የስኬት መርሆች!

ስኬት በብዙ መንገድ ይገለፃል:: ሁሉም እንደየሙያውና እንዳለበት ሁኔታም ነው ለስኬት ያለውን አመለካከት የሚገልፀው:: አንድ ሁሉንም ሊያስማማ የሚችለው ነጥብ ግን ስኬት በየትኛውም የሙያ ዘርፍም ይሁን በየትኛውም ሁኔታና፣ ቦታ፣ ጊዜና ሰአት በፊት ከነበሩበት አነስተኛ፣ ዝቅተኛ፣ የማይጠቅም ወይም የማይረባ ሕይወት መውጣትና ወደተሻለ ቦታ መምጣት ነው:: ሕይወትን በእውን መኖር ነው::

አንዳንድ ሰዎች በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው በስተመጨረሻ ከሱስ ሕይወታቸው የመውጣት ፍላጎት ቢኖራቸውም ከነበሩበት መጥፎ ልማድ ለመላቀቅ ሲቸገሩ ይስተዋላል:: ሱሳቸውን ለመተው ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ተስፋ ቆርጠው እዛው የሱስ ሕይወት ውስጥ ተመልሰው ሲገቡ ይታያሉ:: ነገር ግን ከዚህ የሱስ ሕይወት ድንገት መንጭቀው ወጥተው ወደ ጤናማ ሕይወት የሚመለሱ ሠዎች አሉ:: እነዚህ ሰዎች ሱስን አሸንፈው ወደጤናማ ሕይወት በመመለሳቸው ብቻ ስኬታማ ብለን ልንወስዳቸው እንችላለን::

ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው ራሱን የሚያስተዳድርበት ገቢ አለው:: አንዳንዱ ብዙ ሠርቶ ገቢውን በእጥፍ ያሳድጋል:: ሌላው ደግሞ እንደአቅሙ ተፍጨርጭሮ በመጠኑም ቢሆን ገቢውን የሚያሳድግ አለ:: እዚህ ጋር በእጥፍ ገቢውን ያሳደገውም፤ በገቢው ላይ መጠነኛ ጭማሪ እንዲኖር የለፋውም በየራሳቸው ስኬታማ ናቸው:: ምክንያቱም ሁለቱም ገቢያቸውን ለማሳደግ ሠርተዋል፤ ልዩነት ቢኖረውም ገቢያቸውን አሳድገዋል::

እነዚህን እንደምሳሌ አነሳን እንጂ በየትኛውም የሥራ መስክ በሕይወቱ ስኬታማ መሆን የማይፈልግ ሰው የለም:: ሁሉም ስኬታማ መሆን ይፈልጋል:: የሰው ልጅ በሕይወቱ አውቆም ሆነ ሳያውቀው መሆን የሚፈልገው ነገር ቢኖር ስኬታማ መሆን ነው:: ነገር ግን እውነተኛ ስኬት ምን እንደሆነ በጥልቀት የሚያውቁ ሰዎች በቁጥር እጅግ በጣም ትንሽ በመሆናቸው ሁሉም ሰው ስኬታማ ነው ማለት አይቻልም:: ምንም እንኳን ሁላችንም ስኬታማ መሆን ብንፈልግም እውነተኛ ስኬታማ ሰዎች ቁጥራችን ጥቂት ነው:: ታዲያ ለምድን ነው ሁላችንም ስኬታማ መሆን ያልቻልነው? ይህ ስለስኬት ስናወራ መሠረታዊ ከሆኑ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ነው::

ገና ከመነሻው የስኬት ትርጉሙ ካልገባን አላፊው አግዳሚው ሁሉ ይወስደናል:: ወደላሰብንበት አቅጣጫ እንሄዳለን:: ስለዚህ ስኬት ምን እንደሆነ ገና ጉዞ ሳንጀምር ማወቅ ይጠበቅብናል:: በስኬታማና ስኬታማ ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማጤን ይኖርብናል:: ዛሬ ላይ ስኬት የሚለው ቃል በየቦታው የሚወራ ሆኗል:: ከዚህ አንፃር ሰዎች በስኬት ዙሪያ ግራ ተጋብተዋል ማለት ይቻላል::

