በዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር የሚመራና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ ፕሮፌሽናል የቦክስ ሻምፒዮና ምሽት በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል:: በከተማዋ የተከፈተው የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት በዕለቱ በይፋ የሚመረቅ መሆኑንም የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል::
በቦክስ ስፖርት እምብዛም የሚነሳ ስም የሌላት አፍሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አበረታች እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል:: ይህንንም ተከትሎ በዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር የሚመራ ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕጉሪቷ የሚካሄድ ይሆናል:: ‹‹Africa United›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚደረገው ውድድር የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በመጪው የነሐሴ ወር አጋማሽ በዓድዋ ሙዚየም ይደረጋል:: በውድድሩም የኮንፌዴሬሽኑ አባል የሆኑ ሃገራትን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማኅበር እንዲሁም በስፖርቱ ውስጥ ያለፉ ታላላቅ ቦክሰኞች እንዲገኙ ጥሪ የሚደረግላቸው መሆኑም ታውቋል::
ከቦክስ ውድድር በተጓዳኝ መቀመጫውን በከተማዋ ያደረገው የኮንፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤትም በይፋ ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር ትናንት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቁሟል:: የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ወሰን፤ በአሕጉር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት መሆናቸው ይታወቃል:: በዚህም ኮንፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ከተማ ከፍቷል:: ለጽሕፈት ቤት በተደረገው ሌላ ውድድር ላይም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊው የስፖርት ባለሙያ አቶ ቢልልኝ መቆያ ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡ መሆኑ የሚታወስ ነው:: በመሆኑም ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሚደረገው ይፋዊ የምርቃት ሥነሥርዓት በኋላ ሥራውን የሚጀምር ይሆናል::
በመግለጫው የተሳተፉት የዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ክርስቶፈር ሮበርትስ፤ ኮንፌዴሬሽኑ ከማኅበሩ ጋር በፈጠረው ጠንካራ ግንኙነት ምክንያት ይህ ውድድር በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል:: ኢትዮጵያ ውድድሩን በብቃት እንደምታዘጋጀው እምነታቸው መሆኑንና ማኅበራቸውም ከጎናቸው መሆኑንም አረጋግጠዋል:: ከውድድሩ ባለፈም በቀጣይ ከብሔራዊው ፌዴሬሽን ጋር በመሆን በፕሮጀክቶች በማተኮር የሚሠሩም ይሆናል::
የአፍሪካ እና ኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ወሰን በበኩላቸው፤ የውድድር ዕድሉ ቀድሞ በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ የነበረውን ብልሹ አሠራር ለመቀየር በተደረገው ብርቱ ጥረት የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል:: ይኸውም አፍሪካን የሚያኮራ ሲሆን፤ ስፖርቱን በማሳደግና የኢትዮጵያን ስም በማስጠራት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል:: ከዚህ ቀደም በአሕጉሪቱ ተደርጎ የማያውቀውን ይህንን ዓለም አቀፍ ውድድር ወጪ የሚሸፍነው ዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር ነው:: በአፍሪካ ደረጃ ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ ባይኖርም ኮንፌዴሬሽኑ እያከናወነ ያለውን ጠንካራ ሥራ ተከትሎ ተፎካካሪ ቦክሰኞችን ማፍራት እንደሚቻልም አመላክተዋል::
በኢትዮጵያ የሚደረገው ይህ ውድድር እንዲሁም ጽሕፈት ቤቱ በአዲስ አበባ መከፈቱ ስፖርቱን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ በመንግሥት በኩል የሚደገፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ናቸው:: ውድድሩ ኢትዮጵያ መልካም ገጽታዋን የምትገነባበትን አጋጣሚ የሚፈጥር ሲሆን፤ እንግዶችን ለመቀበልም ዝግጅት እየተደረገ ነው:: ዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር የውድድር ዕድልና ድጋፍ በማድረጉ ምስጋና ይገባዋልም ብለዋል::
በኢፌዴሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ ጽሕፈት ቤቱ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ማድረጉ ኢትዮጵያ በአሕጉራዊ ስፖርት ያላትን ተሳትፎ የምታሳይበት መሆኑን ገልፀዋል:: ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ጨዋታዎችን ጨምሮ በሌሎች አሕጉር አቀፍ ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያዊያን ቦክሰኞች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች በስፖርቱ ያለውን መነቃቃት የሚያመላክት ሲሆን፤ ሻምፒዮናው በከተማዋ መዘጋጀቱ ደግሞ ስፖርቱን ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል:: ውጤታማ ሆኖ የተገኘው የስፖርት ዲፕሎማሲ ተጠናክሮ የሚቀጥልና ለውድድሩም ሃገር አቀፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት::
ዓለም አቀፉ የቦክስ ሻምፒዮና በስምንት ምድቦች ውድድሩን የሚያካሄድ ሲሆን፤ በሴቶች በ60 ኪሎ ግራም በሚሊዮን ጨፎ ከኢትዮጵያ እና ሀድጅላ ከሊፍ ከአልጀሪያ፣ በ54 ኪሎ ግራም ውዳድ በርታል ከሞሮኮ እና ሣራ ሀግሂግሃት ጆ ከሴራሊዮን እንዲሁም በ75 ኪሎ ግራም ፓትሪሺያ ምባታ ከናይጄሪያ እና ራዲ አዶንሲንዳ ግራማኒ ከሞዛምቢክ የሚፋለሙ ይሆናል::
በወንዶች ደግሞ በ92 ኪሎ ግራም ፒተር አቡቲ ከኬኒያ እና አሎሬ አድማስ ከናይጄሪያ፣ በ75 ኪሎ ግራም ያሲኔ ኢሎረዝ ከሞሮኮ እና ቲያንጎ ሙታንጋ ከሞዛምቢክ፣ በ60 ኪሎ ግራም አቡበከር ሴፈን ከኢትዮጵያ እና ራሺድ ኦማሪ ከሶማሊያ፣ በ80 ኪሎ ግራም ፒታ ካቤጂ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የሱፍ ቻንጋላዊ ከታንዛኒያ፣ በ51 ኪሎ ግራም ፓትሪክ ችንየምባ ከዛምቢያ እና ዴቪድ ፒና ከኬፕቨርድ በውድድሩ እንደሚካፈሉ የወጣው የውድድር መርሐ ግብር ያሳያል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም