ሩጫና ቱሪዝም በአርባ ምንጭ

ስፖርትና ተፈጥሮ ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው እንደመሆኑ ለጤናማ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም:: በዚህም ምክንያት ዘመናዊነትና ሰው ሰራሽ ችግር ተፈጥሮ ፊቷን ያዞረባቸው ሀገራት አትሌቶች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን ለልምምድ ይመርጣሉ:: ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያዘጋጁም የተበከለ አየርን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከተፈጥሯዊው ሁኔታ ጋር በማላመድ ሥራ ይጠመዳሉ::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ተፈጥሮንና ስፖርትን ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ ይገኛል:: በተፈጥሮ ከታደሉ አካባቢዎች አንዱ በሆነው አርባምንጭ ስፖርትና ቱሪዝምን ያዋሃደ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ከቀናት በፊት ተካሂዳል::

ስፖርት ቱሪዝም ላይ ከፍተኛ አትኩሮት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ዓላማውን የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያደረገ የሩጫ ውድድር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና ሳፋሪኮም ጋር በመሆን አካሂዷል:: ከዚህ ቀደም በሃዋሳ ሃይቅ ዳርቻ እንዲሁም የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ የአካባቢውን ነዋሪ ያሳተፈና ዓላማውንም ስፖርት ቱሪዝምን ማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማጎልበት የሆነ መሰል የሩጫ ውድድር መከናወኑ የሚታወስ ነው:: አሁን ደግሞ መዳረሻውን በተፈጥሮ ሀብት የታደለችውን አርባ ምንጭ ከተማን በማድረግ ነዋሪውን ያሳተፈ የጎዳና ላይ ሩጫ ተከናውኗል::

‹‹አርባምንጭን አረንጓዴ አድርጎ ማስቀጠል›› የሚል መሪ ሃሳብን ያነገበው ሩጫ፤ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ መርሃግብር የፕላስቲክ ምርት በመቀነስ፣ እጽዋትን በመትከል እና አየርን ሊበክል የሚችል ነገርን በማስወገድ ነፋሻማ ሩጫን ለማካሄድ በሚል በተሳታፊው ከተማዋን በማጽዳት በተራቆተ አካባቢ ችግኝ ተተክሏል:: ከዚህ ባለፈ ከአዲስ አበባ የተጓዙ 60 የሚሆኑ የሩጫ ተሳታፊዎች የዶርዜ አካባቢ ጉብኝት እንዲሁም የእግር ጉዞን አካሂደዋል:: በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የ 7 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድርም የህጻናት ሩጫን ተከትሎ ተከናውኗል:: በአርባምንጭ የመጀመሪያ በሆነው ታላቁ ሩጫ ላይ 2 ሺ700 የሚሆኑ ሰዎች የተካፈሉ ሲሆን፤ ከደቡብ ክልል የተውጣጡ አትሌቶችም የሩጫው አካል ነበሩ::

በዚህም መሠረት መክሊት መኮንን፣ እስራኤል አባተ እና ፋሲካ አየለ በወንዶች እንዲሁም መልካም አጓጉ፣ ታዘበች ተዘራ እና ድንቅነሽ ኦርሳንጎ በሴቶች የሩጫው አሸናፊዎች በመሆን የሜዳሊያ እንዲሁም የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል:: የሩጫው ተሳታፊዎች ደግሞ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የፈረመበት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል::

የሩጫ ውድድሩን በሚመለከትም የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አክሊሉ ታደሰ፤ ሚኒስቴሩ ስፖርት ቱሪዝም ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል:: የአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋም የቱሪዝም መስህብ በሆኑ ተፈጥሯዊና ባህላዊ እሴት ባለቤት እንደመሆኑ፤ በስፖርቱ ዘንድ ትልቅ አውድን ከፈጠረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በመሆን የተዘጋጀ ሩጫ ነው:: ከአዲስ አበባ ባለፈ የሩጫ መርሃ ግብሮችን በክልሎችም በማስፋፋት እየሮጡ ሀገር መጎብኘት የሚቻልበትን ሁኔታ ያለመ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም በአካባቢ ጥበቃ ዐሻራውንም አሳርፏል::

ኦሊምፒክን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ሀገራት ተፈጥሮና ታሪካቸውን በመሸጥ ተጠቃሚ ከሚሆኑባቸው በርካታ እድሎች መካከል አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ነው:: በመሆኑም መንግሥት ለዚህ ዘርፍ፣ ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲሁም ኮንፍረንስ ቱሪዝም ልዩ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፤ በስፖርት ሀገርን ለማስተዋወቅም እየተሠራ ነው:: ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብት በታደለው አርባምንጭና አካባቢውም ‹‹እየጎበኘን፣ እየተዝናናን በሩጫ ጤናችንን እየጠበቅን የሀገራችንን ገጽታ እንሸጣለን›› በሚል ሩጫው እንደሚካሄድም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል::

የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው፤ የሩጫው መሪ ሃሳብ የሆነው ‹‹አርባምንጭን አረንጓዴ አድርጎ ማስቀጠል›› የከተማዋን የተፈጥሮ መስህብ በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀዋል:: የከተማዋ ውበት የሆነውና በአካባቢው የሚገኘው ጥብቅ ደን፣ የከተማዋ መጠሪያ ለመሆን የቻሉት ምንጮች፣ ሃይቆች እና አጠቃላይ ተፈጥሯዊ ሀብቷን በቱሪዝም መስህብነት ለማስቀጠል የአካባቢ ጥበቃ መሠረታዊ ነው:: ሩጫም ያልተበረዘውን የአካባቢውን ማህበራዊ አኗኗር እንዲሁም ሰላምም ይበልጥ አጉልቶ የሚያሳይ ነው:: ሩጫውን ተከትሎ ወደከተማዋ የሚጓዘውን ቱሪስት በመቀበል እንዲሁም በሩጫው መካሄድም የከተማዋ ነዋሪ እጅግ ደስተኛ እንደሆነም ገልጸዋል::

ከ10 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማዋ ውድድር ያዘጋጀ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም ድጋፍ ላደረጉ አካላት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዳግም ተሾመ ምስጋናቸውን ገልጸዋል:: ውድድሩ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው ሩጫዎች መካከል አንዱ ሆኖ የሚቀጥልም ይሆናል:: ለዚህም በከተማዋ የሚገኙ ወጣቶችን አሠልጥኖ አዘጋጅቷል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You