አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመን ለመቶ ሊደፍን ከሁለት አስርተ ዓመታት ያነሰ የእድሜ ባለቤትና የሀገሪቱ የመጀመሪያ የህትመት ሚዲያ ነው። በዚህ የእድሜ ዥረት ውስጥ ጋዜጣው ያላለፈበት መንገድ፣ ያልወጣና ያልወረደው ዳገትና ቁልቁለት፤ ባጭሩ፣ ያልሰነደው ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ • • • ስንክሳር የለም።

በመሆኑም፣ በዚህ ገፅ ላይ አዲስ ዘመን ድሮ በሚል አምድ ስር አንዳንድ ያስደመሙንን ፍሬ ከናፍሮች ስንጠቅስ ዓባይን በሻይ ማንኪያና ለቅምሻ ያህል ነው፣ ለዛሬ ሀገር ሀገር፤ ሕዝብ ሕዝብ • • • የሚል ሽታ ያላቸውን ጽሑፎች ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።

ጎሳዎች ተባብረው ለመኖር ተስማሙ

ከከረዩ፣ ከአዳል፣ ከኢቱና ከአሩሲ ጎሳዎች የተውጣጡ በርከት ያሉ የሀገር ሽማግሌዎችና የገበሬ ማኅበራት ሊቃነ መናብርቶች ባለፈው እሑድ በኤችቪኤ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ አዳራሽ ስብሰባ አድርገው በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ በማስቀረት በኅብረተሰባዊነት ፍልስፍና መሠረት በሰላም ተባብሮ ለመኖር ስምምነት በማድረግ አጥፊዎችን ከየመሃከላቸው መንጥሮ የሚያወጣና ለሕግ የሚያጋልጥ ከየጎሣው የተውጣጡ ሽማግሌዎች የሚገኙበት አንድ ኮሚቴ አዋቅረዋል፡፡

(አዲስ ዘመን፣ ህዳር 12 ቀን 1979 ዓ.ም)

በድሬዳዋ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሔደ

ድሬዳዋ (ኢ.ዜ.አ.)፡- በምሥራቅ ጦር ግንባር የዘመተው መደበኛው መለዮ ለባሽ፤ ሚሊሺያው ሠራዊትና አባላት ጦረኛው የአድኃሪው የሶማሌ ገዥ መደቦች ወራሪ ወታደሮች በማንበርከክና ቅስም በመስበር ፍጹም ስትራቴጂካዊ የሆነውን የካራማራ ኮረብታና የጅጅጋን ከተማ በማስለቀቁ የተሰማውን ደስታ በመግለጽ የድሬዳዋ ከተማና የአካባቢው ሕዝብ ከትናንት በስቲያ ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል።

በከተማው ውስጥ በሚገኘው የኮካኮላ ፋብሪካ አጠገብ በሚገኘው አደባባይ ላይ በተደረገው በዚሁ የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የ፳፫ ቀበሌ የሴቶችና የወጣቶች የገበሬዎች ማህበራት አባሎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች የማምረቻና ሰበነክ ወዛደሮች የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት አንቂ ጓዶችና ወታደራዊ ካድሬዎች የፖሊስ አባሎች መምህራን ተማሪዎች በጠቅላላው ቁጥሩ ከ፺፭ሺህ የማያንስ ሕዝብ ተካፋይ ሆኗል።

ከጦር ሜዳ ትግሉ ጀርባ በደጀንነት ተሠልፎ ዘማቹ ሠራዊት አብዮታዊውን ጦርነት በአሸናፊነት እንዲወጣ የሞራልና የስንቅ እርዳታ የሚያደርገው ይኸው የከተማውና የአካባቢው ሕዝብ በየማኅበሩና በየሙያ አርማው ሥር ተሰልፎ ደስታውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በተጓዘበት ወቅት ‹‹አሻግሮ ገዳይ በረሃ ያለውን ጠላቱን ዛሬ አመድ አረገው›› በማለት ወኔን የሚቀሰቅሱ መዝሙሮች ሽለላና ፉከራዎችን አሰምቷል።

(አዲስ ዘመን፣ የካቲት 29 ቀን 1970 ዓ•ም)

