‹‹ጦሩ››- የኢትዮጵያ ስፖርት የጀርባ አጥንት

በ1936 ዓ.ም የተመሠረተው እና ሀገራቸውን ወክለው በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች መወዳደር የቻሉ ብርቅዬ ጀግና አትሌቶችን፣ እግር ኳስ ተጫዎቾችን እና ሌሎች ስፖርተኞችን ማፍራት የቻለ የማይረሳ ታሪክ ያለው አንጋፋ ክለብ ነው፣ መቻል። ለሰማንያ ዓመታት አንጋፋነቱን አስጠብቆ የዘለቀ በየጊዜው ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ሠሪዎችን በታሪክ ማኅደር አስፍሮ ዛሬም በሀገራችን የስፖርት ዘርፍ የበኩሉን ዐሻራ እያሳረፈ ነው።

ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርት ጋር እኩያ ሊባሉ ከሚችሉ ክለቦች መካከል መቻል ተጠቃሽ ነው። የሃገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባለፈ በዓለም አቀፍ አደባባይ የስኬት ታሪክን የሚጋራው ጦሩ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት በመትጋት ላይ ይገኛል። በ1936 ዓ.ም. ምሥረታውን ያደረገው አንጋፋው መቻል የ80ኛ ዓመት በዓሉን ባለፈው አንድ ወር ‹‹መቻል ለኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበረ ዛሬ በድምቀት ያጠናቅቃል።

‹‹ጦሩ›› የሚል ቅጽል የሚታወቀው ክለቡ እንደየወቅቱ ጠቅል፣ መቻል፣ ፋና፣ ፀሐይ ግባት፣ መከላከያ፣ ማዕከላዊ ዕዝ፣ ጦር ሠራዊት፣ ምድር ጦር፣ አየር ኃይል፣ ባሕር ኃይል፣ …የሚሉ መጠሪያዎችም ነበሩት። ከምሥረታው ጥቂት ዓመታት በኋላ ከ1948 አንስቶ በተለያዩ ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች በመሳተፍም ራሱን ብቻ ሳይሆን ሃገርንም ያስጠራና አሁንም በዚያው ሁኔታ ለመቀጠል በጥረት ላይ ያለ ክለብ ነው።

በተለይ በአትሌቲክስ እና እግር ኳስ ስፖርቶች ዘመናትን የተሻገረ ዝናን የገነባ ቢሆንም፤ መረብ ኳስ፣ ቦክስ፣ ብስክሌት፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ውሃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስ እና ክብደት ማንሳት ስፖርቶችም በውድድሮች ላይ ይካፈል ነበር። ከሜልቦርን ኦሊምፒክ አንስቶ ኢትዮጵያን በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ያስጠራው ሻምበል አበበ ቢቂላን ጨምሮ፤ ባሻዬ ፈለቀ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ እሸቱ ቱራ፣ ቶሎሳ ቆቱ፣ መሐመድ ከድር እና ሃዲስ አበበን የመሳሰሉ አትሌቶች የውትድርናው ዓለም ለኢትዮጵያ ያበረከታቸው ቀደምት ዕንቁዎች ናቸው። አሁንም አትሌት ኢማና መርጋ፣ አሊ አብዶሽ፣ ሱሌ ኡቱራ፣ ደረሰ መኮንን፣ ድሪባ ጋሪ፣ አልማዝ አያና፣ ሙክታር እድሪስ፣ ፀጋዬ ከበደ፣ ቲኪ ገላና፣ ኢብራሂም ጄይላን፣ ጌታነህ ሞላ እና ሃዊ ፈይሳን የመሳሰሉ አትሌቶች ባለቤት ነው ክለቡ።

መቻል በእግር ካሱ በተለይም በ1989 ዓም የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ፌስቲቫል መካሄዱን ተከትሎ ተጫዋቾችን በማሰባሰብ በ1990 ዓ.ም. መከላከያ በሚል ስያሜ በድጋሚ ተዋቀረ። በአዲስ መልክ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላይ ቢጫወትም በዚያው ዓመት ሻምፒዮን በመሆኑ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ሊያድግ ችሏል። እስከ 1993 ዓም ባለው ጊዜም ፋና እና ፀሐይ ግባት በሚል ስያሜ በድጋሚ ተከፍሎ በብሔራዊ እና ከፍተኛ ሊግ ሲጫወቱም ቆዩ። በ1996 ዓ.ም. ድጋሚ ክለቦቹ መከላከያ በሚል ተዋሕዶ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውን ጀመረ።

የመቻል ዋናው እግር ኳስ ቡድን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲሱ ፎርማት ለረጅም ዓመታት ከቆዩት ክለቦች መካከል አንዱ ሊሆን ችሏል። በእነዚህ ዓመታትም ባለፈው ሳምንት ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰበት ውጤት ከፍተኛው ቢሆንም በደረጃ ሰንጠረዡ መካከለኛ ስፍራ ላይ የሚቀመጥ ክለብ ነው። በተለይ ከሊጉ ተሳታፊዎች ክለቡን ለየት የሚያደርገው አንድም የውጪ ተጫዋች ባለማስፈረምና በሃገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ በመገልገሉ ነው። የግብ ጠባቂ እጥረት ያለበት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያማትረው ወደዚሁ ክለብ ነው። ለአራት ጊዜያት ያህልም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን በመሆን ለአራት ጊዜ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑ አንዱ ስኬቱ ነው።

የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ለዓመታት በነገሠበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስሙ ሳይነሳ የቆየውም መቻል ነው። እንዲያውም ስፖርታዊ ጨዋነትን በማስፈን ረገድ ተጫዋቾች የሚወጡት ሚና የሚያስመሰግን ነው።

ስለ መቻል ሲነሳ ብዙ ጊዜ የምንሰማው በሁሉም ዓይነት ማለትም እግር ኳስን ጨምሮ በአትሌቲክስ የተለያዩ ርቀቶች ሀገራቸውን ወክለው በሁለቱም ፆታ በድል የደመቁ ስፖርተኞችን ነው። ይህ ተደጋግሞ መነሳቱ መልካም ሆኖ ሳለ ከተወዳዳሪና ባለድሎች ባሻገር በርካታ የስፖርት ፈርጥ የሀገር ገጸ-በረከት የሆኑ የስፖርት ባለሙዎችን በማፍራት ረገድ ጉልህ ሚና አለው።

ከአሠልጣኞች ጀምሮ በሁሉም የስፖርት ዓይነት በእያንዳንዷ ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች የስፖርት ጠቢባን የሆኑ ሙያተኞችን መቻል ስፖርት ክለብ በማፍራት ከራሱ አልፎ ለሀገር ትልቅ ውለታ ውሏል እየዋለም ይገኛል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You