ካንሰርን – በአሸናፊነት

ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል። ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።

የመርካቶዋ ጭምት

የመሀል መርካቶ ልጅ ናት። ውክቢያ ግርግር ከበዛበት፣ የሰዎች አጀብ ከሚታይበት ደማቅ ሰፈር አድጋለች። መርካቶ የበርካቶች መገኛ፣ የብዙሀን ንግድ መናሀሪያ ነው። የአካባቢው ጎዳና ጭርታን አያውቅም። ሁሉም በግፊያና ትግል ሲሮጥበት ይውልበታል።

ፍቅርተ አለማየሁ /ስሟ የተቀየረ/ ባህርይዋ እንደሰፈሯ አይደለም። ዝምተኛና ጭምት ነበረች። ለቤቱ የመጀመሪያ ናትና የወላጆቿ ዓይን ያርፍባታል። ከድሀ ቤተሰብ ብትገኝም አባቷ ስለእሷ ያላቸው ግምት ለየት ይላል። አቅማቸው ባይፈቀድም ከእኩዮቿ እንዳታንስ ከፍለው ያስተምሯታል። ጠዋት ማታ እጇን ይዘው ትምህርት ቤት አድርሰው ይመልሷታል።

የዛኔዋ ትንሽ ልጅ አድጋ ትምህርቷን እስክትጨርስ ባህርይዋ አልተለወጠም። ዛሬም ጭምትና ዓይናፋር ነች። ወላጆቿ ጌጥ ውበት ሳያምራቸው ስለእሷ ዋጋ ከፍለዋል። በተለይ አባቷ ቁምነገር ደርሳ እንዲያዩ ምኞታቸው ነበር። ፍቅርተ አላሳፈረቻቸውም። በትምህርቷ በርትታ፣ በጉብዝናዋ ስማቸውን አስጠራች። ዕድሜዋ ከፍ ማለት ሲይዝ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ተመረቀች። ይህኔ ወላጆቿ ደስታቸው ጨመረ። ልፋት ድካማቸው ፍሬ ይዟልና ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ።

ፍቅርተ ትምህርቷ እንዳበቃ በተማረችበት ዘርፍ ስራ አግኝታ ተቀጠረች። እንዲህ መሆኑ ራሷን እንድትጠብቅ፣ ቤተሰቧቿን እንድታስብ ዕድል ቸራት። ከእጇ የገባው ገንዘብ ቁምነገረኛነቷን አጎላው። የቢሮ ሰራተኛ ሆና ደሞዝተኛ ተባለች። ልጅነቷ አበቃ፣ በዝነጣ ቦርሳ አንግታ ስራ መመላስ ያዘች።

ሶስት ጉልቻ

አሁን ፍቅርተ ውበቷ አብቧል። ወጣትነቷ ከብዙዎች ዓይን እየጣላት ነው። ይህ ዕድሜ ለብዙ ወጣቶች ፈተና ይሆናል። ፍቅርተ ግን የልጅነት ባህርይዋ ከእሷ እንዳለ ነው። ዛሬም እንደትናቱ ጨዋና ጭምት ነች። ይህ ባህርይ ከሌሎች አስመረጣት። እሷን ያሉ ዓይኖች ከዓይኖቿ አርፈው ከውሀ አጣጪዋ ተገናኘች።

ፍቅርተ ትዳር መስርታ ጎጆ ስትወጣ ከቤተሰቦቿ ራቀች። ዛሬ አስራ አምስት ዓመታት ከቆጠረችበት ጥምረት ሁለት ልጆች አፍርታለች። ከባለቤቷ ጋር ተዋደው፣ ተከባብረው ይኖራሉ።

ፍቅርተ በምትሰራበት የመንግስት መስሪያቤት ከበርካቶች ጋር መግባባት ልማዷ ነው። ያየችውን ታከብራለች። የቀረበችውን ትወዳለች። ኑሮና ትዳሯን የምታከብረው ወይዘሮ በሃይማኖት የበረታች፣ በዕምነቷ የጸናች ናት። ጠዋት ማታ ስለሆነላት በጎነት ለአምላኳ ምስጋናን አታጓድልም።

