ኢራን በሁለት ሳምንት ውስጥ የኑክሌር ቦምብ ግብዓት እንደምታሟላ ተገለጸ

ኢራን በሁለት ሳምንት ውስጥ የኑክሌር ቦምብ ግብዓት እንደምታሟላ ተገለጸ፡፡

ከምዕራባውያን ጋር ሆድና ጀርባ የሆነችው ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ዋነኛ የስጋት ምንጭ መሆኗን አሜሪካ አስታውቃለች፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን በኮሎራዶ በተካሄደ የጸጥታ እና ደህንነት ጉባዔ ላይ ተገኝተው እንዳሉት፤ ኢራን በአንድ አልያም በሁለት ሳምንት ውስጥ የኑክሌር ቦምብ መስራት የሚያስችላትን ግብዓት ታሟላለች ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አስፐን በተሰኘው ዓለም አቀፍ የደህንነት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር አሁን ያለንበት ቦታ ትክክለኛው አይደለም ያሉ ሲሆን፤ ስለ ኢራን ኑክሌር ጉዳይ መሰል አስተያየት ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው ተብሏል፡፡

ኢራን እስካሁን የኑክሌር ቦምብ አልታጠቀችም የሚሉት ብሊንከን ጉዳዩን በጥንቃቄ መከታተል ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ ፖሊሲ ኢራን ኑክሌር ቦምብ እንዳትታጠቅ ነው ያሉት ብሊንከን እስካሁን ኢራን እቅዷን እንዳታሳካ ዲፕሎማሲን ስትከተል መቆየቷንም ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የአሜሪካ ከፍተኛ የመከላከያ አመራር ኢራን እስካሁን በ12 ቀናት ውስጥ አንድ የኑክሌር ቦምብ መሥራት የሚያስችል ግብዓት መሰብሰቧን ተናግረው ነበር፡፡

የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ከኢራን ጋር በሶስተኛ ወገን በኩል ስትደራደር የቆየ ሲሆን በተለይም በፈረንጆቹ 2018 ላይ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመን የተሰረዘው የኢራን ኑክሌር ስምምነትን ዳግም ለማስጀመር ሲወያዩ እንደቆዩም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ይሁንና በ2022 በዓለም አቀፉ አቶሚክ ሃይል ምርመራ ወቅት ኢራን በድብቅ ዩራኒየም እያበለጸገች መሆኗን የሚያሳይ ፍንጭ ማግኘቱን ተከትሎ የሁለትዮሽ ውይይቱ ተቋርጧል ተብሏል፡፡

የእስራኤል- ሐማስ ጦርነት ላይ አሜሪካ በቀጥታ መሳተፏን ተከትሎ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉ ታጣቂዎች በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣዎችን ኢላማ አድርገዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You