ጋምቤላ 1899 ዓ.ም የተቆረቆረች ከተማ እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት ይጠቅሳሉ፡፡ በክልሉ ሦስት የብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ማለትም የአኙዋክ፣ የኑዌር እና የማጃንግ ብሎም የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር፣ የኢታንግ ልዩ ወረዳ እና ሌሎች አሥራ ሁለት ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት፣ የመሬት አቀማመጡ ሜዳማና ዝቅተኛ የሆነ፤ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያለው፣ የተለያዩ ድንበር የሚያቋርጡ ትላልቅ ወንዞች ማትም ባሮ፣ ጊሎ፣ አልዌሮ እና አኮቦ የመሳሰሉ ትላልቅ ወንዞች እና የተለያዩ ገራሚ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሐይቆችም መገኛ ስፍራ ነው ፡፡
በዛሬው ዕትማችን የጋምቤላ ክልል አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ እና ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ የተከናወኑ ተጠቃሽ የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጋምቤላ ክልል በእርስዎ ምልከታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ኡመድ፡- የጋምቤላ ክልል በተፈጥሮ የታደለ አካባቢ ነው:: በውሃ ሃብቷ የታወቀች በቁጥር 113 የሚደርሱ የዓሣ ዝርያዎች እንደሚገኙበት ይገመታል:: ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ በገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው እንደ ጉር ያሉ 107 የሚደርሱ የዓሣ ዝርያዎች “Commercially Important fish species” ይገኛሉ::
የኢንቨስትመንት ሁኔታ በሚመለከት፤ ለግብርና ተስማሚ የሆነ Agro-ecology (ወይና ደጋና ቆላ) የአየር ንብረት ያለው ክልል ነው:: ክልሉ ካለው አጠቃላይ 3ነጥብ24 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የቆዳ ስፋት ውስጥ 803ሺ566 ሄክታር ወይንም 26 ከመቶ ሊለማ የሚችል መሬት ነው:: ከዚህ ውስጥ 317ሺ319 ሄክታር በመስኖ የሚለማ ነው::
ሌላኛው በክልሉ አሉ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የእንስሳት ሀብት ነው:: ለአብነትም እስከ 640ሺ500 የቀንድ ከብት፣ 229ሺ897 በጎች፣ ፍየል 268ሺ402፣ 1ነጥብ2 ሚሊዮን ዶሮ፣ የጋማ ከብት 12ሺ794 እና 113ሺ621 የንብ ቤተሰብ ይገኛል::
በተጨማሪም በክልሉ የተለያዩ የማዕድን ሃብቶች ክምችት እንዳሉ ይታወቃል:: በዋናነት የወርቅ ማዕድን በአራት ወረዳዎች፤ አኙዋሃ ዞን ዲማ፣ አቦቦና ጋምቤላ ወረዳዎች፤ ማጃንግ ዞን መንገሺ ወረዳ ይገኛል::
የቱሪዝም ዘርፍ በሚመለከት በክልሉ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ የተለያ ሃብቶች ይገኛሉ:: በ1964 ዓ.ም የተቋቋመውና በኢትዮጵያ በትልቅነቱ የሚታወቀው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ወደ 592ሺ606 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡ 41 አጥቢ፣ 154 አዕዋፍ እንዲሁም ሌሎች ትላልቅ የዱር አራዊቶች ይገኙበታል:: ለቱሪዝም ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው የቴዶና ጅንዎ የቁጥጥር አደን ቀበሌ እና በጋምቤላ ብቻ የሚገኘው ባለነጭ ጆሮ ቆርኬ (White eared kob) መገኛ በመሆኑ ፓርኩን ተመራጭ ያደርጉታል::
በግብርናና ኢንቨስትመንትም በክልሉ በዋናነት በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሩዝ፣ ማሾ፣ ወዘተ የሚመረት መሆኑ፤ በደጋማው አካባቢ የገበያ ምርቶች ቡና፣ ማር፣ ሻይ ቅጠል፣ ቅመማ ቅመም፣ ወዘተ በብዛት ይመረታሉ:: በአሁኑ ወቅትም የበጋ ስንዴ ምርት ማምረት ተጀምሯል:: የአልዌሮ ሰው ሠራሽ የመስኖ ግድብም 10 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደ ጋምቤላ ክልል ሠላም በማስፈን የተመዘገቡ ዐበይት ድሎች ምንድን ናቸው?
አቶ ኡመድ፡- ከሠላም ጋር ተያይዞ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል:: ጋምቤላ ክልል ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ሠላምና መረጋጋት ያለበት ክልል የነበረ ቢሆንም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ግን የፀጥታ ችግር በጣም ፈታኝ የሆነበትና የክልሉን የልማት መሻት በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ አድርጎታል:: አልፎ አልፎ በክልሉ የሚከሰቱ የሠላምና ፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት እና ክልሉን ወደ ልማት ለመመለስ በመንግሥት በኩል በርካታ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል::
የፅንፈኛው ኦነግ ሸኔና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር በጋምቤላ ከተማ በፈፀሙት ጥቃት በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በመከላከልና መልሶ በማጥቃት የደረሰውን ጉዳት መቀልበስ ተችሏል:: በተለያዩ ጊዜያት ብሔርን ዋሻ ባደረገው በአኙዋክና በኑዌር ብሔረሰቦች መካከል የሚፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭት ለመቀልበስና አንፃራዊ ሠላም ለማስፈን እንዲቻል ከሠላም ሚኒስቴርና ከክልልና ከፌዴራል ፀጥታ አካላት ጋር በተሠራው ቅንጅታዊ ሥራ አዎንታዊ ውጤት እየታየ ይገኛል::
በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ሌብነት፣ ዘረፋና የመሳሰሉ ሌሎች ደረቅ ወንጀሎችን ጨምሮ ለመከላከልና የሕዝቡን በሠላም ወጥቶ በሠላም መመለስ ለማረጋገጥ የፀጥታ ኃይሉን ቁመና ከማስተካከል እና ከማጥራት ጀምሮ የሚቀሩ እንዳሉ ሆነው ተደጋጋሚ ሥራዎች በመሥራት አሁን ላይ መድረስ ችለናል::
በሌላ በኩል ክልላችን ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየጊዜው ድንበር አቋርጠው ወደ ክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በመግባት የንጹሐን ሕይወት የማጥፋት፣ የቤት እንስሳትን የመዝረፍና ሕፃናትን አፍነው የመውሰድ አረመኔያዊ ተግባራትን በመመከት ታፍነው የተወሰዱ ሕጻናትን የማስመለስ ሥራ ተሠርቷል::
አዲስ ዘመን፡- ከመልካም አስተዳደር ጎን ለጎን በግርብናው ክፍለ ኢኮኖሚ በክልሉ የተመዘገቡ ውጤቶች ምንድን ናቸው ?
አቶ ኡመድ፡- በግብርና ዘርፍ ክልሉ በርካታ ሊለሙ የሚችሉ መሬቶች እንዳለው ይታመናል:: ከአራት ዓመት በፊት በነበረው የምርት ዘመን ይታረስ የነበረ የእርሻ መሬት በሄክታር 112ሺ826 ሲሆን አሁን በያዝነው የምርት ዘመን 125ሺ706 ሄክታር መሬት ማረስ ተችሏል:: የተገኘ ምርት በሚመለከት ከአራት ዓመት በፊት 2ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ሲገኝ፤ በያዝነው ዓመት ወደ 3ነጥብ18 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል:: በበጋ ስንዴ 54ነጥብ95 ሄክታር ማሳ በዘር እንዲሸፈን በማድረግ ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል::
በመስኖ መሠረተ ልማት የታየው ለውጥ በተመለከተም ከዚህ በፊት ምንም የመስኖ ልምምድ የሌለ ሲሆን ከለውጡ በኋላ 1ሺ235 ሄክታር የመልማት አቅም ያላቸው 12 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀምረዋል:: ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ የመስኖ ፕሮጀክት ዘር ለብሷል፣ አራቱ የመሬት ዝግጅት ላይ ያሉ ናቸው:: ሦስቱ ፕሮጀክቶች የርክክብ ሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን በቀጣይም ወደ ሥራ ይገባሉ:: ሁለቱ በተለያዩ ምክንያቶች የቆሙና ቀጣይ ሥራ የሚፈልጉ ናቸው:: በአጠቃላይ ከእርሻ ሥራችን ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የሚገጥመን የፀጥታ ችግር ባይከሰትና በግብዓት አቅርቦት፣ በድጋፍ ክትትል ቢደገፍ ከዚህ በላይ ምርት ማግኘት እንደሚቻል እናምናለን::
አዲስ ዘመን፡ ለኢኮኖሚው ትልቅ ትርጉም ካላቸው ዘርፎች አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው:: በዚህ ረገድ ክልሉ ምን ላይ ይገኛል ?
አቶ ኡመድ፡- በየጊዜው የሚፈጠረውን የኑሮ ውድነትና ይህንኑ ተከትሎ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ይገኛሉ:: በዚሁ መሠረት የዶሮ እንቁላል ምርት ከነበረበት 17ነጥብ3 ሚሊዮን በ2016 እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት 18ነጥብ8 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል:: የዶሮ ሥጋ ምርት በ2015 ከነበረበት 212ሺ850 ኪሎ ግራም በ2016 የ9 ወር ጨምሮ 373ሺ463 ኪሎ ግራም ማድረስ ተችሏል::
የዶሮ መንደርን በሚመለከት እስካሁን 34 የዶሮ መንደር ማደራጀት የተቻለ ሲሆን በዚህም 9ሺ450 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል:: የማር ምርት ከነበረበት 1ሺ656 ቶን በ2016 እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት 2ሺ656 ቶን ማድረስ ተችሏል:: 68 የማር መንደር በማደራጀት በዘርፉ 20ሺ129 አናቢዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል::
የዓሳ ምርት በ2015 ዓ.ም 2ሺ925 ቶን ከነበረበት በ2016 እስከ ሦስተኛ ሩብ ዓመት 5ሺ453 ቶን ማድረስ ተችሏል:: በዚህም 19 የዓሣ መንደር በማቋቋም 1ሺ810 አርሶ አደሮች ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል:: የወተት ምርት በ2015 ዓ.ም 31ነጥብ82 ሚሊዮን ሊትር ከነበረበት በ2016 ዓ.ም 53ነጥብ74 ማድረስ ተችሏል:: 32 የወተት መንደርም ተቋቁመው 2ሺ100 አርሶ አደሮች ተሳታፊና ተጠቃሚ ተደርገዋል::
አዲስ ዘመን፡- በበጎ አድራጎትና አረንጓዴ አሻራ ሥራዎች እንደ ጋምቤላ ክልል ምን ተከናወነ?
አቶ ኡመድ፡- የደሃና አቅመ-ደካማ ወገኖች ቤቶች ተገንብተዋል:: 134 ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል:: አረንጓዴ አሻራ ልማት በተመለከተ ዘላቂና የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ሥራችን በ2013 እና 14 ዓ.ም አራት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 5ነጥብ7 ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ በ2015 እና 16 ዓ.ም 15ነጥብ2 ሚሊዮን ችግኞች በ6ሺ93 ሄክታር መሬት ላይ በመትከል የፅድቀት መጠኑን 62ነጥብ8 በመቶኛ ማድረስ ተችሏል::
በዚህ 2016 እና 2017 የተፋሰስ ልማትና አረንጓዴ አሻራ ቅድመ ዝግጅታችንም የተለያዩ ዝርያ ያላቸው 10ነጥ2 ሚሊዮን ችግኞችን አፍልተን በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን:: ችግኝ ጣቢያዎችን በማዘመንና በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማድረግ በኩልም ወደ ሥራ ከገቡ 60 የችግኝ ጣቢያዎች ውስጥ 46ቱ እና ከተከላ ቦታዎች ደግሞ 27ቱ ‹‹Geo-reference›› መረጃ የተወሰደባቸው ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከእነዚህ ተግባራት በተጨማሪም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎች እንዳሉ ይታወቃል:: እንደ ክልል የተፈለገው ውጤት ተገኝቷል?
አቶ ኡመድ፡- በ2011 በጀት ዓመት ብቸኛ አንድ ፋብሪካ (የጥጥ መዳመጫ) ነበር:: ከለውጡ በኋላ በከፍተኛ ሁለት፤ በመካከለኛ ስድስት የዱቄትና ብስኩት ምግቦች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል::
በተጨማሪ በተደረገው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የክልሉ ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሽፋንን ማሳደግ ተችሏል:: ለ1ሺ670 ሥራ ፈላጊ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል:: የማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚደግፍ አደረጃጀት በመፈጠሩ ሁለት ከፍተኛ፤ አስራ ሁለት መካከለኛ እና 74 አነስተኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል::
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በማዕድን ሃብት የታደለ መሆኑም ይነገርለታል:: በዚህ ላይ ምን እየተከናወነ ነው?
አቶ ኡመድ፡- ማዕድን ዋናው የዕድገት ተኮር ዘርፍ ተብለው ከተለዩት አንዱ ነው:: በዚሁ መሠረት በወርቅ ምርት እስካሁን ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገ የወርቅ መጠን በሚመለከት 2011 በጀት ዓመት 122ነጥብ24 ኪሎግራም፣ በ2012 ዓ.ም 264ነጥብ24 እንዲሁም በ2013 ዓ.ም 1212 ነጥብ 24 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ሆኗል:: በ2014 ዓ.ም ደግሞ 1206 ነጥብ51፣ በ2015 ዓ.ም 236 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ የተደረገ ሲሆን በ2016 ዘጠኝ ወራት ብቻ 225 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ተደርጓል:: ይህንኑ የሚመረተውን የወርቅ ምርት በየወቅቱ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ በማድረግ ክልሉ ለሀገር ልማት የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡- ሃብት ከመጠቀም ጎን ለጎን ገቢ አሰባሰቡ ላይ ያለው የክልሉ አቋም እንዴት ይገለፃል?
አቶ ኡመድ፡- ክልሉ የልማት ሥራዎችን እየሠራ በገቢ አሰባሰብም በትኩረት የሚሠራ መሆኑም ይታወቃል:: ዘላቂነት ያለው የሕዝብ ፍላጎትን ያማከለ ልማት ለማምጣት የገቢ አቅምን ለማሳደግ የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎች ተሠርተዋል:: በዚሁ መሠረት ከራስ ገቢ 2011 በጀት ዓመት 603ነጥብ8 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፤ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ወደ 1ነጥብ6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል::
ከጋራ ገቢ ከፌዴራል መንግሥት በተጀመረበት በ2013 በጀት ዓመት ብር 97ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የነበረው በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራትን ጨምሮ 530 ሚሊዮን ደርሷል:: ይሁን እንጂ ካለው የልማት ጥያቄ አንፃር ይህ በቂ ነው ባይባልም የታክስ መሠረቱን በማስፋት ገቢያችንን ለማሳደግ ጥናቶች ለማስጠናት እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን::
በማኅበራዊ ልማት ዘርፍም ክልሉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል:: የአምስት ዓመት የፓርቲያችን የማኅበራዊ ብልፅግና ግብ ለማሳካት እንደ ክልል መንግሥት የተለያዩ ተግባራት እያከናወንን እንገኛለን:: በዚሁ መሠረት የትምህርት ፍትሐዊ ተደራሽነት ላይ በተሠራው ሥራ በተማሪ ቁጥር፣ በትምህር ቤቶች ግንባታ፣ በመምህራን ልማትና በሌሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያሳየ መጥቷል::