አንድ ማለዳ …

ጊዜው የሐምሌ ወር መጀመሪያ ነው። ማለዳው በዳመና ተይዞ ሰማዩ መጥቆር ጀምሯል። ‹‹መጣሁ›› እያለ የሚያስፈራራው ዝናብ ቀኑን ለማክበድ እንዳሰበ ያስታውቃል። ከአልጋ ለመልቀቅ የሚፈትነው አየር ከቤት ለመውጣት አያስመኝም። ፍቅርተ ከሞቀ አልጋዋ የቀሰቀሳት እንደልማዷ ስራ መሄዷ ነበር። ጉዳይዋ ግን ይህ ብቻ አልሆነም። ደርሶ ከብብቷ ስር የሚሰማት ሕመም ሰላም ይነሳት ይዟል።

ቀኝ እ ጇን ወ ደ ግ ራ ብ ብቷ ሰ ዳ ቀ ስ ብ ላ ዳሰሰችው። አንዳች ነገር ጣቷ ላይ ጎርበጥ ሲል ተሰማት። ደነገጠች። በሃይማኖቷ የጸናች ናትና ቤት ካኖረችው የቤተክርስቲያን ዕምነት አንዱን አንስታ ተቀባባች።

ቢሮ ስትገባ ስለሁኔታው እያሰበች ነበር። እየቆየ የሚጠዘጥዛት ነገር አሁንም አልተዋትም። ስሜቱ እየጨመረ ሲሄድ ለቅርብ ባልንጀራዋ አዋየቻት። ባልንጀራዋ ልብሷን ገልጣ አየችና ድንገት የሚያጋጥም የዕጢ መቆጣት መሆኑን ነገረቻት። ፍቅርተ ለጊዜው እንደመረጋጋት ብላ ስራዋን ቀጠለች።

ፍቅርተ ዕለቱን ከጓደኛዋ ጋር ቤተክርስቲያን ለመሳለም ሄደች። በስፍራው ደርሳም ‹‹ይበጃል›› ያለችውን ሁሉ አደረገች። ዕለተ ዓርብ አልፎ ቅዳሜ ተከተለ። ዕሁድ ማለዳ ገላዋን ታጥባ ልብሷን መልበስ ስትጀምር አንዳች ነገር ጡቷን ሲከብዳት ተሰማት።

ለአፍታ በዓይምሮዋ ብልጭ ያለው ስሜት ፈጥኖ ከውስጧ ተመላለሰ። ግራ ጡቷ ላይ እየጠዘጠዘ ሰላም የነሳት ሕመም የጤና አለመሆኑን ጠረጠረች። ፍቅርተ ከልጅነቷ ጀምሮ ስትሰማው የኖረችው አንድ እውነት በየአጋጣሚው ሲረብሻት ኖሯል። የጡት ሕመም ይሉትን ጉዳይ አጥብቃ ትፈራዋለች። ከዚህ ችግር ጋር አብሮ የሚነሳው ‹‹ካንሰር›› የተባለ ሕመም ደግሞ አደገኛ መሆኑን አሳ ምራ ታውቃለ ች።

ፍቅርተ ስለራሷ ብዙ እያሰበች ጡቷን በዝግታ ዳሰሰች። ከላይ ከታች እያለች ጣቶቿን አመላለሰቻቸው። ከዚህ በፊት አይታው፣ ነክታው የማታውቅ ዕባጭ ነገር ከመዳፏ ሲገናኝ ተሰማት። በድንጋጤ ክው እንዳለች በዝምታ ተዋጠች።

ማግስቱን…

ዕለተ ሰንበት እንደምንም መሽቶ ነጋ። ሰኞ ቀን ስራዋ ስትደርስ የጀመራት ሕመም ተባብሶ ነበር። አሁን ፍቅርተ ሕመሟን ውጣ የምትደብቀው አልሆነም። እየሆነ ያለውን ሁሉ ለሌሎች ማጋራት አለባት። ሁኔታዋን ያስተዋሉ፡ ችግሯን የተጋሩ ለመፍትሄው ተጣደፉ። አሉ የተባሉ የሕክምና ዶክተሮችን ፈልገው አገናኝዋት።

