
ኩራ ጅዳ:– የሸገር ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኝ ታላቁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በይፋ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልሰ አብዲሳ 12ቱን የሸገር ክፍለ ከተሞች የሚያገናኝ ታላቁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በትናንትናው ዕለት በይፋ አስጀመሩ።
አቶ ሽመልስ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሸገር ከተማ የተመሠረተው ከፕላን ጀምሮ ሁሉንም ዝግጅት በማጠናቀቅ ነው። በዚህም የሸገር ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኝ መንገድ በይፋ መጀመሩን ገልጸው፤ የመንገድ አጠቃላይ ርዝመት 150 ኪሎ ሜትር መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመጀመሪያ ምዕራፍ የኩራ ጅዳ፣ ጣፎ፣ ኮዬ ፈጬና ገላን ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኝ 38 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የግንባታ ወጪ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሆኑንም ተናግረዋል። የመንገዱ ስፋት 250 ሜትር መሆኑን አስታውቀዋል።
ሸገር ከተማ በከፍተኛ መስዋዕትነት የተመሠረተች ከተማ መሆኗን በመገንዘብ ሁሉም አመራሮች ከወትሮው አሠራር በመላቀቅ የተዘጋጀውን ማስተማር ፕላን በከፍተኛ ጥንቃቄ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የኦሮሞ ሕዝብ ሲደርስበት የነበረውን ከቀዬ የመፈናቀል አደጋ ለመቃወም ውድ መስዋዕትነት መክፈሉን ያወሱት አቶ ሽመልስ፤ በተለይ ለሸገር የተከፈለው መስዋዕትነት የተፈናቀለው መመለስ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ተፈናቃይ እንዳይኖር በልዩ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የከተማዋን እድገት ለማፋጠን እየተሰበሰበ ያለው ገቢ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
ለሕዝቡ የከተሜነትን ኑሮ ምቹ ለማድረግ መንገድን ጨምሮ ብዙ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ይገኛሉ። ሕዝቡ የተሻለ ኑሮ ለመምራት በርካታ ሙያዎችን ማካበት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው፣ መንገዱ በአምስት ምዕራፍ የሚገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመጀመሪያው ምዕራፉ በይፋ ግንባታው የተጀመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሁለተኛው ምዕራፍ ኩራ-ሱሉልታ፣ ሦስተኛው ምዕራፍ ሱሉልታ-ገፈርሳ ጉጄ፣ አራተኛው ምዕራፍ ገፈርሳ ጉጄ-ዲማ፣ አምስተኛው ምዕራፍ ዲማ-ገላን መሆኑ ከንቲባው አብራርተዋል።
ዘጠኝ የልማት ኮሪደሮች የተለዩ መሆኑን ተናግረው፤ የከተማዋ ስፓሻል ፕላን ሥራ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡
የክፍለ ከተሞች ፕላንም መሠረቱን ገልጸው፤ የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሸገር አስፓልት መንገድ ቁጥር ከ63 ወደ 413 እንዲሁም የመንገድ ኔትዎርክን ከ50 በመቶ በላይ ከፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
መንገዱ በአዲስ አበባ የሚስተዋለው የትራፊክ ፍሰት ችግር እንደሚያቃልልና የከተማዋን ምርት በቀላሉ ለአዲስ አበባ ገበያ ማቅረብ እንደሚስችልም ዶክተር ተሾመ ገልጸዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም