ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ሰኔ ወር ገብቶ ሳይጠናቀቅ የተለያዩ ግዥዎችን ለመግዛት ፣ የተለያዩ ክፍያዎችን ለመክፈል፣ የዱቤ አገልግሎቶችን ለመሰብሰብ መሯሯጥ የነበረ አሁንም ያልተቀረፈ ተግባር መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይስተዋላል። ይህ የሚያመላክተው ከሥር ከሥሩ በየጊዜው ነገሮችን ከማከናወን ይልቅ በተለያዩ ምክንያቶች ማጓተት እንዳለ እና ሰኔ ተጠናቆ ኦዲተር ሲመጣ ለኦዲተር ሪፖርት ለማቅረብ እንዲረዳ(እንዲያመች) በሚል ብቻ በእውር ድንብር የሚከናወን ተግባር መሆኑን ነው።
ይህን የእውር ድንብር አካሄድ ተከትለው ቢንቀሳቀሱም ሁሉንም ማሳካት አቅቷቸው እንዳይደርስ ብለው የሚሯሯጡለት ሰኔ 30 እንደይማደርስ የለም ደርሶ ያልፍባቸዋል። ኦዲተር ደግሞ በበጀት ዓመቱ የተፈቀደ ገንዘብ በበጀት ዓመቱ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን እና በበጀት ዓመቱ ለተሰጠ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ መሰብሰቡን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል። እንዲሁም በጉድለት፣ በብክነት፣ ገንዘብ ባለመሰብሰብ፣ ሥራን በተገቢ ሁኔታ ባለመምራት፣ ወዘተ. በማለት በኦዲት አሠራር ሥርዓት መሠረት አጋልጦ ያቀርባል።
በአሠራር ሥርዓቱ መሠረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትም በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ላይ የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል። በዚህ ዓመትም ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት 32ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2015 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አቅርቧል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ፤ በ2014 ዓ.ም. 92 መሥሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝት መሠረት ተመላሽ እንዲያደርጉ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊዮን ብር እና 23 ሺህ ዶላር ውስጥ ኦዲት ሲሠራ ተመላሽ የተደረገው ብር 48 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል። 394 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተመላሽ አልተደረገም ማለት ነው። የዚህ አፈጻጸሙ ሲታይ 11 በመቶ ብቻ ነው። ይህ የሚያመላክተው መሥሪያ ቤቶቹ ተመላሽ እንዲያደርጉ አስተያየት ሲሰጣቸው አስገዳጅ ሁኔታ አለመኖሩን እንዲሁም ተመላሽ እንዲያደርጉ የሚከታተላቸው አካል በአግባቡ የመከታተል ክፍተት እንዳለበት ነው።
በኦዲት ሪፖርቱ በ2015 ዓ.ም በ124 መሥሪያ ቤቶች በጠቅላላው ብር 14 ነጥብ 1 ቢሊዮን በወቅቱ ያልተወራረደ ወይም ያልተሰበሰበ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩ ቀርቧል። ለውሎ አበል እና ለመጓጓዣ እንዲሁም ለግዥ የተሰጠ ክፍያ ሠራተኛው ሥራውን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ በ7 ቀናት መወራረድ እንዳለበት መመሪያው ቢያዝም ተቋማቱ ገንዘቡን በወቅቱ ባለማወራረዳቸው ከፍተኛ ውዝፍ ተሰብሳቢ ገንዘብ ይኖርባቸዋል። ይህ ያልተሰበሰበ ወይም ውዝፍ ሂሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል በከፍተኛ መጠን ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው ጤና ሚኒስቴር ነው፤ መጠኑም 6 ቢሊዮን ብር ነው። ሌሎች መሥሪያ ቤቶችም በቢሊዮን እና በመቶ ሚሊዮን ብር ደረጃ የተጠቀሰ ገንዘብ ማሰባሰብ አለመቻላቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ከአንድ መሥሪያ ቤት 6 ቢሊዮን ብር እንደቀላል ሳይሰበሰብ የቀረ ተብሎ ይገለጽ እንጂ ይህ ገንዘብ ቢሰበሰብ ለሀገር የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ ይሆናል (በአግባቡ ወጪ የሆነም ካለ በወጪ ተይዞም ቢሆን)። ይህ ሁኔታ በአፋጣኝ ለየት ያለ ንቅናቄ ተፈጥሮም ይሁን ወይም በሌላ መንገድ ተመላሽ ገንዘቡ ተሰብስቦ ገቢ መሆን ካልቻለ፤ እንዲሁም ለቀጣይ የሚሰበሰብ ገንዘብ በወቅቱ ተመላሽ እንዲደረግ የሚያስገድድና ከተለመደው አካሄድ በተለየ ጠንከር ያለ አሠራር፣ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲሁም የተጠያቂነት አግባብ መከተል ካልተቻለ ዛሬ በሚሊዮን ደረጃ ሳይሰበስቡ የቀሩ መሥሪያ ቤቶች ነገ ወደ ቢሊዮን ብር ማደጋቸው አይቀሬ ይሆናል።
ሌላኛው የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ የጠቀሰው ጉዳይ በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ሲሆን፣ የሥራ ተቋራጮች ከዚህ በፊት የነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ሳይታይ በሌሎች የግንባታ ጨረታዎች ላይ እንዲወዳደሩ ተደርጎ ማሸነፋቸው ተገልጾላቸው ግንባታ ጀምረዋል። በዚህም 11 ቢሊዮን ብር ገደማ ዋጋ ያላቸው 12 የግንባታ ፕሮጀክቶች ለሁለት የሥራ ተቋራጮች ተሠጥቷል።
ለዚህ ተጠያቂ የሚሆነው የሥራ አፈጻጸማቸው ሳይታይ እንዲገነቡ የፈቀደላቸው መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን መሥሪያ ቤቱን የሚቆጣጠረውም አካል መሆን አለበት። ምናልባት ‹‹እኔ በዚህ ልክ እንደነበረ አላውቅም›› የሚል ከሆነ ከእኛ እኩል መስማት አይገባህም፤ መቆጣጠር ነበረብህ ብለን ድርቅ ሳንል እስቲ በቀጣይ የተወሰደውን የማስተካከያ ርምጃ አሳየን እንላለን። ርምጃ ተወስዶ ማሳየት ካልተቻለ ግን ተቆጣጣሪውም …።
ይህ ብቻ ሳይሆን የግንባታ ፕሮጀክቶች መቋረጥ መንግሥትን ለሀብት ብክነት እየዳረገው ይገኛል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት እንደሚያሳየው ለናሙና ከታዩ 41 የተቋረጡ ፕሮጀክቶች መንግሥትን 17 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጣ እድርጎታል። 17 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ከማስወጣቱ በላይም ግንባታዎችን የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ግንባታዎች ከተቋረጡ በኋላ የተከፈሉ የቅድመ ክፍያዎችን አላስመለሰም እንዲሁም የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና ገንዘብን ተከታትሎ አላስፈጸመም። ይህን የተከፈለ ቅድመ ክፍያ ባለሥልጣኑ ተከታትሎ ማስመለስ ካልቻለ ታዲያ ማን ተከታትሎ ያስመልስ? ባለሥልጣኑን የሚከታተሉ የሚመለከታቸው አካላት ዋና ኦዲተሩ የሚያቀርባቸውን ሪፖርቶች በትኩረት በማየት አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድ በከፍተኛ ሁኔታ መትጋት አለባቸው።
ሌላው የሚገርመው ጉዳይ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከገንዘብ ሚኒስቴር እውቅና ውጪ ከፓስፖርት አገልግሎት ጠያቂዎች 17 ሚሊዮን ብር በሕገወጥ መንገድ በግለሰብ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ሰብስቧል ተብሎ በሪፖርቱ የቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 9 ሚሊዮን ብሩን ለሠራተኞች የበዓል ስጦታ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዳዋለው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት የፓስፖርት አገልግሎትን በውክልና እንደሚሰጥ የተገለፀ ነገር ሳይኖር ቪዲቸር (viditture) ለተባለ የግል ድርጅት የውል ስምምነት በማድረግ ውክልና የሰጠ መሆኑን የዋና ኦዲተር ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
የግል ድርጅቱ ከሀገር ውጭ ያሉ ነዋሪዎች ለፓስፖርት አገልግሎት ኦንላይን ሲያመለክቱ ሰነዱን አጣርቶ፣ ከኢምግሬሽን ፓስፖርቱ ተዘጋጅቶ ሲያልቅ ተቀብሎ ወደ ደንበኛ ለማስተላለፍ ተገልጋዩ ለኢምግሬሽን ከከፈለው በተጨማሪ 100 ዶላር እንደሚያስከፍል ኦዲቱ አጋልጧል። ቪዲቸር የተባለው አስከፋዩ ድርጅት ይህንን ሥራ ለመሥራት የተመረጠበት መስፈርት፣ የግዢ ሂደት እና ፓስፖርትን ለማሠራጨት ፈቃድ ያለው መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃም አላቀረበም። ይሄ ብቻ ሳይሆን የፓስፖርት ሥራ ለመሥራት በሀገሪቱ የንግድ ሕግ መሠረት ንግድ ፈቃድ አላወጣም፤ በታክስ ሕጉ መሠረት ግብር የማይከፍል ነው። ይህ የሚያመላክተው ሥርዓትና ሕግ እየተከበረ አለመሠራቱን ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ኃላፊ መልካም ፍቃድ መሥሪያ ቤቶች እየተመሩ መሆኑን
ነው። ለዚህም ገደብ ሊበጅለት ይገባል።
በኦዲት ሪፖርቱ በ 14 መሥሪያ ቤቶች 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በተከፋይ ተመዝግቦ የተያዘ መሆኑን፣ ነገር ግን ለማን እንደሚከፈል ተለይቶ የማይታወቅ እንደሆነ፤ 30 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች 16 ሚሊዮን 470 ሺህ ብር ከደንብና መመሪያ ውጪ አላግባብ መክፈላቸው፤ መሥሪያ ቤቶች በፋይናንስ አስተዳደር አዋጁ መሠረት የተመደበውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ማዋል የሚጠበቅባቸው ቢሆንም የገንዘብ ሚኒስቴር ስምንት ቢሊዮን ብር፣ የጤና ሚኒስቴር ሁለት ቢሊዮን ብር፣ ግብርና ሚኒስቴር 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር፣ ወዘተ. ከአዋጁ ውጭ ከታለመለት ዓላማ በተለየ ማዋላቸው ቀርቧል። እንደነዚህ አይነት ተግባራት ሲከናወኑ ተከታትሎ የእርምት (የማስተካከያ) እርምጃ የሚወስድ አካል ያስፈልጋቸዋል።
እኛ እንግዲህ አስፈጻሚውን አካል ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ ጉድለት ሲገኝ ማስተካከያ ወይም የእርምት ርምጃ ይወስዳል፤ እንዲሁም እንዲወሰድ ያስደርጋል ብለን በዋነኛነት የምንለው ፓርላማውን ነውና ፓርላማው ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስ ይገባል። ይህንን የማድረግ የሞራልም የህግም ሃላፊነት አለበት ።
የእርምት ርምጃዎችን በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስቴር በ2014 በጀት ዓመት በቀረበለት ሪፖርት መሠረት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ከተሰጠባቸው 19 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የኦዲት አስተያየት ሊሰጠባቸው ባልቻሉ ስድስት ተቋማት ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዱ ተገልጿል።
ከነዚህ መካከል በስድስት ዩኒቨርሲቲዎች እና በሰባት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የገንዘብ ቅጣት እና ከባድ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን ዋና ኦዲተሯ አመላክተዋል። በተጨማሪም ሶስት የዩኒቨርሲቲ አመራሮችም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉንም አንስተዋል። ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም የእርምት ርምጃው በጣም ጥቂት ከመሆኑ በተጨማሪ ብዙ እርቀት መሄድ የሚገባው ነው። ከኃላፊነት ማንሳት ብቻ ሳይሆን በህግ አግባብ ተጠያቂ አድርጎ ውሳኔ ማሰጠትም ይገባል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙና ኮሚሽን፣ የሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በሚያቀርቡበት ወቅት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በስተቀር ሁሉም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በስብሰባው መገኘት እንዳለባቸው ተደንግጓል።
ይህ ይሁን እንጂ ኦዲት ሪፖርቱ ሲቀርብ መገኘት ከነበረባቸው 22 ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ጥቂቶች ብቻ እንደተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ በመንግሥት ኃላፊዎች ደረጃ የኦዲት ግኝቱ ከፍተኛ ትኩረት እንዳልተሠጠው አመላካች ሊሆን ይችላል እላለሁ። ይህን ሃሳቤን የሚያጠናክርልኝም ዋና ኦዲተሯ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከኦዲት ግኝቱ ይልቅ ግኝቱ በሚዲያ መቅረቡ ስለሚያሳስባቸው ሚዲያዎች የኦዲት ግኝቱን በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ አድርጉ ብለው ማሳሰባቸው ነው።
ከላይ እንደገለጽኩት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርትን አድምጦ ተገቢና ተከታታይ ርምጃ የመውሰድ ንቅናቄ ያስፈልጋል። ልክ እንደ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አይነት የሆነ ስያሜ ተሰጥቶ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል። ለቀጣይ ዓመት የተበጀተው በጀትም ትሪሊዮን ደርሷል፤ ይህን ትሪሊዮን በአግባቡ ወጪ ለማድረግ ከቀድመው በተለየ አካሄድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ብልጽግናን ማምጣት አይቻልም።
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016