የሕይወታችን ስኬት በየቀኑ በውስጣችን በሚመላለሱ ሃሳቦችና በምንፈፅማቸው ድርጊቶች ይወሰናል:: አሸናፊዎች ሁሌም የመሻሻልና የእድገት አስተሳሰብ አላቸው:: ይህ አስተሳሰብ ባሉበት መርገጣቸውን በፀጋ ተቀብለው ከሚኖሩ ወይም ለመሻሻል የሚያስፈልገውን ለውጥ ለማድረግ ድፍረት አጥተው ከተቀመጡ ሰዎች በእጅጉ ይለያል:: ህልማችንን እናሳካለን ወይስ ሁሌም የሌሎችን ስኬት በስስት እያየን እልያ ደግሞ የአርባ ቀን እድላችንን እንቆያለን የሚለውን ከሚወስኑት መካከል አንደኛው አስተሳሰባችን ነው::

ያለምንም ጥርጥር ስኬትን የምንተነፍሰውን ያህል እንፈልገዋለን:: ከተወለድንባት ቅጽበት አንስቶ የበለጠ ለማድረግ፣ የበለጠ ለማግኘት፣ የበለጠ ለመሆን እንሻለን:: ስኬት ወደ ፍጽምና ለመድረስ መትጋት እንደሆነ አዕምሮአዊ ምስል ቢኖረንም እውነታው ግን የበለጠ ተፈጥሮአዊ መሆኑ ነው:: ስኬት በውስጣችን ያለውን ወይም የተቀመጠውን እምቅ ህልም ወይም ሃይል የማውጣት ድፍረት ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል:: ትንፋሽ የመስጠት ዕድል ነው ቢባልም ያስኬዳል:: አብዛኛው ሰውን ግን ይሄን ጉዳይ አይሞክረውም ምክንያቱም አደገኛ መስሎ ስለሚታየው ነው – የተለመደ የአዘቦት ቀን ተግባር አይደለምና:: ከነገሩ ጋር ለተለማመዱ ሰዎች ግን የተለመደ የሕይወት ጐዳናቸው ነው:: እነሱ ቤተኛ ናቸው::

ብዙ ወይም የበለጠ የመሻት ስሜት አንዳንድ ጊዜ በአስተዳደጋችን ወይም በባህላችን የተነሳ ከውስጣችን የሚጠፋበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ስለዚህም ከሕይወት የምንጠብቀው ዝቅ ያለና ከዕፁብ ድንቅ ያነሰ ነገር ይሆናል:: ሆኖም ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም:: ለስኬት ያለን ፍላጐት ዳግም ሊነቃቃና ሊነሳሳ ይችላል:: ዳግም ዕፁብ ድንቅ ሕይወት ልንሻ እንችላለን:: ከስኬት ጋርም ቤተኛ እንሆናለን::

ስኬት ሁሉ ግን ስኬት እንዳልሆነ ማወቅ ተገቢ ነው:: አንዳንዶች ሕይወታቸውን ሁሉ የስኬትን መሰላል ሲወጣጡ ከርመው የማታ ማታ መሰላሉ ትክክለኛው ግድግዳ ላይ ተደግፎ እንዳልነበረ ይገነዘቡታል – እናም ስኬታቸው ትክክለኛው ወይም እነሱ የሚሹት አልነበረም ማለት ነው:: ለዚህም ነው ትክክለኛውን ስኬት መቀዳጀታችንን ማረጋገጥ ያለብን:: የእኛን የተሟላ ሰብዕናና ችሎታ በአስደናቂ መንገድ መግለጽ የሚችል ሊሆን ይገባል ስኬታችን:: ስኬት አንዲት ነጠላ ሁነት ወይም ውጤት አይደለችም – በውስጣችን ያለ ድንቅ ተሰጥኦ መገለጫ እንጂ:: ዓለም ይሄንን ተሰጥኦ የበለጠ ሰዋዊና የበለጠ ውብ እንድናደርገው ህልቆ መሳፍርት ዕድሎችን ታቀርብልናለች:: ተሰጥኦአችንን ወይም የነፍሳችንን ጥሪ ፈልጐ ማግኘት ግን የኛ ተግባር ነው::

