አቶ ተስፋዬ ፍቃዱ በስማቸው የተሰየመ የኦቾሎኒ ቅቤ ማኑፋክቸሪንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በኦሮሚያ ክልል ፍቼ ከተማ ተወልደው ያደጉት የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በፍቼ ከተማ ተከታትለዋል። ቤተሰቦቻቸው በንግድ ሥራ የተሠማሩ በመሆናቸው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ቤተሰቡን በንግድ ሥራ የማገዝ ግዴታ ነበረባቸው። ገና ከልጅነታቸው ጀምረው የቤተሰቡን የንግድ ሥራ እየሠሩ ማደጋቸውም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡
ታዲያ በቤተሰብ እቅፍ ሆነው ገና በልጅነት በንግድ ሥራ እውቀት ተኮትኩተው ያደጉት አቶ ተስፋዬ፤ ችሎታቸውን በቤት ውስጥ ብቻ ሊገድቡት አልፈቀዱም። በተፈጥሮ ባላቸው የሥራ ፍቅርና አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት በቤት ውስጥ ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩትን የንግድ ሥራ ዛሬ ከኢንቨስትመንት ተርታ አሰልፈውታል። ወደ ኢንቨስትመንት ማደግ የቻለው የንግድ ሥራም ትልቅ ራዕይ የሰነቀ በመሆኑ ወደፊት በብዙ እጥፍ የማደግና አዳዲስ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ገበያ የማውጣት እንዲሁም ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር ህልም ሰንቋል።
‹‹ነብስ ሳውቅ ጀምሮ የንግድ ሥራን ከቤተሰብ ጋር ሥሰራ አድጌያለሁ›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ የሥራ ክቡርነትን ከቤተሰቦቻቸው መማር እንደቻሉም ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ቤተሰባቸው ነጋዴ በመሆናቸው እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ልጅ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ቤተሰቡን በሥራ እያገዘ ነው ያደገው። ዕድሜው ለሥራ የደረሰ ሰው ሁሉ በቤት ውስጥ ሥራ እየሠራ የሚያድግ ሲሆን በምላሹም ደመወዝ ይከፈለው እንደነበር ይገልፃሉ። በዚህም ወቅት ታዲያ የሥራ ክቡርነትን፤ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስንና ቁጠባን ጭምር እንደተማሩ አጫውተውናል።
ከቤተሰብ ጋር እያሉ ጀምሮ ለሚሰሩት ሥራ ደመወዝ የሚከፈላቸው አቶ ተስፋዬ፤ የንግድ ሥራውን የማሳደግና አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ውስጣዊ ፍላጎት ነበራቸው። ይህ ፍላጎታቸውም ከቤተሰብ በወረሱት የሥራ ፍቅርና ክቡርነት ጋር በማዋሃድ ዛሬ ላይ የፋብሪካ ባለቤት አድርጓቸዋል። ለዚህም ቤተሰባቸው ትልቁን ሚና የተጫወቱ ቢሆንም፤ አዳዲስ ነገሮችን የማወቅና የመሞከር ፍላጎት እንዲሁም ጉጉታቸው፤ የሥራ ክቡርነትን የመረዳት አቅማቸውና የቁጠባ ባህላቸው ጭምር ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው።
ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው በተጨማሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንዲሁም ኤሌክትሪካል ሜካኒካል ትምህርት የተከታተሉት አቶ ተስፋዬ፤ ተወልደው ያደጉባት እንዲሁም የተማሩባት ፍቼ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴዋ ቀዝቃዛ እንደሆነና ብዙም ሀብት የሌላት እንደሆነች እየሰሙ አድገዋል። ያም ቢሆን ታዲያ የግል ሥራ ከመሥራት አላገዳቸውም። ምክንያቱም ‹‹ሀብት ያለው በእያንዳንዳችን አዕምሮ ውስጥ ነው። ያንን አውጥቶ የመጠቀም የኛ ኃላፊነት ነው›› የሚል ጠንካራ ዕምነት አላቸው። በመሆኑም ከትምህርት በኋላ በቀጥታ የራሳቸውን ሥራ መፍጠር እንጂ ተቀጥሮ መሥራትን አልተመኙም።
እናም ‹‹የንግድ እንቅስቃሴዋ ቀዝቃዛ ነው›› ተብሎ በሚነገርላት ፍቼ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ተስፋዬ፤ ሌት ተቀን በመሥራት ግዙፉን የኦቾሎኒ ቅቤ ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ጊዜ አላጠፉም። እርግጥ ነው ፋብሪካውን ከመገንባታቸው አስቀድመው የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ሞካክረዋል። በፍቼና አካባቢዋ የለውዝ ምርት ባይመረትም ጥሬ ዕቃውን ካለበት አምጥቶ እሴት በመጨመር ማምረት ብሎም ለገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ሙሉ ዕምነት ነበራቸው።
የለውዝ ቅቤን ከማምረታቸው አስቀድመው የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን የሠሩ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ቡና ላይ እሴት በመጨመር ቡናን በማሽን ቆልቶና አሽጎ ለካፌዎች ማቅረብና ለውዝ ላይም እንዲሁ እሴት በመጨመር በየካፌው የሚገኘውን የለውዝ ሻይ እና የለውዝ ማኪያቶ አዘጋጅተዋል። ከልጅነት ጀምሮ በሥራ ያደጉት አቶ ተስፋዬ፤ ከትንሽ የጀመሩት የንግድ ሥራና የቢዝነስ ሃሳብ አሁን ላይ ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤን ፍቼ ከተማ ላይ በማምረት በተለያ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ችለዋል። በቀጣይም ከሀገር ውስጥ ባለፈ ምርቱን በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የማድረስ ትልቅ ራዕይ አላቸው።