ለአጠቃላይ ምርመራ ከሀኪም ዘንድ ተገኘች። አሁንም ውስጧ ስለጡት ሕመም የሰማችውን ሁሉ እያመላለሰ ያስጨንቃታል። ከዚህ ቀድሞ በጡቷ ላይ አንዳች ሕመም ተሰምቷት አያውቅም። በእርግጥ አንዳንዴ ራስ ምታት ያስጨንቃታል። ዶክተሩ ምርመራውን አጠናቆ ሊነግራት ሲዘጋጅ የፊቱን ገጽታ በጥንቃቄ ማንበብ ጀመረች።

እሱ ቃል ከማውጣቱ በፊት የሚለውን ገመተች። አሁንም ፊቱ መልካም ነገር አላሳያትም። አስተውላ አየችው። የፈራችው አልቀረም። ዶክተሩ በጡቷ ላይ የሚታየው ውጤት ችግር እንዳለበት የሚያመላክት መሆኑን ነገራት።

የብርታት ጅማሬ …

ፍቅርተ ውጤቱን እንደሰማች ራሷን ማጽናናት፣ ማበርታት ያዘች። እስከዛሬ የፈራችው፣ በሌሎች ሲደርሰ ያየችው ሕመም ከእሷ ጋር እንዳይሆን እየሰጋች ነው። እንዲህ በተሰማት ጊዜ ዕምነቷን በፈጣሪ ትታ ውስጧን አበረታች። ወዲያው እንደብረት የጠነከረ ጽናት በልቧ ሲፈስ ተሰማት።

ምርመራውን ያካሄደው ዶክተር ያሬድ ከጎኗ ለመሆን የቻለውን አደረገ። ቅንነቱ አግዟት ለቀጣዩ ሂደት አዘጋጃት። የናሙና ምርመራውን ለማካሄድ መፍጠን ነበረባት። ሁኔታዎች ግን እንደታሰቡት አልሆኑም። ይህን ለማድረግ ረዘም ያለ ቀጠሮ ተሰጣት። ፍቅርተ በሁኔታው ብታዝንም ተስፋ አልቆረጠችም። ዶክተር ያሬድ ተመለሺ ባላት ቀን በስፍራው ተገኘች። ሀኪሙ ተጣድፎ የናሙናውን ውጤት እንድትሰጠው ጠየቀ። እንደከፋት ስለቀጠሮው መራዘም አስረዳችው። ውስጡ እያዘነ ለሌላ መፍትሄ ተጣደፈ። ጊዜ አልወሰደም። ዳግም የሕክምና ማዘዣውን ጽፎ ሰጣት።

ከሶስት ቀናት በኋላ ውጤቱን ይዛ ከፊቱ ቀረበች። ዳግም በዶክተሩ ገጽታ የሚያስደነግጥ ምልክት ያስተዋለችው ወዲያው ነበር። እሱ አሁን ይበልጥ እርግጠኛ የሆነበት የናሙና ውጤት ከእጁ ገብቷል። በአንደበቱ ‹‹አዎ ! የጡት ካንሰር ነው›› ለማለት ግን አልደፈረም።

ከሁኔታው ምላሽ ያገኘችው ፍቅርተ ለዶክተሩ እንዳይጨነቅ ነግራ የመጣውን ሁሉ በበጎነት በፀጋ እንደምትቀበል አሳወቀችው። ብርታት ጥንካሬዋን ያስተዋለው ሀኪም በሁኔታዋ ተደነቀ። ይህ እውነትም ልቡን ለበጎ አዘጋጅቶ ለሌላ መፍትሄ ከሌላ ሀኪም እንድሄድ መንገድ መራት።

ከካንሰር ጋር ፍልሚያ …

ፍቅርተ የቀጣዩን ሀኪም ስም በልቧ እንደያዘች ወደ ፀበል አመራች። ለእሷ ልክ እንደ ሕክምናው የዕምነት ፅናቷ ያስፈልጋታል። ሁለቱንም ጎን ለጎን ሳትለያይ መቀጠል እንዳለባት ወስናለች።

