በኦሊምፒክ ኮሚቴ የታፈኑ የሕዝብ ሚዲያዎች

የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፉት ስምንት ዓመታት ገደማ እየመራ የሚገኘው አመራር ትልቁ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ በመጣ ቁጥር እየፈጠረ የሚገኘው ችግር በስፖርቱ ብቻ የተገደበ አይደለም። የሀገሪቱ ትልልቅ የሕዝብ ሚዲያዎች ላይ እየፈፀመ የሚገኘው በደል ወንጀልም ጭምር ነው።

በግልፅ ባልሆነ የተቋም መዋቅር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቀድሞ የነበረውን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አፍርሶ ባለሙያዎችንም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ያሰናበተው ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በፊት ነበር። በዚህም በሚዲያው ረገድ ያለው ግንኙነት እንደ ተቋም ሳይሆን እንደግለሰብ ነው። የእኔ የሚላቸው ጋዜጠኞች እንደ ሕዝብ ግንኙነት እያገለገሉት ይገኛሉ። የትኛውንም የሚዲያ ግንኙነቶች የሚያደርገውም በእነሱ በኩል ነው። ትንንሽ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እንኳን ሳይቀሩ እንዲዘግቡ ጥሪ የሚደረግላቸው ለኮሚቴው አካሄድ ምቹ የሆኑ ጋዜጠኞች ብቻ ናቸው። በዚህ ምክንያት በርካታ ትልልቅና አንጋፋ የሕዝብ ሚዲያዎች መረጃ የማግኘትም ሆነ የሀገሪቱን ኦሊምፒክ እንቅስቃሴ እንዳይዘግቡ ታፍነዋል።

በቶኪዮም ሆነ በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ጋር ድርሽ እንዳይሉ ከተደረጉ የሕዝብ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት(ኢፕድ) እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ዋነኞቹ ናቸው። ሁለቱም አንጋፋና ብሔራዊ ሚዲያዎች ኮሚቴው ለቶኪዮና ፓሪስ ኦሊምፒኮች ባቋቋመው የሚዲያ ኮሚቴ ውስጥ ከተመሠረቱ ሁለት ዓመት እንኳን ያልሞላቸውና ከአንድ ከተማ የዘለለ ተደራሽነት የሌላቸው ትንንሽ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ሲካተቱ ሆን ተብሎ ተገፍተዋል። መረጃ የማግኘት መብታቸው ጭምር ታፍኗል። በዚህ የሚዲያ ኮሚቴ ውስጥ በጠቅላላ የተካተቱ ጋዜጠኞች በየትኛው መስፈርትና መርሕ ተመረጡ ካልን “በእከክልኝ ልከክልህ” መርሕ ሆኖ እናገኘዋለን። ግንኙነታቸውም እንደ ተቋም ሳይሆን እንደ ግለሰብ ከኮሚቴው አመራሮች ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ጋዜጠኞች ስለመሆናቸው ከበቂ በላይ ማሳያ መደርደር ይቻላል።

ኮሚቴው በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ወደ ፓሪስ የሚሄዱ ሚዲያዎችን በተመለከተ ‹‹እኛ ጋዜጠኞችን መርጠን ይዘን አንሄድም፤ በራሳቸው ተመዝግበው የዘገባ ፈቃድ(accreditation) ሲያገኙ ይሄዳሉ›› ብሏል። እውነታው ግን ወዲህ ነው፣ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የኅትመትና የፎቶ ጋዜጠኞች የኦሊምፒክ የዘገባ ፈቃድ(accreditation) ፎርምና የምዝገባ ኮድ ለጋዜጠኞች አልያም ለሚዲያ አይልክም፤ የሚልከው ለየሀገራቱ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው፤ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጋዜጠኞች ደግሞ በዓለም አቀፉ ይመዘገባሉ፤ ኢትዮጵያ ያላትን ኮታ የኮሚቴው አመራር ፎርምና ኮዱን ለመረጡትና የእኔ ናቸው የሚሏቸውን ጋዜጠኞች ይሰጡና የኅትመትና የፎቶ ጋዜጠኞች ብለው ወጪያቸውን ችለው ይዘዋቸው ይሄዳሉ። ለምሳሌ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ጋዜጠኞች በቀጥታ በኮሚቴው ተመርጠው የአውሮፕላን ትኬትና ሆቴል ተችለው አበል ተሰጥቷቸው ሄደዋል፤ ለፓሪስ ኦሊምፒክም በተመሳሳይ የተመረጡ ጋዜጠኞች አሉ። ይሄን ዓለም ያወቀው እውነታ ግን ኮሚቴው በግልፅ ሸምጥጧል።

ዘንድሮም ይሁን ያለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተመረጡ ሚዲያዎች አንድም የኅትመትና የፎቶ ግራፍ ጋዜጠኛ የለም። ሁሉም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ሲሆኑ የሕዝብ ሳይሆኑ የግል ናቸው። አንዱ ጋዜጠኛ ከኅትመት ሚዲያ ነው የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን እሱም ቢሆን የተመረጠው ቀደም ሲል ይሠራበት በነበረው ሬዲዮ ጣቢያ እንጂ አሁን በሚሠራበት ጋዜጣ አይደለም። ይህ ጋዜጠኛ ሲመረጥ ይሠራበት የነበረው ሬድዮ ጣቢያ ሲታገድ ወደ ሌላ ጋዜጣ ሥራ ቀየረ። አስገራሚው ነገር ይህ ጋዜጠኛ ባለፈው ኦሊምፒክም ቶኪዮ ተጉዟል። አሁንም ፓሪስ ተጓዥ ነው። ይህ በግልፅ የሚያመለክተው ኦሊምፒክ ኮሚቴው ግንኙነቱ በመርሕና በሕግ ከተቋም ጋር ሳይሆን ከግለሰቦች ጋር መሆኑን ነው።

ወደ ፓሪስ ከሚሄዱ ጋዜጠኞች አንዱ ከሕዝብ ሚዲያ ነው፣ እሱም ቢሆን ኦሊምፒክ ኮሚቴ በራሱ ፍቃድ የመረጠው እንጂ ተቋሙ መድቦት አይደለም። ከሕዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ ግን የሕዝብ ሚዲያዎች አናውቃችሁም ተብለዋል። ጥያቄው የተመረጡት ጋዜጠኞች ለምን ተመረጡ አይደለም፣ በምን መስፈርት ተመረጡ እንጂ። ቢቻል ሁሉም የኢትዮጵያ ሚዲያ ወደ ፓሪስ ቢሄድ የሚቃወም የለም። ነገር ግን ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለማነው?

ተፅፎ ባይገኝ እንኳን ለማንም ግልፅ የሆነው መርሕ ለሕዝብ ሚዲያዎች በተደራሽነታቸው በሚዲያ ኮሚቴውም ሆነ ለኦሊምፒኩ ዘገባ ቅድሚያ እንኳን ባያገኙ መካተት እንዳለባቸው ነው። የሆነው ግን በተቃራኒ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አንጋፋና ቀዳሚ የሆነ ትልቅ የሕዝብ ሚዲያ መሆኑ ይታወቃል። ኢፕድ በተለያዩ የኅትመት ውጤቶቹ በሀገር ውስጥና በውጪ ቋንቋዎች ከ80 ዓመታት በላይ ለሕዝብ መረጃዎችን ከማድረስ በተጨማሪ የሀገራችንን ታሪክ ለትውልድ ሰንዶ በማስቀመጥም ብቸኛው የሚዲያ ተቋም ነው። በነዚህ ዓመታት እለታዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን በመዘገብ ለትውልድ የሚሻገሩ ታሪኮችን ሲሰንድ የብርቅዬና ጀግና አትሌቶቻችን የኦሊምፒክ ስኬትም አንዱና ትልቁ ትኩረቱ መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በ1960ው የሮም ኦሊምፒክ በጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ ጀምሮ መረጃዎችንና ለሕዝብ በማድረስ ኢፕድ እንደ አንድ የሕዝብ ሚዲያ ኃላፊነቱን ተወጥቷል። በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ እንቅስቃሴም ከዓለም አቀፍ መድረኮች በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ኦሊምፒክን የተመለከቱ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በቅርበት በመሥራት በውድድር ስፍራዎች ተገኝቶ ሲዘግብና ታሪክን በኅትመት ውጤቶቹ ለትውልድ መዝግቦ ሲያኖር ቆይቷል። ለዚህም በእያንዳንዱ ኦሊምፒክ በጋዜጦች ላይ የተሠሩ ዘገባዎችና ቃለመጠይቆች ሕያው ምስክር ሆነው ይገኛሉ።

ኢፕድ አሁንም ተደራሽነቱን በማስፋት በኢትዮጵያ ብቸኛ በሆኑትና በየእለቱ ለኅትመት በሚበቁት አንጋፋዎቹ አዲስ ዘመን እና ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጦች፣ በየሳምንቱ በሚታተሙት የአፋን ኦሮሞ፣ ትግሪኛ፣ ዓረብኛ እና ሲዳምኛ ቋንቋዎች በሚታተሙ ጋዜጦች እንዲሁም በኦንላይን የፌስ ቡክ ገፆቹና ዌብሳይት ሰፊ ተደራሽነት ባላቸው ሶማልኛና አፋርኛ ቋንቋዎች ለሚሊዮኖች ተደራሽ ነው። ካለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ጀምሮ ግን በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ካለ አንዳች ምክንያት ገለል ተደርጓል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በተመሳሳይ።

ይህ የአንድ ተቋም ጉዳይ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያን በኦሊምፒኩ የሚወክሉ አትሌቶች ከተለያዩ ክልሎችና የተለያዩ ቋንቋዎችን ከሚናገሩ ሕዝቦች የተገኙ ናቸው። የአትሌቶቹ ቤተሰቦችም ይሁኑ የወጡበት ማኅበረሰብ ድላቸውንም ይሁን በደላቸውን በቋንቋው መስማት ወይም ማንበብ ይፈልጋል፣ መብቱም ነው። ስለዚህ ጉዳዩ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሊዮኖችን መረጃ የማግኘት መብት የማፈንም ጭምር የሚሆነው ለዚህ ነው። አስገራሚው ነገር ይህ አሳፋሪ ድርጊት የሚፈፀመው አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነ ሰው በሚመራው ተቋም ነው።

አሁን ወደ ፓሪስ የሚሄዱት ሚዲያዎች ይህ ሁሉ ግልፅ የሕግ ጥሰትና የአትሌቶች በደል በአደባባይ እየታየ አንድም ነገር ትንፍሽ ሲሉ አልታዩም። ፓሪስም ሄደው ትክክለኛውን ነገር ለሕዝብ ተደራሽ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ባለፈው ቶኪዮ ላይም ያሁሉ የአትሌቶች በደል ሲፈፀም መረጃውን አፍነው ምንም እንዳልተከሰተ አልፈዋል። ኦሊምፒክ ኮሚቴም የመረጣቸው ለዚሁ ነውና።

አሜን ከካምቦሎጆ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You