የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በክልሎች

ጽዱ አካባቢ የሥልጡን ማኅበረሰብ መገለጫ ነው። ንጹሕ መንደርና የጸዳ አካባቢ ያማረ ከተማን ይፈጥራል። የሀገር እድገትም በከተሞች ውበት ይለካል።

በመዲናችን አዲስ አበባና በሌሎችም የሀገራችን ከተሞች በተለያዩ ጊዜያት የፅዳት ዘመቻዎች፣ አካባቢን በአረንጓዴ የማልማት የንቅናቄ ሥራዎች ይከናወናሉ። ዘመቻዎቹ ግን የአንድ ሰሞን ብቻ ይሆኑና ዘላቂ ለውጥ ሳያመጡ ይቀራሉ። ከማኅበረሰቡ ዘንድ ፅዳትን ባሕሉ አድርጎ ማስቀጠል፤ ቤቱ ሲቆሽሽ የሚጸየፈውን ያህል አካባቢው ሲቆሽሽ የሚቆረቆርበትን ባሕል ለማዳበር ወደኋላ ሲጎተት ይታያል።

በከተሞች የሚታየውን ሥር የሰደደ የፅዳት ችግር ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የ“ፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ንቅናቄ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ለንቅናቄው ዓላማ ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ተከፍቶ በነበረው የቴሌቶን ገንዘብ ማሰባሰቢያም በርካቶች በቻሉት ልክ የዜግነታቸውን አበርክተዋል።

በመዲናዋ አዲስ አበባ ንቅናቄውን መነሻ ያደረጉ ተጨባጭ ጅምር ሥራዎች ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዘው ተግባር ላይ እየዋሉ እንዳሉ እያየን ነው። ከዋና ከተማዋ ውጪ ባሉ የክልል ከተሞችስ ንቅናቄው በምን ያህል ልክ ዘልቋል? ምንስ እያከናወኑ ይገኛሉ?

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሠናይት ሰሎሞን፣ በክልሉ 32 ከተሞች መኖራቸውን አንስተው፣ በሁሉም ከተሞች ከአረንጓዴ ልማት እና ከከተማ ውበት ጋር ተያይዞ ዕቅዶች ወጥተው በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከንቅናቄው ጋር በተያያዘ በሁሉም ክልሎች ሕዝባዊ ውይይት መካሄዱን የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ ከኅብረተሰቡ ጋር ጥሩ የሚባል መግባባት ላይ በመደረሱ ነዋሪዎች ከራሳቸው ግቢ አንስተው አካባቢያቸውን የማፅዳትና የማስዋብ ሥራ እንዲያከናውኑ መደረጉን ገልጸዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች አማካኝነትም ከተሞችን የማስዋብና የማጽዳት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። የክልሉ አመራሮችና የኅብረተሰብ ክፍሎችም በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት ከተሞችን ፅዱ በማድረግ ንቅናቄው ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው። በተግባርም አመራሩ በፅዳትና ችግኝ ተከላ ላይ በመሳተፍ ወጣቱን በማነቃቃት ረገድ ግንባር ቀደም ሆኖ እየተሳተፈም ይገኛል። ከዚህ ቀደምም በተሠሩ ከተሞችን የማስዋብ ሥራዎች እንደ አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላና ሌሎችም ከተሞች ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱንም አንስተው በቀጣይም ሰፋፊ ሥራዎች እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

የፅዳት ጉዳይ በቀጥታ ከጤና ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ፣ የጤና ተቋማት ፅዱና ለተገልጋዮቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻል ዘንድ ራሱን የቻለ የንቅናቄ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ በሁሉም በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት ላይ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ኃላፊዋ ገልፀዋል። የሕዝቡን ተሳትፎ በማሳደግ ንቅናቄውን በቀጣይነት ለማስኬድ የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተሠሩ ናቸው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የከተማ ልማትና ኮንትስራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የማታዓለም ቸኮልም፣ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በፌደራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፣ ክልሉም ይህንን መነሻ በማድረግ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ ሌሎች የክልልና የከተሞች አመራሮችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተገኙበት የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን ተናግረዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት፣ ከንቅናቄ መድረኩ በኋላ በክልሉ ከሚገኙ 16 የከተማ አስተዳደሮች መካከል 14ቱ ወደ ተግባር ገብተዋል፤ በከተሞቹ የተለያዩ አካባቢዎችም የፅዳት ዘመቻዎች ተካሂደዋል።

በክልሉ በየጊዜው እየተቆራረጠ መቀጠል ያልቻለውን የከተማ ፅዳት ሥራ በቀጣይነት በማኅበረሰብ ዘንድ ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው፤ ከከተማ ፅዳት ጋር ተያይዞ በአዋጅ የተቀመጡ አስገዳጅ ሕጎችን የማስተግበር ተግባራትም እየተተገበሩ ናቸው ብለዋል። በዚህም ቀደም ሲል በአዋጅ የተቀመጡ “አንድ ነዋሪ ከቤቱ ደጃፍ ተነስቶ 20 ሜትር ዙሪያ ድረስ አካባቢውን እንዲያፀዳ፣ ተቋማት ደግሞ 50 ሜትር ዙሪያቸውን እንዲያፀዱ” በሚል የተቀመጠውን መመሪያ እንዲተገበር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው።

ከማኅበረሰቡ በተጨማሪ በመደበኛነት ፅዳት ላይ ለሚሠሩ አካላትም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ትኩረት ዋና ዋና አደባባዮችን እንዲያፀዱም አቅጣጫ ወርዶ፤ እየተተገበረ እንደሚገኝም አቶ የማታዓለም ገልፀዋል።

ከተሞቻችንን ፅዱ ማድረግ የዜግነት ግዴታችን ነው ያሉት በአፋር ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መሐመድ አሊ፣ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጀምሮ ሌሎችም አመራሮች፣ ሠራተኞችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጀመረውን ንቅናቄ ወደራሱ በመውሰድ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል። ለሀገሩ በሚደረግ መልካም ነገር ሁሉ የአፋር ሕዝብ ቆራጥ ነው ያሉት አቶ መሐመድ፣ በዚህ ንቅናቄም ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን ተናግረዋል።

አቶ መሐመድ እንዳሉት፣ የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችው ሰመራ በ2018 ዓ.ም የከተሞችን ፎረም ለማዘጋጀት ዝግጅቶች እያደረገች ሲሆን፣ ከንቅናቄው በፊት የተጀመሩ ከንቅናቄው በኋላም እየተጠናከሩ የመጡ የፅዳት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

በንቅናቄው ፅዳት ከራስ ቤትና ጊቢ ያለፈ ነው በሚለው ላይ ኅብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳሉ ያነሱት ኃላፊው፣ በዚህም በየአካባቢው ለጤና ጠንቅ የሆኑ የተከማቹ ቆሻሻዎችን የማስወገድ ሥራ ተሠርቷል። ከዚህ ባለፈም ቀደም ባሉ ዓመታት የተጀመረው ችግኝ ተከላም እየተጠናከረ መጥቷል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ ባሕል፣ እሴትና ክብር ያለው ሕዝብ ነው ያሉት አቶ መሐመድ፣ የአካባቢ ብሎም የከተማ ፅዳት የአንድ ሕዝብ መገለጫ፤ ለማኅበረሰብ ጤናም ወሳኝ እንደመሆኑ ኅብረተሰቡ ቆሻሻን በመፀየፍ አካባቢውን ከቆሻሻ የፀዳ በማድረግ ራሱንና ሀገሩንም ሊያስከብር ይገባል ብለዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You