በሰው አእምሮ ውስጥ በሚቀበሩ ቺፕሶች ላይ ሁለተኛ ሙከራ ሊደረግ ነው

የአሜሪካዊው ቢሊየነር ኢሎን መስክ የሆነው የባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ኒውራሊንክ ባለፈው ጥር ወር የመጀመሪያውን ችፕስ በሰው አእምሮ ውስጥ የቀበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ሙኩራ እየተዘጋጀ ነው።

የመስክ የባዮቴክ ኩባንያ የ30 ዓመት እድሜ ባለው ግለሰብ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ችፕስ የገጠመው ባለፈው ጥር ወር ነበር። የአነስተኛ ሳንቲም መጠን ያላትን ቺፕስ የሰው ልጅን እንቅስቃሴ ፍላጎት ከሚያዘው የአእምሮ ክፍል ላይ በቀዶ ጥገና እንድትቀመጥ ተደርጓል። ይህቺ ቺፕስ “የአእምሮን እንቅስቃሴ በመመዝገብ እና የእንቅስቃሴ ፍላጎትን ወደሚተረጉም መተግበሪያ ወይም አፕ” ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ ውላለች።

ኒውራሊንክ ባለፈው ዓመት በሰጠው መግለጫ ፕሪሳይዝ ሮቦቲካሊ ኢምፕላንትልድ ብሬን ኮምፒውተር (ፒአርአይኤሜኢ) ፕሮግራም ዓላማ ሙሉ በሙሉ የሚቀበር እና ዋየርለስ ብሬን ኮምፒውተር በማልማት ሰዎች በማሰብ ብቻ የኮምፒውተር ከርሰር ወይም ኪቦርድ እንዲቆጣጠሩ ማስቻል እንደሆነ ገልጾ ነበር።

ይህ አይነስውራንን፣ ሰውነታቸው የማይታዘዝላቸውን እና የመሳሰሉ የአካል ጉዳት ያለባቸውን እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የአእምሮ ውስንነት፣ ድብርትና ስኪዞፈርኒያ አይነት በሽታዎች ያሉባቸውን ሰዎች ለማከም መንገድ የሚጠርግ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር (ኤፍዳኤ) የመጀመሪያው የቺፕስ ቀበራ ወይም ቸፕስ ኢምላንቴሽን ያጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር ነበር።

ባለፈው ጥር ወር የቺፕስ ቀበራው ከተካሄደ ከበርካታ ሳምንታት በኋላ የተቀበረለት ሰው “ሙሉ በሙሉ ማገገሙንና ምንም ህመም እንደሌለበት” እንዲሁም የኮምፒውተር ማውዝን “በማሰብ ብቻ” በስክሪን ላይ ማንቀሳቀስ መቻሉን መስክ ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል።

ነገርግን ባለፈው ግንቦት ወር በአእምሮ ውስጥ የተቀበረች ቺፕስ ከቦታዋ በመንሸራተቷ ምክንያት ትንሽ ችግር አጋጥሞት እንደነበር አምኗል። ያም ሆኖ ኤፍዲኤ ሁለተኛው የቺፕስ መቅበር ሙከራ እንዲደረግ ፍቃድ መስጠቱን ዋል ስትሬት ባለፈው ወር ዘግቧል።

በዚህ ወር ይካሄዳል በተባለው ሁለተኛው ሙከራ፣ ቺፕሱ እንዳይንሸራተት ጠለቅ ብሎ ወደ አእምሮ ውስጥ እንዲቀበር ይደረጋል ተብሏል። ያም ሆኖ ኤፍዲኤ ሁለተኛው የቺፕስ መቅበር ሙከራ እንዲደረግ ፍቃድ መስጠቱን አል አይን ወር ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You