ ብቁ አትሌቶችን በማፍራት በዓለም አደባባይ ደምቀንና ጎልተን እንድንወጣ ሁላችንም በቅንጅት መሥራት ይጠበቅብናልም ብለዋል።

ቦጋለ አበበ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You