ሽፍቶችን ለማስወገድ ፈቃድ ጠየቁ

ሐረር፤ በውጋዴን ግዛት የሚገኙ ባላባቶች ሁሉ ከየጐሣቸው አንዳንድ ታላላቅ ባላባቶች ወደ ሐረር በመላክ ሽፍቶቹ በሀገራቸው ላይ ስለሚያደርጉት ጉዳት አሳባቸውን ለጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ ለክቡር ሌተና ኰሎኔል ታምራት ይገዙ እንዲገልጹላቸው አድርገዋል፤ የተላኩት ባላባቶችም መስከረም ፫ ቀን ፶፮ ዓ.ም ወደ ክቡር እንደራሴ ቀርበው የተሰጣቸውን እምነትና አደራ የረሱ ከሃዲዎች በሀገራችን ላይ በመሸፈት ሀገራችንን ከማጥፋት በላይ በንብረታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱብን ተባብረን ለማጥፋት ቆርጠን የተነሳን ስለሆነ፤ መንግሥታችን ይህንኑ እንዲፈቅድልን እንለምናለን:: ሽፍቶቹም ተወላጆቻችን አይደሉም በማለት አሳባቸውን ገልጸውላቸዋል::

ክቡር እንደራሴውም አሳባቸውን ካዳመጡ በኋላ፤ ሰው ሆኖ የማያጠፋ የለም፤ ቢቻል በምክር ውንብድነታቸውን ቢተዉ ምከሩአቸው፤ ካልሆነ እያንዳንዳቸው እጃቸውን እየያዛችሁ ለመንግሥታችሁ ብታስረክቡ መልካም ነው፤ በማለት መልስ ስለሰጡዋቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ተመልሰዋል። ከባላባቶችም የቀብሪ ደሐር አውራጃ ግዛት ሕዝብ እንደራሴ ቀኛዝማች አሙመር ባራሌ፤ የቀላፎ አውራጃ ገዥ ቀኛዝማች በሽር ሴክ አብዲ፤ የሬርሬር ወረዳ ግዛት ገዥ፤ አቶ መሐመድ ባሂርና ሌሎችም እነሱን የመሳሰሉ ተገኝተው ነበር ሲል በጠቅላይ ግዛቱ የሚገኘው ወኪላችን አስታውቋል፡፡(አዲስ ዘመን፣ መስከረም 5 ቀን 1956 ዓ.ም)

የ፻ አለቃ ግርማ ወ. ጊየርጊስ በኢንተር- ፓርላማ ጉባዔ

የኢትዮጵያ የሕግ መምሪያ ፕሬዚዳንት የተከበሩ የ፻ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለ፶፪ኛው የኢንተር-ፓርላማ ጉባኤ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል::

የተከበሩ የ፻ አለቃ ግርማ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር፤ ዮጎዝላቪያ ስላደረገችላቸው መልካም አቀባበል ከአመስገኑና በእስኮፔጅ ስለደረሰውም አሰቃቂ ጥፋት የተሰማቸውን ቅሬታ ከገለፁ በኋላ፤ ‹‹ብዙ የአፍሪቃ አገሮች የራሳቸውን ጉዳይ ራሳቸው ለመወሰን የሚያደርጉት አስደናቂ ጥረት፤ አፍሪቃውያን ራሳቸውን ለማስተዳደር አልበቁም የሚለውን መሠረተ ቢስ ሀሜት የሚያስተባብል ነው›› ብለዋል። እንደዚሁም የአዲስ አበባው ከፍተኛ ጉባዔ በአፍሪቃ ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የተከበሩ የመቶ (፻) አለቃ ግርማ፤ ስለ ኑክሊየር በመስኮብ የተደረገው ውለታ አንድ ጥሩ ውጤት መሆኑን ከገለጡ በኋላ ሌላው የሰላም አስጊ ጉዳይ ደግሞ የዘርና የቀለም ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል። ፕሬዚዳንት ኬኔዲ የቀለምን ልዩነት ለመደምሰስ የሚያደርጉትን ጥረት የመቶ አለቃ ግርማ አመስግነዋል፡፡

የደቡብ አፍሪቃ ሁናቴ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መሄዱን በመግለጥ፤ በደቡብ አፍሪካ መንግሥትና በፖርቱጋል አገዛዝ ሥር በሥቃይ የሚገኙት አፍሪቃውያንን ለማዳን የፓርላሜንት አባሎች ሁሉ የተቻላቸውን ያህል እንዲረዱ መቶ አለቃ ግርማ ጠይቀዋል፡፡

(አዲስ ዘመን፣ መስከረም 12 ቀን 1956 ዓ.ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 /2016 ዓ.ም

Recommended For You