በትምህርት ለትውልድ መርሐ ግብርም አያሌ ተግባራት ተከናውነዋል:: የትምህርት ተቋማትን ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በንቅናቄ በተሠራው ሥራ፡ በኅብረተሰቡና አጋር አካላትን በማስተባበር የተገነቡ 378 አንደኛ ደረጃ፣ 24 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፣ 237 አንደኛ ደረጃ እና 13 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጠግነዋል:: የተደረገው ተሳትፎ በገንዘብ ሲተመን ወደ 230 ሚሊዮን ብር ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ በጤናና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች የተመዘገቡ ስኬቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ኡመድ፡- መከላከልና አክሞ ማዳን መርሕ ያደረገው የጤና ፖሊሲያችንን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል:: በእናቶች ጤና አገልግሎት ዘርፍ ቤተሰብ ተኮር የሆነ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በገጠር በማስፋፋት፤ ከአምስት ዓመት በፊት 17ነጥብ5 በመቶ የነበረው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋን በአሁኑ ጊዜ 24 በመቶ ደርሷል::
የወሊድና የድኅረ ወሊድ የጤና አገልግሎቶች ከነበረበት ከ36 ከመቶ በታች ሽፋን በአሁኑ ወቅት የቅድመ ወሊድ አገልግሎት ሽፋን ወደ 77 በመቶ፣ በሠለጠኑ ጤና ባለሙያ የተሰጠው የማዋለድ አገልግሎት ወደ 42ነጥብ7 በመቶ፣ የድህረ ወሊድ ሽፋን ደግሞ ወደ 42ነጥ6 በመቶ፣ ለቅድመ ወሊድ፣ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ እና የሚያጠቡ እናቶች የHIV ምክርና ምርመራ አገልግሎት ወደ 95 በመቶ አድጓል::
ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ኤች አይ ቪ ኤድስ ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝባቸውና መድኃኒት ለሚያስፈልጋቸው እናቶች የፀረ ኤች አይ ቪ ሕክምና እንዲጀምሩ ወይንም እንዲወስዱ በማድረግ ሽፋኑን ወደ 95 በመቶ ማድረስ ተችሏል:: የሕፃናት ክትባት ሽፋን በተመለከተ ከ65 ከመቶ በታች የነበረው የሽፋን መጠን በተደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ውጤቶች ታይተዋል::
የፔንታ ቫለንት አንድ ክትባት መቶ በመቶ፣ የፔንታ ቫለንት ሦስት ክትባት 95ነጥብ9 በመቶ፣ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት 85ነጥብ3 በመቶ እና ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሕፃናት 82ነጥብ7 ማድረስ ተችሏል::
በሽታ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድም የተከናወኑ በርካታ ተግባራት አሉ:: ክልሉ ወባማ አካባቢ ከመሆኑ አንጻር በወባ በሸታ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ሕመምና ሞት ለመቀነስና የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ፤ የቤት ውስጥ የፀረ-ትንኝ ኬሚካል ርጭት እና በኬሚካል የተነከረ የመኝታ አጎበር በመስጠት የመከላከል ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ተችሏል:: የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል በተሠሩ ሥራዎች ደግሞ በክልሉ ምንም ዓይነት የኦክስጂን ፕላንት የሌለበትን አዲስ በመትከል በከፍተኛ ደረጃ ከኦክስጂን እጥረት የተነሳ ሲከሰት የነበረውን የሪፈራልና አደጋን መቀነስ ተችሏል::
