አረንጓዴ ዐሻራ በሁሉም መስክ ራሳችንን ለመቻል ለጀመርነው ንቅናቄ ስትራቴጂክ አቅም ነው!

አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ሀገር እውቅና ካገኘችባቸው አጀንዳዎች አንዱ ነው። ይህ ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ንቅናቁ በሕዝባችን ከፍ ያለ ተቀባይነት በማግኘቱም በየአመቱ እተመዘገበ ያለው ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተፈጠረ ሀገራዊ መነቃቃት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የተራቆቱ መሬቶችን በደን ከመሸፈን ባለፈ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ ሊያጋጥማት የሚችለውን ፈተና ለመሻገር የሚያስችል ትልቅ አቅም እንደሆነ ይታመናል።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት ፤ ከችግኝ ተከላ ጋር የተያያዘው የሀገሪቱ ታሪክ ሺ ዓመታትን ወደኋላ የሚመልስ ነው። ይህ ባህል መቀጠል ባለመቻሉም የሀገሪቱ የደን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ እና ፍጥነት እየተመናመነ መጥቷል ለተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችም ሀገሪቱን ተጋላጭ አድርጓታል።

በዘመናት ሂደት ውስጥ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የከተሞች መስፋፋት ፣ የሚታረስ መሬት መጨመር … ወዘተ የደኖች ምንጣሮ መብዛቱና እነሱን የመተካቱ ጥረት ዝቅተኛ መሆን ሀገሪቱን ከፍተኛ ለሆነ የደን መራቆት ዳርጓታል።

ችግሩ እስካሁን ባለው ሁኔታ ሀገሪቱን ዓመታት እየቆጠረ ለሚከሰት የድርቅ አደጋ ተጋላጭ አድርጓታል። ችግሩን ለመሻገር በሚደረግ ጥረትም እንደ ሀገር የሌሎችን እጅ ጠባቂ እንድትሆን አስገድዷታል። ይህም አጠቃላይ በሆነው የሀገር ክብር ላይ እያስከተለ ያለው ተጽእኖ አንገት የሚያስደፋ ሆኖ ቆይቷል።

በጊዜው መላ ካልተበጀለት ችግሩ ዓለምን እየተፈታተነ ካለው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተዳምሮ ሀገሪቱን የከፋ የተፈጥሮ አደጋ ስጋት ውስጥ ሊከታት እንደሚችል ይታመናል። ለዚህ አሁን ላይ የሚስተዋሉ የአየር መዛባቶች ፣ የድርቅ ፣ የጎርፍ ፣ ወዘተ አደጋዎች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

እነዚህን ተጨባጭ ስጋቶች በመሻገር ሂደት ውስጥ አረንጓዴ ዐሻራ መተኪያ የሌለው አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል። እስካሁን ባለው አፈጻጸምም ችግን ከመትከል ባለፈ ፤ የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው የአካባቢ አየር ለውጥን በመከላከል ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ከ32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። በቀጣይ ሦስት ዓመታት ደግሞ 17 ነጥብ አምስት ቢሊዮን በመትከል 50 ቢሊዮን ችግኞችን በስምንት ዓመታት ውስጥ ለመትከልና ለማጽደቅ እቅድ ተይዟል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮ ዓመት አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል። የችግኝ ቁጥር በሄክታር ሲሰላ ዘንድሮ ተከላ የሚደረግበት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚሆን ይገመታል።

ያለፉት አምስት ዓመታት ሕዝባችን ከሁሉም በላይ የችግኝ ተከላ ለራሱም ሆነ ለመጪዎች ትውልዶች እጣ ፈንታ የቱን ያህል ወሳኝ አቅም እንደሆነ በአግባቡ ተረድቶ በኃላፊነት መንፈስ በስፋት የተንቀሳቀሰባቸው ናቸው ፣ እያስመዘገበ ያለው ውጤትም ከፍያለ ዓለም አቀፍ እውቅና ያጎናጸፈው ነው።

የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግን ተከላን የአረንጓዴ ዐሻራ አካል አድርጎ እየተሠራበት ያለው መንገድም፤ ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ፣ እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ለምናደርገው ሀገራዊ ንቅናቄ ስትራቴጅክ አቅም መሆን የቻለ ነው። እንደ ሀገር ያለብንን የተመጣጠነ የምግብ እህል አቅርቦት ችግር ለመፍታትም ሌላኛው አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ብዛት ያለው የሰው ኃይል ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ባለው የሥራ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ፤ ዘርፉ የሠው ኃይል ወደ ሥራ የሚገባባትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር አስችሏል። ከጠባቂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ረድቷል ።

በዚህ ክረምት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለስድስተኛ ጊዜ የምናካሂደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርም ይህንን በዘርፉ እያስመዘገብን ያለውን ስኬት በማስቀጠል ወደላቀ ደረጃ ማሻገር የሚያስችል ፤ ሀገራዊ ተጠቃሚነታችንን በማጎልበት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያገኘነውን ዕውቅናና ተደማጭነት ማስቀጠል የሚያስችል ነው ።

የአረንጓዴ ዐሻራው አሁን ላይ እንደ ሀገር ራሳችንን በምግብ እህል ለመቻል የጀመርነውን ሀገራዊ ንቅናቄም ሆነ ፤ ድህነትን ታሪክ አድርገን ለመሻገር ለጀመርነው ትግል ስኬት ዋነኛ ስትራቴጂክ አቅም ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል። ለስኬታማነቱም የሁሉንም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል።

አዲስ ዘመን  ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You