እውነተኛ ስኬት ለማሸነፍ ሲባል ብቻ የማሸነፍ ጉዳይ አይደለም:: ቲሞቲ ጋልዌይ የተባለ የስኬት ሊቅ እንዲህ ይላል- ..ማሸነፍ አንድ የሆነ ግብ ላይ ለመድረስ መሰናክሎችን ማለፍ ነው፤ የአሸናፊነቱ ትልቅነት የሚለካው ግን በተደረሰበት ግብ ትልቅነት ነው:: ሆኖም ግን የማሸነፍ አባዜ ተጠናውቶን ብቻ የምንቀዳጀውን ጊዜያዊ ስኬት ሕይወታችንንና የሌሎችን ሕይወት ከሚያበለጽግልን ዘላቂ ስኬት መለየት መቻል አለብን:: ትክክለኛውና ዘላቂው ስኬት የዓለምን ሀብት በከፍተኛ ሁኔታና ያለብዙ ብክነት ጥቅም ላይ ያውላል::

የስኬት መርሆች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ተስፈኝነት (ደግ አሳቢነት) አንዱ ነው:: ትላልቅ ችግርና መከራዎችን አሸንፈው ስኬትን የተቀዳጁ ሰዎች ሁሉ ምስጢር እንደሆነም ይነገራል:: ኔልሰን ማንዴላ፣ ኧርነስት ሻክሌተን፣ ኢሊኖር ሩስቬልት – የመከራ ጊዜያቶችን ተቋቁመው ለማለፍ ያስቻላቸው በአዎንታዊ ነገሮች ላይ የማተኮር ችሎታቸው እንደሆነ በይፋ ይቀበላሉ:: እነዚህ ሰዎች ክላውዴ ብሪስቶል የተባለው ሊቅ ..የእምነት ተዓምራዊ ሃይል.. የሚለው ነገር ገ ብቶአቸዋል ማለት ነው::

ታላላቅ መሪዎች እንዲሁ ደረቅ እውነታን ፊት ለፊት የመጋፈጥ ያልተለመደ ችሎታ እንዳላቸው ይነገራል:: ለዚህ ብቸኛ ሃይላቸው አድርገው የሚቆጥሩት ደግሞ ቆራጥነት የተመላበትን ተስፈኝነታቸውን ነው:: ተስፈኛ ሰዎች የሚሳካላቸው ነገሮች ጥሩ ይሆናሉ ብለው ስለሚያምኑ ብቻ አይደለም፤ ስኬትን መጠበቃቸውም ተግተው እንዲሠሩ ስለሚያደርጋቸው ጭምር ነው:: ከሕይወት የምንጠብቀው ትንሽ ነገር ከሆነ ትንሽ ሙከራ እንኳን ለማድረግም አንነሳሳም:: ከፍ ያለ ነገር ስንጠብቅ ብቻ ነው ጥረታችንም ከፍ ያለ የሚሆነው::

ስኬት የታመቀ ጥረት ይፈልጋል:: አብዛኞቹ ሰዎች ጉልበታቸውን (ሃይላቸውን) በብዙ ነገሮች ላይ ይበታተኑታል:: በዚህም የተነሳ በምንም ነገር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይሳናቸዋል:: ኦሪስን ስዌት ማርደን ይሄን በተመለከተ ሲናገር ..ዓለም ጠበቃ፣ ሚኒስትር፣ ሃኪም፣ ገበሬ፣ ሳይንቲስት ወይም ነጋዴ እንድትሆን አትጠይቅህም፤ መሥራት ያለብህን አትነግርህም፤ ነገር ግን በምትሠራው ማናቸውም ሥራዎች የበቃህ እንድትሆን ትጠይቅሃለች:: ስለዚህም ስኬታማ ለመሆን የላቀ ዓላማና ግብ ሊኖርህ ይገባል፤ ያንን ለማሳካትም በቁርጠኝነት ጥረትህን መግፋት አለብህ::

የዓለም ሥልጣኔ ጐህ ሲቀድ አንስቶ የነበሩ ታላላቅ መሪዎች ሁሉ የየራሳቸው ህልም የነበራቸው ናቸው:: ህልም ሳይኖርህ ስኬት የሚታለም አይደለም:: ሀብትና ብልጽግናን በምናብህ ሳትቀርጽ በባንክ ሂሳብህ ውስጥ ከቶውንም ልታይ አትችልም:: የሚቀድመው የምትሻውን በምናብህ መሳል ነው:: ከዚያም በእውንህ ታየዋለህ::

ግን ህልም ከየት ይፈጠራል? ‹‹Think and Grow Rich›› የተሰኘው ድንቅ መጽሐፍ ደራሲ ናፖሊዮን ሂል፤ ህልም እንደ እሳት ከሚንቀለቀል ውስጣዊ ፍላጐት ይወለዳል ይለናል:: ህልም ከችላ ባይነት፣ ከስንፍና ወይም ከፍላጐተ – ቢስነት አይፈጠርም:: የስኬታማ ሰዎች ሌላው መርህ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን ነው – አንድ ድንቅ የሆነ ነገር ለመፍጠር ሁሌም ተግተው ይሠራሉ:: ተግተን በሠራን ቁጥር ስለራሳችን አንድ ነገር እናውቃለን:: የስኬት ሕግ እንደሚለው አንድ ጊዜ ስኬትን ከተቀዳጀን እንዲዘልቅ የሚያደርገው ሁኔታ ራሱ ይፈጥራል::

እንደ ስኬት የሚቀጥል ምንም ነገር የለም ይባላል:: ዘላቂ ስኬት የሚገነባው በዲሲፕሊን ላይ እንደሆነ ማወቅ ብልህነት ነው:: ለራሳችን ትዕዛዝ መስጠትና ትዕዛዙን መከተል መማር አለብን:: ይሄ ጉዳይ ለጊዜው አሰልቺ ሊመስለን ይችላል:: የረዥም ጊዜ ውጤቱ ግን አስደማሚ ይሆናል:: ታላላቅ ስኬታማ ሰዎች ዩኒቨርስ የተገነባው በአቶሞች እንደመሆኑ ስኬት ደግሞ በእያንዳንዷ ደቂቃ እንደሚገነባ አሳምረው ያውቃሉ።

በእርግጥ ለዛሬው ዘመን ህልመኞች ትዕግስትና ክፍት አዕምሮ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው:: አዳዲስ ሃሳቦችን ለመቀበል የሚፈሩና ዝግጁ ያልሆኑ ሰዎች ገና ሳይጀምሩ ያከተመላቸው ናቸው:: ልትሠራ የምትፈልገው ነገር ትክክለኛና የምታምንበት ከሆነ ሳታወላውል አድርገው ይላል ናፖሊዮን ሂል:: እወድቃለሁ ብለህ አትፍራ:: እያንዳንዱ ውድቀት አቻውን የስኬት ዘር ይዞ ይመጣልና:: የስኬትና የብልጽግና ሌላው መርህ ጥብቅ የሆነ እምነት ነው::

በእርግጥ አንድን ነገር መፈለግ ወይም መመኘትና የፈለጉትን ነገር ለመቀበል ዝግጁ መሆን የተለያዩ ነገሮች ናቸው:: ማንም ሰው አንድን ነገር እንደሚያገኘው እስካላመነ ድረስ ለዚያ ነገር ዝግጁ ነው ማለት አይቻልም:: አዕምሮው ተስፋና ምኞት ላይ ሳይሆን እምነት ላይ ማተኮር አለበት:: ያውም ጥብቅና የማይናወጽ እምነት:: ያኔ ነው ያሻውን በእጁ የሚያስገባው:: ለእምነት ደግሞ ክፍት አዕምሮ ወሳኝ ነው:: የዝግ አዕምሮ ባለቤቶች ለማመን አይነሸጡም፤ ናፖሊዮን እንደሚለው:: ምናብ ዕቅዶች የሚፈጠሩበት ዎርክሾፕ ነው ይላል – ሂል:: ፍላጐትህ መልክና ቅርጽ የሚይዘው እንዲሁም ወደ ተግባር የሚለወጠው በምናብህ እገዛ ነው:: በምናብህ የቀረጽከውን ማናቸውንም ነገሮች መፍጠር ወይም ማድረግ ትችላለህ::

ለተግባር ቸልተኛ ከሆንክ የምናብህ አቅም እየተዳከመ ሊመጣ ይችላል:: ሙሉ በሙሉ ባይሞትም ለጊዜውም ቢሆን ያንቀላፋል:: ሆኖም ጥቅም ላይ ስታውለው ከእንቅልፍ ሊነቃና ሊታደስ ይችላል:: ራስህን ካላሸነፍክ በራስህ ትሸነፋለህ ይላል – ናፖሊዮን ሂል በመጽሐፉ:: የውድቀት ዋና ሰበቡ ለውሳኔ ዳተኛ መሆን ወይም መወሰን አለመቻል ነው:: የሌሎች ሃሳብ ወይም አስተያየት ተጽእኖ የሚያሳድርብህ ዓይነት ሰው ከሆንክ የራስህ ፍላጐት አይኖርህም:: የራስህን ውሳኔ በመወሰንና በመከተል ለራስህ ፍላጐት ተገዢነትህን አሳይ:: የራስህ ሃሳብና አዕምሮ እንዳለህ አትዘንጋ፤ ስለዚህም ተጠቀምበት::

በእርግጠኝነትና በፍጥነት ውሳኔ ላይ የሚደርሱ ሰዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ ብቻ ሳይሆን ያገኙታልም:: በየትኛውም የሕይወት ዘርፍ ላይ የሚገኙ መሪዎች በፍጥነትና ፈርጠም ብለው የሚወስኑ ናቸው:: ለዚህም ነው መሪ የሆኑት:: የሁሉም ስኬት መነሻ ፍላጐት ነው:: ፍላጐታችን ደካማ ሲሆን ውጤቱ ደካማ ይሆናል:: አንዳንድ ሰዎች ሀብትና ስኬት አጥብቀው ሊፈልጉ ይችላሉ:: ችግሩ ግን ጽናት ይጐድላቸዋል::

የሚፈልጉትን ለማግኘት በሚያልፉት ሂደት በሚገጥማቸው ትንሽ ፈተና ወይም መሰናክል እጃቸውን ይሰጣሉ:: ይሸነፋሉ:: ገንዘብና ሀሃብት ወይም ስኬት ቶሎ የሚሳቡት አዕምሮአቸው እነዚህን ለመቀበል ዝግጁ ወደሆኑት ነው:: ድህነትም የሚሳበው ድህነትን ለመቀበል ዝግጁ ወደሆነው አዕምሮ ነው:: የጽናትን ልማድ ያዳበሩ ሰዎች የሽንፈት ዋስትና አላቸው:: የቱንም ያህል ጊዜ ቢሸነፉ በመጨረሻ የስኬት ጣራ ላይ መውጣታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You