በማኅበረሰብ ጤና መድን አገልግሎትም ሰፋፊ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ የጤና ፋይናንስ ሥርዓቱን ለማጠናከር በአሁኑ ሰዓት ካሉት 14 ወረዳዎች 12ቱ ወይንም 85 በመቶ ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን 52 በመቶ የማኅበረሰቡ አባላት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል:: የጤና መሠረተ ልማት አገልግሎት አኳያም ከስድስት ዓመት በፊት በክልሉ አንድ ሆስፒታል ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን የክልሉ የጤና መሠረተ ልማት ሽፋን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት አንድ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ አራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣ 30 ጤና ጣቢያዎች እና 150 ጤና ኬላዎች እና ሌሎችም በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል::
የሕክምና ባለሙያዎችን አቅም ከማጎልበት አንጻር በተከነወኑ ተግባራት ከስድስት ዓመት በፊት ሁለት ስፔሻሊስት ሐኪም፣ ሦስት ፋርማሲስት፣ አምስት አዋላጅ ነርሶች የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ላይ በተለያዩ ሙያዎች ስምንት ስፔሻሊስት ሐኪሞችና በተቀሩት ዋና ዋና የሙያ ዘርፎች በሁሉም ሆስፒታሎች በቂ የሰው ኃይል ማሟላት ተችሏል::
በውሃ ዘርፍ ልማት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል:: በፊት የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በስምንት ከተሞች ብቻ የነበረውን በማሳደግ አሁን ላይ ከአኮቦ (ቴርጎል ከተማ) በስተቀር በክልሉ 13ቱም ከተሞች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት አግኝተዋል:: በገጠሩ ቀደም ሲል ለኅብረተሰቡ የንፁሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚደርሰው ከእጅ ፓምፕ ከሚመነጭ ውሃ ብቻ ነበር:: አሁን ላይ በርካታ የገጠር ማኅበረሰቦችን ለመድረስ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከ23 በላይ የገጠር ቧንቧ ስርጭት ግንባታዎችን (RPS) በማጠናቀቅ ለገጠር ኅብረተሰብ ለማድረስ ተችሏል::
በአጠቃላይ አሁን ላይ በገጠር 1ሺ204 ውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ:: የትምህርት እና የጤና ተቋማት የመጠጥ ውሃ ተቋማት ብዛት ቁጥር አነስተኛ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት 109 ትምህርት ቤቶችና 86 የጤና ተቋማት የንፁሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል:: በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም አሁን ላይ የክልሉ የመጠጥ ውኃ ሽፋን በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት 76ነጥብ8 በመቶ ላይ ይገኛል፤ ይህም በገጠር 86 በመቶ በከተማ 64 በመቶ ነው:: በአጠቃላይ ከ387ሺ943 ህዝብ በላይ የንፁሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ሆኗል::
አዲስ ዘመን፡- የክልሉን አጠቃላይ አሠራር ለማዘመን የቴክኖሎጂ ዘርፍ ሚናው የጎላ መሆኑ ይታወቃል:: በዚህ ረገድ ምን ተሠራ?
አቶ ኡመድ፡- በ”ICT”ዘርፍ የተገኘ ስኬት በሚመለከት፤ 12 ተቋማት የወረዳ ኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል:: አምስቱ ማዕከላት የቪዲዮ ኮንፈረንስ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው:: 19 የመንግሥት ተቋማት በቀጣይ የወረዳ ኔት ኔትዎርክ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የወረዳ ኔት ላን አይፒ አግኝተዋል:: በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) በክልላችን በቅርቡ ነው የተጀመረው:: እስከ ዛሬ ድረስ 3ሺ456 ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ የተወሰኑት ብሔራዊ መታወቂያውን ወስደዋል::
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ስድስት ዓመታት ከመሠረተ ልማት አኳያስ ምን ተከናውኗል?
አቶ ኡመድ፡- የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭት ለማረጋገጥ በለውጡ ዓመታት የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት በርካታ የመንገድ፣ የመብራትና የቴሌኮም ማስፋፊያ ተግባራት ተከናውነዋል::
በመንገድ ልማት ዘርፍ ብንመለከት፤ ከለውጡ በፊት አንድ ለእናቱ የነበረው የጎሬ-ጋምቤላ የአስፋልት መንገድ ብቻ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በፌዴራል መንግሥት የተጀመሩ 612ነጥብ24 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስድስቱ (አቦቦ-ሜጢ፣ ጎግ-ጆር-አኮቦ፣ ጋምቤላ-አቦቦ-ዲማራድ፣ ላሬ-ጂካዎ-ኝንኛንግ፣ ፒኝውዶ-ጊሎ ወንዝ፣ አኩላ-አቻኛ) በተሻለ የግንባታ ደረጃ ላይ የሚገኙና በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል:: ቀሪዎቹ ሦስቱ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸው የቆሙ ናቸው:: እነዚም (ጋምቤላ-ኢሊያ፣ ኢሊያ-መኩዌይ እና አቦቦ-ሜጢ ኩቢጦ ማዞሪያ) ናቸው::
በራስ አቅምና በአጋር አካላት ትብብር የሚገነቡትን በሚመለከትም በወረዳዎች ያለውን የመንገድ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በስምንት ወረዳዎች ከ80 ኪሜ በላይ የሆኑ የገጠር መንገዶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል:: በአጠቃላይ ቀበሌ ከቀበሌ የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ አጠቃላይ የመንገድ ኔትዎርክ ርዝመት በ2010 በጀት ዓመት ከነበረው 1ሺ530 ኪሎ ሜትር ርዝመት በ2016 በጀት ዓመት ወደ 2ሺ153 ኪ.ሜ ለማድረስ ተችሏል::
በቴሌኮም ዘርፍ ደግሞ፤ ከለውጡ በፊት በከተማ ብቻ የተወሰነው የስልክ ተደራሽነት በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት ከአኮቦ ወረዳ በስተቀር በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ከተሞችና ወረዳዎች በከተማው ውስጥ ቋሚ የስልክ መስመር ወይም የቤት ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል::
የሞባይል እና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በብሮድባንድ፣ 2ጂ እና 3ጂ የኔትወርክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል:: ጋምቤላ፣ ፒኝውዶ፣ አቦቦ፣ ኢታንግ፣ ሜጢ እና ዲማ ከ2014 ጀምሮ የ4ጂ LTE አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል:: በኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘርፍም በለውጡ ዋዜማ ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ ለጋምቤላ ቅርብ የሆኑ ከተሞች ብቻ የመብራት አገልግሎት ነበራቸው:: በአሁኑ ሰዓት ከዋንቶዋ እና አኮቦ ወረዳዎች በስተቀር ሁሉም የመብራት ተጠቃሚ ሆነዋል::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍላችን ስም እያመሰገንኩ፤ መልዕክት ካለ መጨመር ይችላሉ::
አቶ ኡመድ፡- በአጠቃላይ በለውጡ ዓመታት በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚና መሠረተ ልማት፣ በማኅበራዊ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል:: ይሁን እንጂ በየጊዜው የሚፈጠሩ እና ከልማትና ብልፅግና ጉዞ ዓይናችንን እንድናነሳ የሚያደርጉን በውስጥ ብሔርን ዋሻ ያደረገ ጽንፈኛ ቡድን በውጪ ደግሞ ዕድገታችንን የማይሹ ወገኖች በሚገጥሙን ሴራዎች እና ፈተናዎች በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባንገኝም ችግሮቹን እየተቋቋምን እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በራሱ የአሸናፊነት ምልክት ሆኖ እናየዋለን::
በመሆኑም በቀሪ ጊዜያት በጊዜ የለንም ስሜት መፍጠንና ያመለጡንን ወርቃማ ዕድሎች መጠቀም የሕልውና ጉዳይ አድርገን እናየዋለን::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም