በሃውቲዎች ጥቃት የደረሰባት መርከብ በቀይ ባህር መስመጧ ተነገረ

በየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን ባለፈው ሳምንት ጥቃት የተፈጸመባት መርከብ መስጠሟ ተነገረ።

የላይቤሪያን ሰንደቅ አላማ የምታውለበልበውና የግሪኩ “ቱተር” ኩባንያ ንብረት የሆነችው መርከብ በቀይ ባህር መስመጧን የብሪታንያ የማሪታይም ንግድ አስተዳደር አስታውቋል።

“ቁርጥራጮች እና የሚፈስ ነዳጅ መርከቧ ለመጨረሻ ጊዜ በታየችበት አካባቢ ታይቷል” ያለው ተቋሙ፤ ይህም መርከቧ መስጠሟን እንደሚያመላክት ገልጿል።

ሃውቲዎች ከሰባት ቀናት በፊት በውሃ ውስጥ በሚጓዝ ድሮን ጥቃት የተፈጸመባት “ቱተር” መርከብ ስለመስመጧ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።

ጥቃቱ ሲፈጸም በመርከቧ የሞተር ክፍል ውስጥ የነበረ ፊሊፒናዊ መርከበኛ ህይወቱ ማለፉን የአሜሪካ ባለስልጣናት ቢገልጹም ማኒላ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

በቀይ ባህር በሃውቲዎች ጥቃት መርከብ ሲሰጥም የ”ቱተር” ሁለተኛው ነው።

ባለፈው መጋቢት ወር ማዳበሪያ የጫነችው የብሪታንያ “ሩብይማር” መርከብ በቀይ ባህር መስመጧ ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ድብደባ የሚቃወሙት የሃውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል፣ አሜሪካና ብሪታንያ ጋር ግንኙነት አላቸው ባሏቸው መርከቦች ላይ ከ50 በላይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።

ዋሽንግተን ከጥር ወር ጀምሮ አጋሮቿን አስተባብራ በቡድኑ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ስትፈጽመ መቆየቷ ይታወሳል።

ከሦስት ቀናት በፊት በሆዴይዳህ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና በካማራን ደሴት አቅራቢያ ከብሪታንያ ጋር የአየር ድብደባ መፈጸሟን ነው ሬውተርስ የዘገበው።

ይሁን እንጂ የዋሽንግተን እና ለንደን ድብደባ የሃውቲ ታጣቂዎችን አንድ መርከብ ከመያዝና ሁለት ከማስመጥ አልገታቸውም።

የቡድኑ የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት የመርከብ ኩባንያዎች አቋራጩን የስዊዝ ካናል አይተው በረጅሙ የኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ (ደቡብ አፍሪካ) መስመር እንዲጓዙ አድርጓቸዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ ደህንነት ተቋም በቅርቡ ያወጣው ሪፖርትም በቀይ ባህር የሚያልፉ እቃ የጫኑ መርከቦች ቁጥር ከታህሳስ ወር ወዲህ በ90 በመቶ መቀነሱን ነው የጠቆመው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You