ባለቤቷ በእሷ ላይ የሆነውን ባየ ጊዜ በእጅጉ አዘነ። እስካሁን ላይሆን ይችላል ብሎ የተጠራጠረበት ጉዳይ አሁን በሕክምናው ዕውን ሆኗል። ይህን ሲረዳ ከጎኗ ሊሆን ተዘጋጀ። በወቅቱ ፍቅርተ ሕክምናውን የጀመረችው ዶክተር እንግዳ ከሚባል ሀኪም ዘንድ ነበር። እሱም እንደቀድሞው ሀኪም በመልካም ትህትና ተቀብሎ አስተናገዳት።

ፍቅርተ በጡቷ ላይ የተከሰተው ካንሰር ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯታል። እሷ በወቅቱ ስለበሽታው ከመጨነቅ ለመፍትሄው ታደላ ነበር። ስለህመሙ የሚነገሩ፣ መረጃዎችን በመከታተል ግንዛቤ ለመውሰድ ትጥራለች። ሕጻናት ልጆቿ እንዳይጨነቁና ቤተሰብ እንዳያዝን ራሷን ቀድማ ታበረታለች።

አካልን በስንብት …

ውሎ አድሮ ወይዘሮዋ ከራሷና ከባሏ ተማከረች። ከሀኪሞች ተነጋግራም ከውሳኔ ደረሰች። ለቀናት ከሆስፒታል ተኝታ በቀዶ ሕክምና ግራ ጡቷ እንዲወገድ ሆነ። ለሴት ልጅ ጡት ማለት የማንነቷ ምልክት፣ የጾታዋ መለያ ነው። ከውበት አልፎ እናትነቷን የምትቸርበት በረከቷ ጭምር።

ፍቅርተ ይህ አካሏ ተቆርጦ ሲወገድ እንደሴት፣ ብሎም እንደ እናት ለአፍታ ‹‹ሽው›› ያለባት ስሜት አልጠፋም። እንዲያም ሆኖ ስሜቱ አብሯት አልቀጠለም። ሁሉን ትታ ፈጣሪን ለማመስገን አልዘገየችም። ለእሷ ሕመሟ ታውቆ ለሕክምና መድረሷ ብቻ ታላቅ ጸጋ ነው። ዛሬም ‹‹ሁሉም ለበጎ ነው›› ባይነቷ ማንነቷን አጽንቷል።

እንዳያልፉት የለም የ‹‹ ኬሞ›› ፈተና …

በቀዶ ሕክምና አንድ ጡቷ ከተወገደ በኋላ ቀጣዩ ሂደት የጨረርና የኬሞ ቴራፒ ሕክምና ነበር። ፍቅርተ ይህ አይነቱ ሂደት በእጅጉ ፈትኗት አልፏል። ዛሬ ላይ ሆና ያን ጊዜ ስታወሳው የመድሀኒቱን ክብደት ገድሎ እንደማንሳት ትቆጥረዋለች።

ፍቅርተ ሕክምናውን ስትወሰድ በእጅጉ ይደክማት ነበር። የምግብ ፍላጎት ማጣት ማስመለስና ሌሎች ችግሮችም ፈትነዋታል። በዚህ ወቅት ጥፍርና ጸጉር ይሏቸው አብረው እንዳልተፈጠሩ ይክዳሉ። ሰውነት ይዝላል፣ ማንነት ይሸሻል። መልካም ባህርይን ይለውጣል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ከጎኗ የነበሩ ቤተሰቦቿና የመስሪያቤት ባልደረቦቿ ሕመሟን እንድትረሳ ከጎኗ ቆመዋል። በጎዶሎዋ ተገኝተው ሙላት በረከት ሆነዋታል። ‹‹አይዞሽ፣ አለንሽ›› ሲሉ ዕንባዋን አብሰዋል። ይህ ወቅት ከማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጋር የተገናኘችበት ነበር። ተቋሙ በወቅቱ አስፈላጊ የሕክምናና የመድሀኒት እገዛ አድርጎላታል። የባለሙያ ምክር ባስፈለጋት ጊዜም ከጎኗ ተገኝቷል። በተለይ በዘመነ ኮረና ሶሳይቲው ያለውን አካፍሎ ሕይወቷን መታደጉን ፈጽሞ አትረሳውም።