በ2003 ዓ.ም በጥቂት የሰው ኃይልና አነስተኛ አቅም ባላቸው ማሽኖች የተመሠረተው ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤ፤ አሁን ላይ ለ170 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለና ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢንቨስትመንት ደረጃ አቅሙን ማሳደግ የቻለ አምራች ድርጅት ነው። ከከተማ አስተዳደሩና ከኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በሚሠራው የትብብር ሥራም በአሁኑ ወቅት ትልቁ የኦቾሎኒ ቅቤ አምራች ድርጅት መሆን ችሏል። የኦቾሎኒ ቅቤው ማንም ሰው በቀላሉ ሊጠቀመው የሚችል በመሆኑ ገበያ ውስጥ በስፋት የሚፈለግና ለጤናም ተስማሚ እንደሆነ ይናገራሉ። ምርቱ ከቤት ውስጥ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በማረሚያ ቤቶችና በተለያዩ ቦታዎች የሚፈለግ ነው፡፡
‹‹የኦቾሎኒ ቅቤው ከጤና አንጻር ተቀባይነትን ያለው ነው›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ለዚህም በዋናነት ያለምንም ማጣፈጫ ቅመሞች ሙሉ ለሙሉ ለውዝ ብቻ በመጠቀም የሚመረት መሆኑ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና ተፈላጊ አድርጎታል ይላሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ጣፋጭ ነገሮችን መጠቀም ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን የሚያስከትል እንደመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ህጻናትን ጨምሮ አብዛኛው ሰው ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤን የሚጠቀም በመሆኑ ምርቱ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይመረታል።
በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ ፍቼ ከተማ ላይ የሚገኘው ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤ ማምረቻ በስድስት ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ፋብሪካው ከኦቾሎኒ ቅቤ ባለፈም ሰሊጥ ላይ የመሠማራት ዕቅድ አለው። ሰሊጥ ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ ያላቸው አቶ ተስፋዬ፤ ሰሊጥ በጥሬው ወደ ውጭ በመላኩ የሚቆጩ ናቸው። ስለዚህ ሰሊጥ ላይ በትንሹም ቢሆን እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ቢቻል በድርጅቱም ሆነ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ እንደሆነ የጸና እምነት አላቸው፡፡
እሳቸው እንዳሉት ሰሊጥን በቀላሉ አበጥሮ፣ ፈትጎና ቆልቶ ወደ ቅቤነት በመቀየር የሰሊጥ ቅቤ ማዘጋጀት ይቻላል። እናቶቻችን በቀላሉ በቤት ውስጥ አዘጋጅተው ፍትፍት ላይ፣ አነባብሮ ላይ፣ ሰላጣና በሌሎች ምግቦች ላይም የሚጠቀሙትን አሁንም በቀላሉ መጠቀም ይቻላል። ለዚህም ተስፋዬ የለውዝ ቅቤ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የሰሊጥ ቅቤን ወደ ገበያ ለማምጣት እየሠራ ይገኛል። በመሆኑም በቅርቡ በሀገር ውስጥ ገበያ ተደራሽ እንደሚሆንና ወደፊትም ወደ ውጭ ገበያ እንደሚላክ ሙሉ ዕምነት አላቸው።
‹‹ለውዝ በባህሪው ትንሽ ተመግበውት ረጅም ጊዜ የረሃብ ስሜት እንዳይሰማን ያደርጋል›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ለለውዝ ቅቤውም ሆነ ለሰሊጥ ቅቤ ዋና ግብዓት የሆነውን ለውዝና ሰሊጥ ከቤኒሻንጉልና ከቻግኒ እንደሚያስመጡ ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት አምራቾች ጥሬ ዕቃውን ብቻ ሳይሆን ማሸጊያዎችንም ጭምር ማምረት አለባቸው። በመሆኑም ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤ የተለያየ መጠን ያላቸውን ፕላስቲክ ማሸጊያዎች ጭምር በማምረት ያለቀለት የኦቾሎኒ ቅቤን በተለያየ መጠን አሽጎ ለገበያ ያቀርባል።
ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤ በአንድ ኪሎ፣ በ500 ግራምና በ350 ግራም ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን፤ የማምረት አቅሙም በቀን 10 ኩንታል ወይም አንድ ሺ ኪሎ ግራም ነው። ይሁንና አሁን ላይ ፋብሪካው ባጋጠመው የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የትራንስፖር እጥረት በሙሉ አቅሙ እያመረተ አይደለም። ነገር ግን አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ሲፈቱ በቀጣይ በሙሉ አቅሙ የማምረትና ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ባለፈ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተደራሽ የመሆን ራዕይና አቅም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከአስር ዓመት በላይ ገበያ ውስጥ የቆየው ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤ በጥራት የሚመረትና ሲጀምር ጀምሮ የነበረውን ጣዕም ይዞ በመቆየቱ ተመራጭ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሱቆች እንዲሁም ኩዊንስና ኦልማርት ሱፐርማርኬትን ጨምሮ በትላልቅ የገበያ ማእከላት ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ህጻናት በቀላሉ ዳቦ ላይ ቀብተው የሚመገቡት ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ማረሚያ ቤቶችና ትላልቅ ሆቴሎች ጭምር ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤን ተመራጭ አድርገዋል፡፡
በቀጣይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የምግብ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የመሥራት ዕቅድ ያላቸው አቶ ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ጸጋዎች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ ይህንኑ ጸጋ መጠቀምና ለውጥ ማምጣት ከአምራች ኢንዱስትሪው የሚጠበቅ እንደሆነ አብራርተዋል። እሳቸው እንዳሉት አሁን ላይ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል። ይህ ከዚህ ቀደም አልነበረም። በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራቹ መነቃቃት ተፈጥሮለታል። ሸማቹም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ማወቅና መረዳት የቻለ ሲሆን የገበያ ትስስርም ፈጥሯል።
‹‹እንደ አምራች ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ትልቅ አቅም አለ›› በማለት አንዳንድ ከውጭ የሚገቡ በተለይም የታሸጉ ምግቦችን ሲመለከቱ ውስጣቸው በእጅጉ የሚያዝን መሆኑን ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› በማለት የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ ለዚህም ጥሬ ዕቃው ከኢትዮጵያ ተልኮ ነጮቹ መጠነኛ የሆነ እሴት በመጨመር ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ተኪ ምርቶችን በሀገር የማምረትና ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችል ትልቅ አቅም ያላት በመሆኑ ይህንን አቅም ለመጠቀም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጉልህ አበርክቶ ነበረው ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ካገኛቸው ትሩፋቶች መካከል የገበያ ዕድል አንዱ ሲሆን፤ በጉብኝት ወቅት የተለያዩ የውጭ ዜጎች ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው አሁን ላይ ጥያቄ አቅርበዋል። ስለዚህ የገበያ ፍላጎት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ እየሰፋ መጥቷል። በመሆኑም የውጭ ገበያው በሚፈልገው የጥራት ደረጃና መጠን በማምረት በቀጣይ ምርቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ይሆናል። በዚህም ድርጅቱ ከሚያገኘው ጥቅም ባለፈ በአገራዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የድርሻውን የሚወጣና የቀጣይ እቅዳቸውም ይኸው መሆኑን ገልጸዋል።
ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት መንግሥት ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት እንዳለበት ሁሉ ማህበረሰቡም በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝና በሀገር ውስጥ መጠቀም እንዲችል ሚዲያው ኃላፊነት አለበት ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ከምንለብሰው ልብስ ጀምሮ የተለያዩ ምግቦችን በሀገር ውስጥ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤ በተለይም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ ሄደው ታሽገው ተመልሰው እንዲመጡ መፍቀድ የለብንም በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ህብረተሰቡ ጥራት ያላቸውና በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዕውቅና የተሰጣቸውን ምርቶች ብቻ መጠቀም እንዲችል ግንዛቤ መፍጠር ተገቢ እንደሆነ ያነሱት አቶ ተስፋዬ፤ ፈቃድ የሌላቸውና አድራሻቸው ጭምር በምርቱ ላይ ያልተገለጹ ምርቶች በገበያ ውስጥ እንዳሉና ደረጃውን ሊያሟላ የማይችል ምርት ገበያ ውስጥ እንዳይገባና ባለሱቁ እንዳይዘው ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋል። በማለት ገበያው በእነዚህ አይነትና አመሳስለው በሚሠሩ ምርቶች እየተረበሸ መሆኑን በመጥቀስ ይህም የዘርፉ ፈታኝ ችግር እንደሆነ አመላክተዋል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የተለያዩ ድጋፎችን ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚያደርገው ተስፋዬ የኦቾሎኒ ቅቤ፤ በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል። ለአብነትም የውሃ መውረጃ ድልድይ በመሥራት በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ባለው የምገባ ማዕከልም እንዲሁ የሰሊጥ ፍትፍት ያቀርባል። የሰሊጥ ፍትፍቱን እንደ አንድ የምግብ አይነት ለተማሪዎች እያቀረበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ ሰሊጥ በባህሪው ኃይል ሰጪና በካልሺየም የበለጸገ መሆኑን ገልጸው ህጻናቱ ከወተት የሚያገኙትን ካልሺየምና ኃይል ከሰሊጥ እንዲያገኙ በምገባ ሥርዓት ውስጥ በማስገባት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነና መንግሥታዊ ለሆኑ ሀገራዊ ጥሪዎችም እንዲሁ ድርጅቱ ባለው አቅም ተሳታፊ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም