በሞት የተቋጨው ጓደኝነት

ጓደኝነት ሕሊና ቢወረስ በክፉ ትዝታ፤

ልቦና እየሻረው በጣፋጭ ትውስታ፤

በአብሮነት ጎዳና ገስግሶ የሚያነግሠው፤

መሆኑ ብቻ ነው ጓደኛ ጓደ’ኛ ሰው፤

ጊዜ እያፈለቀ የመቻቻል ወኔ፤

ለመልካም ተግባርህ ለደካማው ጎኔ፤

በጥሩ ቀን ሞገድ፤ አግባብቶን አላምዶ፤

ላያለያየን ነው፤ ያገናኘን ፈቅዶ፤

አንዴ ጥፋተኝነት አንዴም ደግሞ ደግነት

ኩርፊያም ፍቅር ያለበት ደስ ይላል ጓደኝነት።

ይህ የስንኝ ቋጠሮ ‹ጓደኛነት› በሚል ርዕስ ድምፃውያን በጋራ ካቀነቀኑት ሙዚቃ ላይ የወሰድነው የጓደኝነትን ትስስር በቀላል ትዕግስት ማጣት ስለበጠሱት ጓደኛሞች ታሪክ ልናወጋችሁ ስለወደድን ነው። ይህን ታሪክ ያገኘነው ከአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ቤት ነው። የተዘጉ ዶሴዎችን አገላብጠን ለአንባቢ እናደርስ ዘንድ የፈቀዱልንን የመዝገብ ቤት ባለሙያዎች ከልብ እናመሰግናለን። ከዚሁ ክፍል ያገኘነውን መረጃ እነሆ በተናጋሪው ዶሴ ይዘንላችሁ ቀርበናል። መልካም ቆይታ።

ጓደኝነት

እድሜያቸው በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ ቢሆንም፤ በሩቁ ለሚያያቸውና ቀርቦ ለማያውቃቸው ሰው፤ ተክለ ሰውነታቸውና ለሁሉም የሚያሳዩት የተግባቢነት ባሕሪያቸው ትልልቅ ሰዎች እንጂ ወጣትነት እድሜ ላይ ያሉ አይመስሉም። ቁምነገረኞች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ጓደኝነታቸው ከሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀ ነበር።

ታምር ሲሳይ እና በሱፍቃድ ቶሎና ይባላሉ። ትውውቃቸው የጀመረው ገና በአፍላነት እድሜያቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በነበሩበት ወቅት ነው። በአንድ የጋራ ጓደኛቸው አማካኝነት እንደተዋወቁና ቀስ በቀስ እየተላመዱና ልብ ለልብ እየተግባቡ ሲመጡ፤ አስደሳች የሆነ የጓደኝነት ሕይወትን በወጣትነታቸው እንዳሳለፉ የሚናገሩት እነኚህ ጓደኛሞች፣ ከቆይታ በኋላ ግን አንዱ እልኸኛ እየሆነ አንዱ ደግሞ በየእለቱ እየታገሰ ማለፍ ሰልችቶት እስከ መቆራረጥ የደረሱ ጓደኛሞች ነበሩ።

ብዙ ጊዜ ታምር ጓደኝነት ስሜት ነው ሲል ይደመጣል፤ በሕይወት የተለያዩ አጋጣሚዎች ተዋውቀው በሂደት ስለተላመድነው ሰው የማሰብ፣ የመጨነቅና እንደራስ አድርጎ በማየት የመውደድ ስሜት። ብዙኃኑ የእምነት አስተምሮዎች ሆነ ማኅበራዊ ተቋማት ስለ ጓደኝነት አስፈላጊነትና የሕይወት በረከቶች አጥብቀው የሚያስተምሩ ሲሆን፤ ከስጦታዎች ሁሉ ውዱ ስጦታ እውነተኛ ጓደኛን ማግኘት እንደሆነም በመናገር የጓደኛው ልብ በሐሴት እንዲሞላ ያደርጋል።

‹‹ጓደኛ በሁለት አካላት የምትኖር አንዲት ነፍስ ናት።›› ይላል ግሪካዊው ባለ ቅኔና ፈላስፋ አርስቶትል የጓደኝነትን ጥልቀትና ምስጢርነት ሲገልፅ። ጓደኝነት ጥቅሙ የማይለካ ነው፣ አንድ ሰው ጓደኛ ሲኖረው የሚመካበት እና የሚወደው ሰው እንዳለው ማሰቡ በራሱ ትልቅ የራስ መተማመንን ይሰጠዋል። ብዙ ማንነትና ብዙ መዋደድ ትልቅ የሕይወት ጣዕም እንዳለውና አመለካከትን እንደሚያዳብርም በመግለፅ፣ ድካምና ጥንካሬን ሁሉ በትክክል ማወቅ የሚቻለው ከጓደኛ ነው ።

ታዲያ ይህን የጓደኝነት መስመር አንዱ ብልጣ ብልጥ በመሆን፤ አንደኛው ደግሞ ለጓደኝነት የሚከፈል መስዋዕትን ያለ ስስት የሚከፍል ሰው ነበር። ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ለጓደኛው የሚከፍል ሰው ነበር።

ወጣት ታምር ሲሳይ

ታምር በጓደኝነት ሊገኝ የሚችለው ነገር በሙሉ ከጓደኛው ማግኘት የሚፈልግ ሰው ነበር። ከገንዘብ ድጋፍ አንስቶ እስከ ሀሳብ ድጋፍ ምንም ሳይጎል ማግኘት የሚፈለግ ሰው ነበር። ነገር ግን ይህ የገንዘብ ድጋፍ የጓደኝነት ግብ አለመሆኑንና እንደ ማንኛውም ድጋፍ እንደሚያደርግ የቤተሰብ አባል ሁሉ፤ ጓደኛም ችግር በገጠመን ሰዓት የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል መረዳት እስኪያቅተው ድረስ ጓደኛው ላይ ተጣብቋል። ‹‹ይሄ በራሱ ነውር አይደለም›› ባይሆንም የዚህም ምክንያት በጓደኝነት መሐል በሌላ ጊዜ ይሄ ድጋፍ ከእሱም የሚጠበቅበት መሆኑን ረስቶታል።

ብቻ ባገኘው አጋጣሚ በሙሉ የጓደኛውን ድጋፍ መጠየቅ ሥራው ነበር። ዘወትር በጓደኛው ተደግፎ በራሱ ሳይቆም ሕልሜ ወደሚለው ሊጓዝ ይፍጨረጨራል። ይህም መልካሙን ጓደኛውን ሊያሳጣው እንደሚችል ልብ ሳይል ቀረ። ተቀባይ እንጂ ሰጪ መሆን የተሳነው ታምር እለት በእለት በሚያደርጋቸው ነገሮች በእሱ ፍቃድን ያስቀይመው ጀመር።

መልካም ጓደኛ

መልካም ሰው ነው። ለሰው ሟች የሚባል አይነት በምግባር የተሞላ መልካም ሰው። በሱፍቃድ ቶሎና ይባላል። ያለውን ነገር በሙሉ ለመስጠት የማይሰስት መልካም ሰው ነበር። በቅንነት ለጓደኝነት የሚከፈለውን መስዋዕትነት በሙሉ የሚከፍል ከማንም ምንም የማይጠብቅ ሰው ነበር። በደግነት ያለስስት ጉልበቱን፤ ገንዘቡን፤ ላቡን በሙሉ ሳይሰስት የሚለግሰው ሰው በጎደለው ቀን ግን የዋለለት ሰው ካልደረሰለት በጣም የሚከፋ ሰው ነበር።

ከጓደኛው ታምር ጋርም ያጋጫቸው ይህ ጉዳይ ነበር። ታምር ምንም ነገር ሲፈልግ ከጓደኛው በሱ ፈቃድ ቀድሞ የሚያስታውሰው ሰው አልነበረውም። እሱ በተፈለገ ሰዓት ከች እያለ የጓደኛውን ሸከም ሲያቀል ሰንብቶ እሱ ችግር ሲገጥመው ታምር ፊቱን አዞረበት።

በእለቱ እናቱ ታመው ለሕክምና የጎደለውን ገንዘብ ማግኘት ሲፈልግ ሊያገኝ ባለመቻሉ የተከፋው ይህ ሰው ለክፉ ቀን የደረስኩለት ሲከፋኝ ከጎኔ ካልቆመ ጓደኝነቱን አልፈለግም ብሎ ይተወዋል። ምንም አይነት አስታራቂ መካከላቸው ቢገባ በሱ ፈቃድ እርቁን ሊቀበል ፍቃደኛ ሳይሆነ ይቀራል። እርቁን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን የነፍስ ጓደኛው ታምርን ስም በአካባቢው የሚጠራ ሰው ቀንደኛ ጠላት ሆኖ ይቆጠር ጀመር።

የሁለቱን ጓደኝነት የሚያውቁ ሰዎች መጣላታቸው ሲገርማቸው ለመጠየቅ ሙከራ ያደርጋሉ። በየአጋጣሚው የሰሙትን ነገር በተዛባ ሁኔታ ለሁለቱም እያደረሱ ፀባቸው እንዲከር ያደርጉታል። በዚህም የተነሳ ታምር ተናዶ ቂም ይዞ የልብ ጓደኛውን ሊደበድብ ይፈልገው ጀመረ። ያን የመሰለ በርካቶችን የሚያስቀናው ጓደኝነታቸውን ለጥቅም ብቻ የፈለገው ታምር ጥቅሙ ሲቀርበት ተናዶ እየተመላለሰ በሱ ፈቃድን ነገር ይፈለገው ጀመር። ምንም እንኳን ታምር በሱፍቃድን አንዴ ለእርቅ ሌላ ጊዜ ለጸብ ቢፈልገውም ቅሉ በሱ ፈቃድ ግን አንጀቱ ቆርጦ ነበር እና ሁሉንም በዝምታ ያልፈው ጀመር።

ወንድነት የተለካበት ሰዓት

በእለቱ ታምር ሲሳይ የተባለው ወጣት ሆን ብሎ ጓደኛውን ለማጥቃት በማሰብ ከቤቱ ወጣ። በነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 5፡15 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ንግሥት አስፋው ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሟች በሱፍቃድ ቶሎናን እየተተናኮለ፣ ነገር እየፈለገው ቆይቶ ዝም ሲለው ትዕግስቱን ሊያስጨርስ የተለያዩ ሙከራዎች ያደርግ ጀመር።

ከዛ እስኪ አንተ ወንድ ነህ በለኝ በማለት በተደጋጋሚ የቀድሞ ጓደኛውን ሲያስጨንቅ ቆይቶ በሱፈቃድ እስኪ አንተ ወንድ ነህ በማለት ሲመልስለት ታምር ይዞት የነበረውን ቢላ ከሱሪው ውስጥ በማውጣት ሟች በተቀመጠበት በቀኝ በኩል ትከሻው ላይ በመውጋት ጉዳት አደረሰበት። በሱፈቃድም በደረሰበት ጉዳት በሕክምና እየተረዳ እያለ በእለቱ ሕይወቱ አለፈ።

የጓደኝነት መተሳሰሪያ ገመዱ እስከወዲያኛው ተበጠሰ። አይደለም በጓደኝነት በሕይወት ዳግም ላይገናኙ ተቆራረጡ። አንዱ ማደሪያው መቃብር ሲሆን የሌላኛው ዘብጥያ ሆነ።

በፀቡ ሰዓት በአከባቢው የነበሩ ሰዎች ጉዳት አድራሹን በመያዝ ለፖሊስ ያስረከቡ መሆኑንና ተጎጂውንም በአፋጣኝ ሆስፒታል ቢያደርሱትም ሊያተርፉት ባለመቻላቸው ፖሊስ ክስ ለመመስረት መረጃ ማሰባሰብ ጀመረ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ መረጃው እንደደረሰው ግዜ ሳያጠፋ በቦታው ተንቀሳቅሶ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አዋለው። ወንጀሉን ለመፈፀም እንዳላሰበ እየማለና እየተገዘተ ቢናገርም ፖለስ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የሰው ምስክርነትና የሕክምና ማስረጃውን ፖለስ አያይዞ ምርመራውን ቀጠለ። ሰውየው ማሰረጃው ከተገኘበት በኋሏ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ያላመነ በመሆኑ የሰው እና የሰነድ ማስጃዎቹን በመጨመር ወንጀለኝነቱ ተረጋገጠ።

በዚህም ምክንያት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ተራ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የፀቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር

ታምር ሲሳይ የተባለው ተከሳሽ ሰውን ለመግደል ሆን ብሎ በማሰብ ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 5፡15 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ንግሥት አስፋው ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሟች በሱፍቃድ ቶሎናን እየተተናኮለ፣ ነገር እየፈለገው ቆይቶ እስኪ አንተ ወንድ ነህ በለኝ በማለት በተደጋጋሚ ሟችን ሲያስጨንቅ፤ ሟች እስኪ አንተ ወንድ ነህ በማለት ሲመልስለት ተከሳሽ ይዞት የነበረውን ቢላ ከሱሪው ውስጥ በማውጣት ሟች በተቀመጠበት በቀኝ በኩል ትክሻው ላይ በመውጋት በደረሰበት ጉዳት በሕክምና እየተረዳ እያለ በእለቱ ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ተራ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

አስመረት ብሥራት

አዲስ ዘመን  ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You