ፍቅርተ በስምንት ተከታታይ ዙር የወሰደችውን ‹‹ኬሞ ቴራ›› በብዙ ውጣውረድና ፈተና በድል አጠናቀቀች። ይህ ጥንካሬዋ ዛሬን በሕይወት እንድትቀጥል ነገን በተስፋ እንድታስብ ዕድል ችሯታል። ለዚህ ማንነቷ ከጎኗ የነበሩ የስራ ባልደረቦቿ ከልቧ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላቸው። ፍቅርተ ከእሷ ጋር ሕክምናውን የጀመሩ ብዙዎች ዛሬ በሕይወት እንደሌሉ ታውቃለች። ይህን እውነት መለስ ብላ ስታስበው ፈጣሪን ከማመስገን በላይ ቃል የላትም።

ዛሬና ትናንት …

አሁን ወይዘሮዋ በሕክምናው ያለፈችበት መንገድ ተቋጭቶ፣ በመልካም ጤንነት ቆማለች። ትናንት የተጎዳ አካሏ ወዝ ተመልሷል፤ የረገፈ ዞማ ጸጉሯ እንደ አዲስ በቅሎ ውበት አላብሷታል።

ስለጡቷ እንዲህ ነው ብላ ካላወጋች ለምን የሚያስብል ምልክት የለባትም። እንደ ቀድሞው ስራዋ ውላ ትገባለች። ዛሬም የባሏ ሚስት፣ የልጆቿ እናት ከመሆን ያገዳት የለም። ደስተኛና ሰላማዊ ሕይወት እየመራች ነው። ፍቅርተ ዘወትር አመስጋኝ ነች። ሁሌም ከአንደበቷ የፈጣሪ ምስጋና አይጠፋም።

ዛሬም በቋሚነት የምትወሰድውን መድሀኒት ያለመሰልቸት ትጠቀማለች። አሁን ላይ የሚሰማት ሕመም የለም። አንዳንዴ ከሀኪሞች ስትገናኝ ግን ስላለችበት የጤና ሁኔታ አንድ ነገር እንዲሏት ትሻለች። እስከዛሬ ከተለመደው ምርመራ የዘለለ ስለህመሙ የሚያስረዳትን ሀኪም አላገኘችም። መጠየቅ መወያየት ብትፈልግም ይህ አይነቱ ዕድል ያለመኖሩ በጥያቄ ውስጥ እንድትኖር አድርጓታል።

መልዕክት ለሌሎች…

‹‹እኛ ታመን ካልጋ ካልወደቅን በቀር ሀኪም ዘንድ አንሄድም። ማንም ሰው ሕመም በተሰማው ጊዜ ፈጥኖ ሀኪም ቤት የመሄድ ልምድ ሊኖረው ይገባል። ቢቻል ጊዜ ወስኖ በየዓመቱ የጤና ምርመራ ማካሄድ ጥሩ ነው። ውድ ሴቶች ይህ ዓይነቱ ሕመም ቢገጥማችሁ ፈጥናችሁ ተስፋ አትቁረጡ። በሽታው ገዳይ ነው ብላችሁም ቀድማችሁ አትሙቱ። ሁሌም ለመፍትሄው በመትጋት በጥንካሬ መሻገር እንደሚቻል ከእኔ ሕይወት ተማሩ ››

ዛሬ ፍቅርተ የጡት ካንስርን አሸንፋ በድል መራመድ ከጀመረች ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁንም ውስጧ በታላቅ ተስፋ እንደተሞላ ነው። ነገ ለእሷ ብሩህ ሆኖ ይታያታል። ራሷን ትጠብቃለች፣ በፈገግታ ትውላለች። ፈጣሪዋን ደግማ ደጋግማ ታመሰግናለች ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You